17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፡ የእኛ ሠው በዶሃ

ዶሃ

ቀድሞኝ ዶሃ የከተመው የሥራ ባልደረባዬ አንድ መልዕክት ስልኬ ላይ አኖረልኝ። 'ልብስ ይዘህ እንዳትመጣ' የሚል። መጀመሪያ መልዕክቱ ፈገግ አሰኘኝ። የወዳጄ መልዕክት ቀጭን ትዕዛዝ መሆኑ የገባኝ የዶሃን አየር ፀባይ በተመለከተ መረጃዎችን ለማግኘት ወደ ድረ ገፆች ጎራ ባልኩበት ጊዜ ነው።

ሃማድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንኳን እኔ 'ሦስተኛ ዓለም' ከሚሉት ቀጠና የመጣ ይቅርና አሜሪካውያንና እንግሊዛዊያንን በአግራሞት አፍ ያስከፍታል። እንዴት ያን የሚያክል ህንፃ እንደ ቤተ-መቅደስ በመልካም መዓዛ ይታወዳል? ሀሉም ነገር ተብለጨለጨብኝ።

በቤተ መንግሥት ግቢ የተገነባው አንድነት ፓርክ በውስጡ ምን ይዟል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

ዶሃ የገባሁት ጠዋት አንድ ሰዓት ገደማ ነበር። ቪዛና ሌሎቹ ኮተቶቼን አጠናቅቄ ከአየር መንገድ ስወጣ 2 ሰዓት ገደማ ሆኗል። ልክ ከአየር መንገዱ ስወጣ የተቀበለኝ ጥፊ ነው። አዎ ጥፊ! ወበቁ ይጋረፋል። ያስደነግጣል።

"ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው የመጣኸው?" አንድ በደንቡ የለበሰ ሰው ጠየቀኝ። "አዎ!"። "በል ተከተለኝ" . . . ምን አማራጭ አለኝ. . . በፈገግታ የተሞላው ቃጣሪ [የኳታር ዜጋ] ለአንድ ሕንዳዊ አቀበለኝ።

"ጌታዬ፤ ወደ ሆቴል ነው ወደ ስታድዬም?"። ኧረግ 'ጌታዬ'፤ ኧረ ልጅ ዓለም በለኝ ልለው አሰብኩና ከአፌ መለስኩት። የሆቴሌን ስም የነገርኩት ሕንዳዊ ሹፌር ሻንጣዎቼን የመኪናው ሳንዱቅ ውስጥ ጨምሮ ጉዞ ጀመርን።

በበዴሳ ከተማ ታዳጊውን ለመታደግ የሞከሩ 4 ሰዎች የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ሞቱ

ልክ ወደ መኪናዋ ስዘልቅ የተሰማኝ ቅዝቃዜ. . . የሆነ ነገር አንቆኝ ስታገል ቆይቼ በስተመጨረሻ የተገላገልኩ ያክል ተሰማኝ። የዶሃ መለያዋ ምንድነው? ቢሉ ሰው ሰራሽ ማጤዣዋ [ኤሲ] እልዎታለሁ።

ከኤርፖርት ወደ ሆቴል የነበረውን ጉዞ በሕንፃዎች መካከል እየተሹለኮለክን አለፍነው። የሕንፃ ጫካ አይቶ፤ 'ቬጋስ ተንቆጥቁጣ' ሲል ያቀነቀነው ዘፋኝ ዶሃን አላያትም ማለት ነው? እያልኩ ወደ ማረፊያዬ ደረስኩ።

ኤሲ፣ ኤሲ፣ ኤሲ. . . ኑሮ በዶሃ በኤሲ የተቃኘ ነው። ወደ መኪና ሲገቡ ኤሲ፤ ወደ መገበያያ ሥፍራ ሲገቡ ኤሲ. . . ሌላው ቀርቶ 50 ሺህ ውጦ አላየሁም የሚለው ኻሊፋ ዓለም አቀፍ ስታድዬም ኤሲ ተገጥሞለታል። ለ50 ሺህ ሰው አየር ማቀዝቀዣ!

