በኢኳዶር የተቃዋሚ ሰልፈኞች ፖሊሶችን አገቱ

በኢኳዶር የተቃዋሚ ሰልፈኞች Image copyright AFP/Getty

በኢኳዶር መንግስትን በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ የሚገኙት ዜጎች ስምንት የፖሊስ አባላትን ማገታቸው ተገለጸ።

በሺዎች የሚቆጠሩት ሰልፈኞች በዋና ከተማዋ ኩዊቶ መድረክ ላይ በመውጣት ሰባት ወንድ ፖሊሶችና አንዲት ሴት ፖሊስን በድንገት ከከበቡ በኋላ ማገታቸው ተገልጿል።

የደቡብ ኮርያ ፖለቲከኞች ለምን ጸጉራቸውን በአደባባይ ይላጫሉ?

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ ትናንት እና ዛሬ

ሰልፈኞቹም መንግስት የተዘፈቀበትን እዳ ይቀንስ፤ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ሌኒን ሞሬኖ ከስልጣናቸው ይልቀቁ የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያሰሙ ነበር። በዚሁ ምክንያት ፕሬዝዳንቱ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሃገሪቱ እንዲታወጅ ያደረጉ ሲሆን ተቃውሞውን ሽሽትም ወደ ሁለተኛ ከተማዋ ጉዋያኩዊል ሄደዋል።

በሰልፈኞችና በፖሊስ ሃይል መካካል በተከሰተ ግጭትም እስካሁን በርካቶች ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

የተቃውሞ ሰልፉ የተጀመረው የኢኳዶር መንግስት ከዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም 'አይኤምኤፍ' ጋር ያደረገው የብድር ስምምነት ተከትሎ በነዳጅ ዋጋ ላይ ያደርገው የነበረውን ድጎማ ማቆሙን ተከትሎ ነው።

በቀጣይ ቀናትም የነዳጅ ዋጋ በእጅጉ በመጨመሩ ዜጎች ይህንኑ በመቃወም ጎዳና ወጥተዋል። በዚህ ሳምንትም ሰልፈኞቹ መንገድ በመዝጋትና የተለያዩ ህንጻዎች ሰብረው በመግባት ከፖሊስ ጋር ሲጋጩ ነበር።

ፖሊስም በምላሹ አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ሰልፈኞቹን ለመቆጣጠር ሞክሯል።

በሰልፈኞች የታገቱት ስምንት ፖሊሶች ወደ አንድ መድረክ በግድ እንዲሄዱ ከተደረጉ በኋላ የጭንቅላት መከላከያ ቆባቸውን፣ ደረትን ከጥይት ለመከላከል የለበሱትንና ወታደራዊ ጫማዎቻቸውን እንዲያወልቁ ተደርገዋል።

ሦስት ሚሊየን ሶሪያውያን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው

በፀጥታ ኃይሎች እንግልት ሲደርስብን ነበር በሚሉት ሰልፈኞች የተያዙት ፖሊሶች እስካሁን ደረሰባቸው የተባለ ምንም አይነት ጉዳት ባይኖርም ጉዳዩ ግን አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ሌኒን ሞሬኖ ከሰልፈኞቹ ጋር ድርድር ለማድረግ እየተዘጋጁ የነበረ ሲሆን የፖሊሶቹ መታገት ግን ነገሮችን እንዳያባብስ ተሰግቷል። ሰልፈኞቹም ቢሆኑ ገና ከዚህ በኋላ በደንብ የተደራጀ ተቃውሞ ለማካሄድ እያሰቡ እንደሆነ እየገለጹ ነው።

ፕሬዝዳንቱ ግን መንግስት በየዓመቱ ለነዳጅ ድጎማ ያወጣው የነበረው 1.3 ቢሊየን ዶላር ከአቅሙ በላይ መሆኑን ተናግረዋል። ይህን ድጋፍ በማቆሙም የኢኳዶር መንግስት 4.2 ቢሊየን ዶላር ለመበደር ያስችለዋል ተብሏል።