ሻኪል አፍሪዲ፡ ኦሳማ ቢን ላደንን ለማግኘት ሲ አይ ኤን የረዱት ዶክተር

ሻኪል አፍሪዲ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ዶክተር ሻኪል የቀረቡባቸውን ክሶች የተቃወሙ ሲሆን ፍትህ እንዳላገኙ ተናግረዋል

የአልቃይዳን መሪ ኦሳማ ቢን ላደንን ለማግኘት የአሜሪካ የስለላ ድርጅትን ሲ አይ ኤን ረድተዋል የተባሉትና በእስር ላይ የሚገኙት ፓኪስታናዊ ዶክተር ይግባኝ ጠየቁ።

የዶክተር ሻኪል አፍሪዲ የፍርድ ጉዳይ በክፍት ፍርድ ቤት ሲታይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ነገር ግን አቃቤ ሕግ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው በመጠየቁ ጉዳያቸውን ለማየት የ12 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

አልቃይዳ ከወዴት አለ?

የኦሳማ ቢን ላደን ልጅ 'በአየር ጥቃት መገደሉ' ተነገረ

የዶክተሩ ሚና በፓኪስታኖች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን የፈጠረ ቢሆንም ዶክተሩ ግን ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲሉ የቀረበባቸውን ክስ ተቃውመውታል።

በዓለማችን እጅግ ተፈላጊ የነበረውን ቢን ላደንን ለማደንና ለመግደል ዶክተሩ ተጫውተውታል በተባለው ሚና እስከ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2011 ድረስ ይፋዊ የሆነ ክስ አልተመሰረተባቸውም ነበር።

ከዚያ በኋላ በዶክተሩ መታሰር የተቆጣችው አሜሪካም ለፓኪስታን የምትሰጠውን ዓመታዊ የገንዘብ ድጋፍ ከ33 ሚሊየን ወደ 1 ሚሊየን ዶላር ቀንሳለች።

ምንም እንኳን ዶክተሩ በአሜሪካውያን እንደ ጀግና የሚወደሱ ቢሆንም በፓኪስታኖች ዘንድ ደግሞ ከዳተኛና አገሪቷን ያዋረዱ ተደርገው ይቆጠራሉ።

Image copyright Reuters

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በ2016ቱ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከተመረጡ ዶክተር ሻኪልን "በሁለት ደቂቃ ውስጥ" እንደሚያስፈቱ ቃል ገብተው ነበር፤ ነገር ግን የገቡት ቃል እውን አልሆነም።

የአሜሪካ የባህር ኃይል ወደ ሥፍራው በመግባት በመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት ላይ ዋና ተዋናይ የሆኑትን ቢን ላደንን ያለምንም ተግዳሮት ለመግደል ችለዋል።

ይህ መሆኑም በርካታ ጥያቄዎችን ሳይፈጥር አልቀረም። የአገሪቷን ደህንነት የሚያስጠብቀው የፓኪስታን የጦር ኃይል የት ነበር? ቢን ላደን በአገሪቷ ውስጥ ይኖር እንደነበር ያውቁስ ነበር ወይ? የሚል።

ዶክተር ሻኪል አፍሪ ማን ናቸው?

ዶክተር ሻኪል በፓኪስታን ሃይበር ግዛት ታዋቂ የሆኑ የሕክምና ባለሙያ ናቸው። በዚያው ግዛትም የጤና አገልግሎቶች ኃላፊ በመሆን በርካታ በአሜሪካ የሚደገፉ የክትባት ፕሮግራሞችን መርተዋል፤ ተቆጣጥረዋል።

እንደ መንግሥት ተቀጣሪም በአገሪቷ ጦር አፍንጫ ስር ቢን ላደን ይኖርበት ነበር በተባለው በአቦታባድ፣ ጋሪሰን ከተማን ጨምሮ የሄፒታይተስ ቢ የክትባት ፕሮግራም ያካሂዱ ነበር።

በመሆኑም የአሜሪካ የስለላ ድርጅት እቅድ የነበረው በአቦታባድ አካባቢ ከሚኖሩ ህፃናት ከአንዳቸው የደም ናሙና በመውሰድ ከቢን ላደን ጋር ዝምድና እንዳላቸው ማረጋገጥ ነበር።

በዚህም መሠረት የዶክተር ሻኪል የሥራ ባልደረባ ወደ ግቢው በማቅናት የደም ናሙና እንደሰበሰቡ ይነገራል። ይሁን እንጂ ይህ ናሙና አሜሪካ ኢላማዋን ለመምታት ረድቷት ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።

ኻሾግጂ የዓመቱ ምርጥ ሰው ዝርዝር ውስጥ ተካተተ

የቢንላደን የቀድሞ ጠባቂ በጀርመን

ዶክተር ሻኪል በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ግንቦት 23፣ 2011 ኦሳማ ቢንላድን ከተገደሉ ከ20 ቀናት በኋላ በቁጥጥር ሥር ዋሉ። በወቅቱ በአርባዎቹ መጨረሻ የእድሜ ክልል የሚገኙ ጎልማሳ ነበሩ።

በጣም ሥነ ሥርዓት ያለው የአስተዳደግ ዳራ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ዶክተሩ፤ በአውሮፓዊያኑ 1990 ከሃይበር ሜዲካል ኮሌጅ ከመመረቃቸው፣ ቤተሰባቸው እርሳቸው ከታሰሩ በኋላ የታጣቂዎች ጥቃት ይደርስብናል ብለው በመፍራት ተደብቀው እንደሚኖሩ ካለው መረጃ በስተቀር ስለ ግል ሕይወታቸውም በዝርዝር አይታወቅም።

