ሜክሲኮ ውስጥ አንድ ከንቲባ በመራጮቻቸው መኪና ላይ ታስረው ተጎተቱ

ከንቲባው ከመኪና ጋር ታስረው ሲጎተቱ Image copyright TWITTER/@TINTA_FRESCA
አጭር የምስል መግለጫ ከንቲባው ከመኪና ጋር ታስረው ሲጎተቱ ከሚያሳየው ቪዲዮ ላይ የተገኘ ምስል

በደቡባዊ ሜክሲኮ የአንድ አካባቢን ከንቲባ ከጽህፈት ቤቱ አስወጥተው የጭነት መኪና ኋላ አስረው ጎዳናዎች ላይ ጎትተዋል ተብለው የተጠረጠሩ አስራ አንድ ሰዎች ተያዙ።

በከንቲባው ልዊስ ኤስካንደን ላይ ድርጊቱ ሲፈጸም ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ያስቆመ ሲሆን ከንቲባውም ከባድ ጉዳት ሳይደርስባቸው መትረፋቸውም ተነግሯል።

ከንቲባው የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ጊዜ የአካባቢውን መንገድ እጠግናለሁ ብለው የገቡትን ቃል አልፈጸሙም በሚል ነው ይህ ጥቃት የተሰነዘረባቸው። የአካባቢው አርሶ አደሮች በከንቲባው ላይ ጥቃት ሲፈጸሙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ግምቶች አሉ

ከጥቃቱ በኋላ ጸጥታ ለማስከበር ተጨማሪ የፖሊስ መኮንኖች ወደ ቺያፓስ ግዛት መሰማራታቸው ተነግሯል።

ሜክሲኮ ውስጥ ከንቲባዎችና ፖለቲከኞች ዕፅ አዘዋዋሪዎች የሚጠይቋቸውን ነገር አላሟላም ወይም አልተባበርም በሚሉ ጊዜ ለጥቃት መጋለጣቸው የተለመደ ነገር ሲሆን፤ ፖለቲከኞች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል መፈጸም ሲሳናቸው እንዲህ አይነት ጥቃት መሰንዘር የተለመደ አይደለም።

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ከንቲባም በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ የአፈናና የግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ እመሰርታለሁ ብለዋል።

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች የቀረጹት ነው በተባለ ቪዲዮ ላይ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከንቲባውን ከጽህፈት ቤታቸው ጎትተው በማስወጣት ከመኪናው ኋላ በጉልበት ሲጭኗቸው ይታያል።

መንገድ ላይ ከተተከሉ የደህንነት ካሜራዎች የተገኘው ምስል ደግሞ የከንቲባው አንገት ላይ ገመድ ታስሮ ሳንታ ሪታ በተባለው ጎዳና ላይ በመኪናው ሲጎተቱ ያሳያል።

አሥመራን አየናት፡ እንደነበረች ያለችው አሥመራ

መኪናውን በማስቆም ከንቲባውን ከዚህ ጥቃት ለማስጣል በርካታ ፖሊሶች ጥረት ያደረጉ ሲሆን፤ በጥቃት አድራሾቹን በፖሊሶች መካከል በተፈጠረው ግብግብ ብዙ ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከአራት ወራት በፊት ደግሞ ከንቲባው ላይ ጥቃት ለማድረስ ወደ ጽህፈት ቤታቸው የሄዱ ሰዎች ቢሯቸው ውስጥ ስላላገኟቸው ንብረት አውድመው መሄዳቸው ተነግሯል።

ለከንቲባነት ከተደረገው ውድድር ቀደም ብሎ አሁን ጥቃት የተፈጸመባቸው ከንቲባ ከእጩ ተፎካካሪያቸው ደጋፊዎች ጋር አምባጓሮ ውስጥ ገብተው ነበር ተብለው ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ነበር። በኋላ ግን ማስረጃ ስላልተገኘ ተለቀዋል።