የወላጆች ራስ ምታት እየሆነ የመጣው የልጆች የጌም ሱስ

ጌም የሚጫወት ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለወላጆች ልጆቻቸው በተንቀሳቃሽ ስልክም ሆነ በበይነ መረብ የተለያዩ ጌሞች ላይ ተጠምደው እንደማየት የሚያሳስባቸው ነገር የለም።

ግን ይህ ታሪኩን የምናጋራችሁ አባት ከአቅሜ በላይ ሆኖ የቁም ቅዠት ሆኖብኛል ይላል። ስቲቭ ይባላል፤ የሚወደው ልጁ ከተራ ጌም ተጫዋችነት አልፎ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሰ ሱሰኛ ሆኗል።

ከዚህም ባለፈ መቆጣጠር የማይችለው የቁማር ሱስ ውስጥ ተዘፍቋል።

"ልጄ በጌሞች እንዲህ ይሆናል ወይም መጨረሻው የቁማር ሱስ ይሆናል ብዬ በፍጹም ገምቼ አላውቅም።''

የስቲቭ ልጅ በሃያዎቹ መጀመሪያው ውስጥ የሚገኝ ወጣት ነው። በልጃቸው ምክንያት ስቲቭና ባለቤቱ ለሦስት ዓመታት ተሰቃይተዋል። ''እኛ ያየነውን መከራ ማንም ቤተሰብ ማየት የለበትም። ልጃችን የቁማር ሱሰኛ መሆኑን ስናውቅ ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ገብቶን ነበር።''

የስቲቭ ልጅ ለትምህርቱ የሚሰጠውን ሳምንታዊ ወጪውን በደቂቃዎች ውስጥ የሚያጠፋ ሲሆን ከአቅሙ በላይ ሲሆንበትም ቤተሰቦቹን አማክሯቸው ነበር። እነሱም በዚሁ የሚገላገሉ መስሏቸው ማንኛውም ቤተሰብ እንደሚያደርገው ሙሉ እዳውን ከፈሉለት። ነገር ግን ብዙ ነገሮች ተከትለው መጥተዋል።

ከአንድ ከዓመት በኋላ ስቲቭ ልጃቸው ከእራሱ አልፎ የሰዎችን ገንዘብ እያስያዘ መቆመር መቀጠሉን ሲሰማ በጣም ነበር ያዘነው። የሚያስይዘው ገንዘብ ደግሞ እጅጉን የተጋነነና ትልቅ እዳ ውስጥ የዘፈቀው ነበር።

''በበይነ መረብ ካርታ ነበር የሚጫወተው። እጅግ አስፈሪ ሁኔታ ነበር።''

ስቲቭና ባለቤቱ ልጃቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለ የተረዱት በዚህ ወቅት ነው። ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ሆነ ማንን ማማከር እንዳለባቸው ምንም ዓይነት እውቀቱ አልነበራቸውም።

''የቁማርተኛው ቤተሰቦች መባልን በመፍራትና ልጃችን ገንዘብ የተበደራቸውን ጎረቤቶች ዓይን ላለማየት እራሳችንን ከማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እስከ ማገድ ሁሉ ደርሰን ነበር።''

''ተስፋ ቆርጠን ፊታችንን ወዴት ማዞር እንደምንችል ግራ ገብቶን ነበር። ለራሳችን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ለብዙ ወራት ምርምሮችን ስንሰራም ነበር'' ይላል ስቲቭ።

በሠሩት ጥናት መሠረትም የልጃቸው ሱስ የጀመረው ገና የ12 ወይም የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ እንደሆነ ደርሰውበታል። መጀመሪያ አካባቢ የሚያዘወትራቸው ጨዋታዎችም እግር ኳስና የመኪና ውድድር የመሳሰሉትን ነበር።

በወቅቱ መኝታ ቤቱ ውስጥ ሆኖ ለሰዓታት ጌሞቹን የሚጫወት ሲሆን ጓደኞቹም ተመሳሳይ ነገር ያደርጉ ስለነበር፤ ብዙም አሳስቦን አያውቅም ይላል ስቲቭ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲያስታውስ።

"ጨዋታዎቹ ምን ዓይነት እንደሆኑና ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀሙ ምንም የማውቀው ነገር አልበረም" የሚለው ስቲቭ ከመጀመሪያው ጀምሮ ተከታትዬው ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ ላይፈጠር ይችል ነበር ብሎ ያስባል።

''ለረጅም ሰዓታት እግር ኳስ በመጫወት የተጀመረው ሱስ ቀስ በቀስ ወደ ቁማር ሱስ ተቀይሯል።''

በቅርቡ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው 55 ሺህ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ11 እስከ 16 የሚደርሱ የእንግሊዝ ታዳጊዎች አሳሳቢ የሚባል የቁማር ሱሰኞች ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸው ስለሱሳቸው ብዙም አያውቁም።

ከሦስት ዓመታት ትግል በኋላ ስቲቭ የአስተማሪነት ሥራውን ትቶ ልጆች የቁማር ሱስ ውስጥ እንዳይገቡ የሚያስተምርና ቤተሰቦችን የሚደግፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁሟል።

''ነገር ግን በጣም የተወሳሰበ ነገር ነው። ቤተሰቦች ልጆቻቸው ለረጅም ሰዓታት ኢንተርኔት ላይ ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ምን እየሠሩ ነው ብለው ሊጠይቁ ይገባል'' ይላል።

ልጆች ምን ዓይነት ጌሞችን እንደሚጫወቱ መጠየቅ፤ ቢቻል ደግሞ አብሮ ለመጫወት መሞከር ነገሮችን ለመቆጣጠርና በአጭሩ ለመቅጨት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ስቲቭ ይመክራል።

ምንም እንኳን በኢንተርኔት የሚደረጉ ጨዋታዎችን በትምህርት ቤቶች አካባቢ ወይም ከ25 ዓመት በታች ለሆኑ ዜጎች እንዳይተዋወቁ በእንግሊዝ ሕግ የተከለከለ ቢሆንም ብዙም ውጤታማ የሆነ አይመስልም።

ታዳጊዎቹ በትምህርት ቤታቸው አልያም በሚያዘወትሯቸው አካባቢዎቹ ጌሞቹ ባይተዋወቁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ማስታወቂያዎቹን በኢንተርኔትም ሆነ በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ያገኟቸዋል።

ከዚህ ባለፈም ድርጅቶቹ ማስታወቂያዎቻቸውን በታዋቂ ሰዎችና በትልልቅ ስፖርተኞች ስለሚያሠሩ ታዳጊዎቹ ላይ ተጽእኖ የማሳደር አቅማቸው ከፍተኛ ነው።

ስቲቭ እንደሚለው እሱና ቤተሰቡ አሁን በጥሩ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኙት። በተፈጠረው ነገር ከማዘንና ከመሸማቀቅ ይልቅ በጊዜ ወደ መፍትሄ ማፈላለግ መሄዳችን ጠቅሞናል ይላል።