ባለቤታቸው የትምህርት ባለሙያ ሲሆኑ ራሳቸውን ደብቀው ከመኖራቸው በፊት በአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በመሆንም ሠርተዋል። ጥንዶቹ ሁለት ወንድ እና አንድ ሴት ልጆችም አፍርተዋል።

በአውሮፓዊያኑ ጥር 2012 የአሜሪካ ባለሥልጣናት ዶ/ር ሻኪል ለአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ ይሠሩ እንደነበር አምነዋል።

ይሁን እንጂ ዶክተሩ በድርጅቱ ያላቸውን ሚና ምን ያህል ያውቁት እንደነበር ግልፅ አይደለም። ከግድያው ጋር በተያያዘ የኦቦታባድ ኮሚሽን ባደረገው ምርመራ አደረጉ የተባሉትን አስተዋፅኦ በተመለከተ ምንም ያሉት ነገር የለም።

የአገሪቷ የምርመራ ውጤት እንደሚያስረዳውም ዶክተር ሻኪል የድርጊቱ ኢላማ ማን እንደነበር እና እርሳቸው በሲ አይ ኤ እንዴት እንደተመለመሉ አያውቁም።

ታዲያ ጥፋተኛ ስባላቸው ምንድን ነው?

በእርግጥ ዶክተሩ በመጀመሪያ በአውሮፓዊያኑ ግንቦት 2012 በክህደት የተከሰሱ ሲሆን አሁን ላይ የሌለውን 'ላሽካር ኢ እስላም' የተባለ በአገሪቷ እንዳይንቀሳቀስ የታገደ ታጣቂ ቡድንን በገንዘብ በመርዳት ጥፋተኛ ተብለው ታስረው ነበር።

ከዚህ ቡድን ጋር አላቸው በተባለው ግንኙነት የ33 ዓመታት እስር የተበየነባቸው ሲሆን በኋላ ላይ በጠየቁት ይግባኝ እስሩ ወደ 23 ዓመታት ተቀንሶላቸዋል።

ክሱ የተመሠረተባቸው ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ብቻም ሳይሆን ለቡድኑ የህክምና ርዳታ በመስጠት እና እርሳቸው በሚያስተዳድሩት የመንግሥት ሆስፒታል ውስጥ ቡድኑ ስብሰባ እንዲያካሂድ በመፍቀዳቸውም ጭምር ነበር።

ቤተሰቦቻቸው ግን በእሳቸው ላይ የተላለፈውን ውሳኔ አጥብቀው ተቃውመውታል። ጠበቃቸውም ዶክተሩ ለቡድኑ የከፈሉት ገንዘብ ቢኖር በ2008 በእነዚህ ታጣቂዎች ታግተው በነበሩበት ወቅት እንዲለቋቸው 6375 ዶላር [1 ሚሊየን የፓኪስታን ሩፒ] ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

በ2012 ከታሰሩ በኋላ በፓኪስታን የደህንነት ድርጅት ስቃይና እገታ እንደተፈፀመባቸው ዶክተሩ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

ከዚያም ከአንድ ዓመት በኋላ ለሕግ ባለሙያዎቻቸው 'ፍትህ ተነፍጌያለሁ' ሲሉ በእጃቸው የተፃፈ መልእክት ማስተላለፍ ችለው ነበር።

ታዲያ አሜሪካንን በመርዳት ለምን አልተከሰሱም?

ለምን እንደሆነ ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም የቢን ላደን ጉዳይ ግን ለፓኪስታን ትልቅ ኪሳራ ነበር።

ምንም እንኳን የአገሪቷ ባለሥልጣናት ጉዳዩን የሉዓላዊነት ጥሰት አድርገው ቢያዩትም፤ የደህንነት ተቋሙ የአልቃይዳ መሥራችና መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ትልቅ ግንብ ጀርባ፣ በባለ ሦስት ፎቅ ህንፃ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በምስጢር ይኖሩ እንደነበር እንደማያውቁ በአደባባይ ገልፀዋል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ቢንላደን ይኖርበታል የተባለው ግቢ በ2012 ሙሉ በሙሉ ከመፍረሱ በፊት

በዋይት ሃውስ የሽብርተኝነት ተቆጣጣሪ ኃላፊ ጆን ብሬናን "በዚህ ጊዜ ቢን ላድን በፓኪስታን ውስጥ ድጋፍ አልነበራቸውም ማለት አሳማኝ አይደለም" ሲሉ ቢከሱም፤ ኢስላማባድ ግን ክሱን አልተቀበለችውም።

ፓኪስታን ዶ/ር ሻኪልን አሜሪካ ባካሄደችው ዘመቻ ተጫውተውታል በተባለው ሚና መክሰስ የባሰ የአገሪቷን ገፅታ ሊያጠለሽ ይችላል በሚል በይፋ የመሠረተችው ክስ አልነበረም።

ዶክተር ሻኪል በቀጣይ በሚኖራቸው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ክሳቸው ሊቋረጥላቸው አሊያም የእስራቱ ጊዜ ሊጨመርባቸው እንደሚችል አቃቤ ሕግ አሳውቋል።

በሌላ በኩል ባሳለፍነው ዓመት ከፔሻዋር እስር ቤት ወደ ፑንጃብ የተዛወሩት ዶክተሩ፤ ከአልቃይዳ ጋር በተያያዘ በአሜሪካ በእስር ላይ ከሚገኙት ፓኪስታናዊ የነርቭ ሐኪምና የ3 ልጆች እናት ከሆኑት አፊያ ሲዲቂ ጋር የእስረኛ ልውውጥ በማድረግ ሊፈቱ እንደሚችሉ ጭምጭምታ አለ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