የዶሃ ሰው

የምዕራብ እስያዊቷ ሃገር ኳታር የሕዝብ ቁጥር 2.8 ሚሊዮን ይገመታል። ከዚህ ውስጥ አረብ ወይም ቃጣሪ ተብለው የሚጡት የአገሪቱ ዜጎች 15 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ሲነገር፤ የተቀሩቱ ከሌሎች አገራት የመጡ ዜጎች ናቸው።

የሕንድ፣ ኔፓል፣ እና ፊሊፒንስ ዜጎች ኳታርን ሞልተዋታል። በንጉሳዊ አገዛዝ የምትተዳደረው ኳታር በዓለም ሦስተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያለባት አገር ነች። የዜጎቿ የነብስ ወከፍ ገቢም በዓለም አሉ ከሚባሉት የሚመደብ ነው።

ዶሃ ውስጥ ያለ ፓስፖርት ወይም ሕጋዊ ማስረጃ መንቀሳቀስ ቀላል አይደለም። ይህንን ስል በየመንገዱ ፖሊስ እያስቆመ 'ፓስፖርት ወዲህ በል' ይላል ማለቴ አይደለም። ዶሃ የመጀመሪያ ተግባሬ የነበረው ሲም ካርድ ማውጣት ነበር።

ወደ አንዱ የቴሌኮም ድርጅት ሄጄ ሲም ካርድ ፈልጌ ነው አመጣጤ ማለት፤ 'ፓስፖርት እባክዎን ጌታዬ'፤ ኧረ ልጅ ዓለም ይበቃል. . .አሁንም በውስጤ። ሰውዬው ፓስፖርቴን ከተቀበለ በኋላ ወደ አነስተኛ ማሽን ሲያስጠጋት ሚስጥሬ ሁሉ ስክሪኑ ላይ ተዘረገፈ። የትውልድ ቀንና ቦታ፤ ለምን ያህል ጊዜ ዶሃ እንደመጣሁ. . .

ስቶርምዚ በካምብሪጅ የጥቁር ተማሪዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋፅኦ አድርጓል ተባለ

ቀጣይ ተግባሬ ደግሞ ዶላር ወደ ኳታሪ ሪያል መመንዘር። እዚህም ያስተናገደኝ ሰው ፓስፖርቴን ለአንድ ማሽን ቢያቀብል ሙሉ መረጃዬ ተዘረገፈ። አንድ ዶላር በ3 ሪያል ሂሳብ መንዝሬ ሳበቃ የዶሃ መንግሥት እንዴት የዜጎቹን ሚስጥር እንደሚቆጣጠር እየገረመኝ ሹልክ አልኩ።

'ሕጉን ካከበርክ. . .'

ዶሃ ውስጥ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ጥያቄ ይወዳሉ። በተለይ ሕንዶችና እና ኔፓሎች። ጋዜጠኛ እኔ ሳልሆን እነሱ ነበር የሚመስሉት። ታዲያ ጨዋታቸው ደስ ይላል። 'ከየት ነው የመጣኸው?' የሁሉም ጥያቄ ነች። ከዚህ ነው የመጣሁት፣ አመጣጤ ደግሞ ለዚህ ነው. . . እኔም መልሴን አዘጋጅቼ መጠባበቅ ያዝኩ። ከሆቴል ወደ ስታድዬም መሄድ ነበረብኝና 'ኡበሬን' መዥረጥ አድርጌ ታክሲ ብጠራ ፀጋይ ከች።

የአገር ሰው መቼም የሃገር ነው ብዬ ተንገብግቤ ነበር ፀጋይ 'ሰላም ነህ ወንድሜ?' ስል እጄን የሰጡት። ፀጋይ አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋው እንደሆነ ቢያሳብቅም አቀላጥፎ ይናገራል። ፀጋይ ኤርትራዊ ነው። ዶሃ ከከተመ በርካታ ዓመታት ሆነውታል። ባለቤቱና ልጆቹ ኑሯቸው አስመራ ነው። በዓመትም ይሁን በሁለት እየተመላለሰ እንደሚጎበኛቸው አጫወተኝ።

ታድያ ኑሮ በዶሃ እንዴት ነው?፤ "ይገርምሃል እኔ ዶሃን በደንብ ነው የማውቃት። መቼም ቃጣሪዎች በቁጥር ትንሽ እንደሆኑ ታውቃለህ። ግን ገንዘቡ ያለው በእነርሱ እጅ ነው። እዚህ አገር የማታገኘው ዓይነት የውጭ ዜጋ የለም። ከአፍሪቃ እና እስያ ሃገራት የሚመጡት ተውና ከአሜሪካ እና ከአውሮጳ ሳይቀር እዚህ መጥተው የሚሠሩ ብዙ ናቸው።"

የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የተዘረፈው ዘውድ ይመለስልኝ እያለች ነው

ፀጋይ የማይጠገብ ጨዋታውን እየመገበኝ ስታድየም ደረስን። ስልክ ተለዋውጠን ተለያየን። ከዚያ ቀን በኋላ ወደ ምፈልገበት ቦታ ሲያደርሰኝ የነበረው ፀጋይ ነበር። ጨዋታው የሚጠገብ አይደለም። ስለ ዶሃ ብዙ አጫወተኝ። አንገቴን እስኪያመኝ ቀና ብዬ የማያቸው መጨረሻ የሌላቸው ሕንፃዎችን ከነስማቸው እየዘረዘረልኝ ጉዞዬን አሰመረው።

"እዚያ ጋር ይታይሃል? ፎቶ እና ቪድዬ ማንሳት ክልክል ነው የሚል የተለጠፈበት አጥር?"። ወደ ጠቆመኝ ቦታ እየተመለከትኩ ጭንቅላቴን በአዎንታ ወዘወዝኩ። "የአልጃዚራ ዋና መሥሪያ ቤት ነው። ገና ምኑን አይተህ፤ መጨረሻ የለውም።" እውነትም መጨረሻ የለውም።

በዶሃ ቆይታዬ ፖሊስ ያየሁት ስታድየም ዙሪያ ብቻ ነው። ዶሃ ተፈልጎ የማይገኘው ሌላው የትራፊክ አደባባይ ነው፤ አዎ! አደባባይ። ብዙዎቹ መንገዶቹ ማሳለጫቸው መስቀለኛ ነው። በአቅጣጫ ጠቋሚ የትራፊክ መብራቶች ተሞልተዋል። ታዲያ፤ መሽቷል፣ አልያም ትራፊክ የለም በሚል ተልካሻ ምክንያት መብራት መጣስ ጣትን ወደ እሳት እንደመስደድ ነው።

አንድ ጋናዊ ሹፌር እንደነገረኝ የትራፊክ መብራት መጣስ እስከ 6000 የቃጣር ሪያል ያስቀጣል። ወደ 59 ሺህ ብር ገደማ ማለት ነው። ተሽከርካሪዎች ጥፋት መፈፀም አለመፈፀማቸውን መርምረው የሚያሳብቁ ካሜራዎች በየቦታው ተተክለዋል። "እያየህ ግባበት ነው" ያለው ፀጋይ ወዶ አይደለም።

ግብጽ በአባይ ላይ ያለኝን መብት ለመከላከል ኃይሉም ቁርጠኝነቱም አለኝ አለች

ፀጋይም ሆነ ሌሎች ያጋጠሙኝ አሽከርካሪዎች እንዲሁም የዶሃ ነዋሪዎች በአንድ ጉዳይ ይስማማሉ። ዶሃ ለኑሮና ሥራ ምቹ ናት። ዋናው ነገር ሕጉን ማክበር ነው። ሕግ ጥሰው የተገኙ እንደሆነ የፀጥታ ሰዎች ካሉበት መጥተው ነው የሚለቅምዎት ሲሉ ብዙዎች ያስረዱኝ።

የሃበሻ ኑሮ በዶሃ

ዶሃ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን እንዳሉ ፀጋይ አጫውቶኛል። እኔም ወዲያ ወዲህ ስቅበዘበዝ ያገኘኋቸው እና ለሰላምታ የተጠመጠምኩባቸው የዶሃ ምድር ይቁጠራቸው። ኳታር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 25 ሺህ ይገመታል።

ይህም የጠቅላላው ሕዝብ ቁጥሩን 0.8 በመቶ ድርሻ ይይዛል። በቤት ሠራተኝነት የተሰማሩ፣ አሽከርካሪዎች፣ የጥበቃ ሠራተኞች. . . እንዲሁም ሌሎች የሥራ መስኮች ኢትዮጵያውያን ተሠማርተው ኑሯቸውን የሚገፉባቸው መስኮች ናቸው።

ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን 'ፕሮፌሽናል' ተብለው የሚጠሩ የሥራ መስኮችም ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ። እርግጥ ነው የአትሌቲክስ ቡድናቸውን ለመደገፍ ኻሊፋ ስታድየም የተገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በርካታ ነበር። በባንዲራ ጉዳይ ጎራ ከፍለው ቢቀመጡም። ምን ያህል ኤርትራውያን ኳታርን መጠለያቸው እንዳደረጉ ግን ውል ያለው መረጃ የለም። ፀጋይ፤ ቢበዛ 5 ሺህ ገደማ ብንሆን ነው ሲል አጫውቶኛል።

"ምን ተይዞ ምርጫ?" እና "ምንም ይሁን ምን ምርጫው ይካሄድ" ተቃዋሚዎች

እንደው አንድ ቀን የቡና ጥም ከዶሃ ሙቀት ጋር ተቀላቅሎ ቢያንገላታኝ ስታርባክስ የተሰኘ ቡና መሸጫ ሱቅ ገባሁ። ታዲያ ከፊት ለፊት የተቀበለኝ ኢትዮጵያ የሚል ስም ደረቱ ላይ የለጠፈ የታሸገ ቡና ነው። ጀበናችንም ከረጢቱ ላይ ተስላ ትታየኛለች። ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ኮለምቢያ አለች። በገዛ ቡናችን እንደባይተዋር ተሰልፌ ተራዬ ሲደርስ ሸምቼ ወንበሬን ስቤ ተቀመጥኩ።

አንድ 'ሱፐርማርኬት' ገብቼ ቡናዎች ከተደረደሩበት ሥፋራ ባቀናም የኢትዮጵያ ስም የተለጠፈበት አንድ እሽግ አይቻለሁ። የሚደንቀው ነገር የኢትዮጵያን ስም እንደ ታርጋ የሚጠቀሙት እኒህ እሽግ ቡናዎች ዋጋቸው ከሌሎቹ ወደድ ያለ መሆኑ ነው።

ኳታር 2022

ምናልባት እኔ ነገሮች ተመቻችተውልኝ ስለጎበኘኋት ይሆን? ብቻ ዶሃ አትጠገብም። ጊዜ ቢያጥረኝ እንጂ ከእግር እስከ ራሷ ብጎበኛት ደስታዬ ወደር አልነበረውም። በቻልኩት መጠን ግን በርካታ ሥፍራዎችን ሲቻል ወደ ውስጥ ዘልቄ ሳይሆን ሲቀር ከቅርብ ርቀት ማየት ችያለሁ።

የዶሃ ቅርሶች አብዛኛዎች ሰው ሰራሽ ናቸው። ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች፣ የሕንድ ውቅያኖስ ላይ የተንሳፈፉ ሆቴሎች፣ ሌላው ቀርቶ ሰው ሰራሽ ደሴቶችና ጫካዎች የከበቧት ናት፤ ዶሃ።

በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ረቂቅ ጥፋተኛና አቃቤ ህግ ይደራደራሉ

ቃጣሪዎች ዶሃ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ማሳያዎች ብዙዎች ናቸው። ከብዙ ሃገራት ተቃውሞ ቢገጥመውም የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበራት ፌዴሬሽን የዘንድሮውን ውድድር ከማምጣት አልተቆጠበም።

በገንዘብ ገዙት እንጂ እንዴት በዚህ በረሃ ላይ የሩጫ ውድድር ይካሄዳል እያሉ ሃሜት እና ምሬት ሲያሰሙ ያደመጥኳቸው አሉ። ነገር ግን ኳታር ዝግጅቱን በድል ጀምራ በድል አጠናቃዋለች።

የመጀመሪያዎቹ ቀናት የተመልካች ድርቅ መቶት የነበረው ግዙፉ ስታድየማቸው እያደር ደምቆላቸዋል። አሁን ሁሉም 2022ን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን። 'ገንዘብ ካለ. . . 'የሚለውን አባባል እውን ያደረጉት ቃጣሪዎች የሚሳናቸው ያለ አይመስልም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