"ኦዴፓ የሠባሪ/ተሠባሪ ትርክት ማቀንቀኑ የሃገሪቷን አንድነት የሚጎትት ነው"ኢዜማ

የኦዲፒና ኢዜማ አርማዎች

ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በተከበረውን የኢሬቻ በዓል ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያደረጉት ንግግር የሚያብራራ የሚመስል መግለጫ ፓርቲያቸው ኦዴፓ ዛሬ አውጥቷል።

ቅዳሜ ዕለት በበዓሉ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አደረጉት የተባለው ንግግር በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ በተለይ አንዳንድ የአዴፓና የኦዲፒ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ በማህበራዊ መድረኮች ላይ ሲወዛገቡና ጠንከር ያሉ ቃላትን ሲለዋወጡ ቆይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ትናንት ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተባለው ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ላይ ጉዳዩን በማንሳት ትችትን ሰንዝሯል።

ዛሬ ጠዋት የወጣው የኦዲፒ መግለጫ በበኩሉ የምክትል ፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ የተከሰተውን ውዝግብ ለማጥራት የሰጠው መግለጫ መሆኑን ባያሰፍርም ያነሳቸው ነጥቦች ግን ንግግራቸውን የተመለከቱ እንደሆነ የሚያመላክቱ ጉዳዮችን ይዟል።

"መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ያስገባል"ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

"ምን ተይዞ ምርጫ?" እና "ምንም ይሁን ምን ምርጫው ይካሄድ" ተቃዋሚዎች

ኢዜማ የተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮችን በዳሰሰበትና ትናንንት ባወጣው መግለጫ ላይ ይህንኑ ጉዳይ አንስቶ ትችት ሰንዝሯል።

ፓርቲው "የኦዴፓ አደረጃጀት የሰላም፣ የይቅርታ እና የምስጋና ታላቅ በዓል የሆነውን ኢሬቻን መጥለፉ ሳያንስ የተለመደውን የ100/150 ዓመት የሠባሪ/ተሠባሪ ትርክት ማቀንቀኑ ሀገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የሚጎትት" እንደሆነ አመልክቷል።

ኢዜማ በመግለጫው ላይ እንዲህ ዓይነቱ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም በመጠየቅ፤ "የአገር አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማምጣት ሂደት የምንጠቀምበት ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን እናሳስባለን" ሲል መክሯል።

ኢዜማ አክሎም የአዲስ አበባ ህዝብ የተለያዩ አፈናዎችና ትንኮሳ እየደረሰበት እንደሆነና "የከተማ ሕዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነና በሕገ መንግሥቱም እውቅና የተሰጠውን ራሱን የማስተዳደር መብት ለመሸርሸር የሚደረግ ምንም ዓይነት አካሄድን አይቀበልም" ብሏል።

የአዲስ አበባ ህዝብ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ለመቃወምና ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች እንደሚደግፍ በመግለጫው አስታውቋል።

ዛሬ ጠዋት ባወጣው የኦዲፒ መግለጫ የህዝቡን ዘርፈ ብዙ ፍላጎቶች ለማሟላት ከእህት ድርጅቶችና ከአጋሮቹ ጋር ኅብረት ፈጥሮ ሲታገል፣ በጋራ መሥዋዕትነት ሲከፍል መቆየቱንና አሁንም እየታገለ መሆኑን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ግምቶች አሉ

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን እንደማትቀበል አሳወቀች

አክሎም "በታሪክ ውስጥ የተሠሩ ስህተቶችን በጋራ ነቅሶ ማረም፣ እንዲሁም ካለፈው ትምህርት ወስዶ ተጨማሪ ስህተቶችን ባለመድገም፣ ብሎም የነበሩንን ድሎች አስፍቶና አጠናክሮ በማስቀጠል የመጪውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት" ዋነኛ አላማው እንደሆነም አመልክቷል።

መግለጫው ኦዲፒ ሲያደርግ የነበረው ትግል "ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር እንጂ ከሕዝቡ ጋር አልነበረም። ሕዝቦች ሲጨቆኑ እንጂ ሲጨቁኑ አልኖሩም። ከየትኛውም ወገን የመጡ ጨቋኝ ገዥዎች ጥቅማቸውን እንጂ የመጡበትን ወገን እንደማይወክሉ በጽኑ ያምናል" ይላል።

ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፈዉ ታሪካቻው ከተፈጸሙ ስህተቶች ይልቅ በአንድነት የሚያስተሳስሯቸው መልካም ነገሮች በርካታ እንደሆኑ ጠቅሶ "ከመጣንበት መንገድ በላይ ወደፊት አብረን የምንጓዘዉ ረጅም ጉዞ እንደሚረዝም" ፓርቲው እንደሚረዳ ጠቅሷል።

በተለይም መግለጫው በኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች መካከል ያለው የወንድማማችነት ትስስር በቀላሉ የሚበጠስ እንዳልሆነ በማንሳት "የአዴፓና የኦዴፓ የዓላማ እና የተግባር አንድነት ከዚህ በፊት ያጋጠሙትን ፈተናዎች እንዳለፈ ሁሉ ወደፊትም መሰናክሎቹን ሁሉ እየተሻገረ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርቲያችን በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ደግመን ለማረጋገጥ እንወዳለን" ብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች