አሜሪካ በቱርክ ላይ ማዕቀብ ልትጥል እየተሰናዳች ነው

ቱርክ የአየርና የምድር ጥቃት ከከፈተችባቸው ከተሞች አንዱ በርቀት Image copyright AFP

ቱርክ በሶሪያ በኩርዶች ይዞታ ሥር የሚገኙ አካባቢዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟን እንድታስቆም አሜሪካ ላይ ጫና እየበረታባት ነው።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ፀኃፊ ማርክ ኤስፐር "ጠበቅ ያለ ርምጃ" ሊወሰድ እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ፤ የገንዘብ ሚኒስትሩ ፀኃፊ ስቴቨን ሙንቺን በበኩላቸው አዲስ ማዕቀብ ሊጣል የሚችልበትን ዕድል ተናግረዋል።

መከላከያ ሚኒስትር ፀኃፊው አክለውም ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን " መዘዙ ብዙ የሆነ ርምጃ" እንደወሰዱ በመናገር ድርጊቱ " የአይ ኤስ ወታደሮች ታስረውበት ያለውን ሥፍራ አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ቱርክ ከሶሪያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ በፈፀመችው ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

አሜሪካ ቱርክ ሶሪያ ላይ ጥቃት እንድትፈፅም ይኹንታዋን እንዳልሰጠች ገለፀች

ግብጽ በአባይ ላይ ያለኝን መብት ለመከላከል ኃይሉም ቁርጠኝነቱም አለኝ አለች

የገንዘብ ሚኒስትሩ በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቱርክ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ረቂቅ እንዲዘጋጅ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

"ከፈለግን የቱርክን ኢኮኖሚ ቀጥ እናደርገዋለን" ሲሉ አክለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ቱርኮች የሰው ሕይወት እንዲቀጥፉ አንፈልግም፤ ማዕቀብ መጣል ካለብን እናደርገዋለን" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዲሞክራቶችና ሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎቹ በጋራ ተቀምጠው ቱርክ ላይ ጫና የሚደረግበትን ጉዳይ እየተነጋገሩ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦራቸውን ከሥፍራው ለማውጣት መወሰናቸው ቱርክ ወታደሮቿን ወደ ሥፍራው አሰማርታ ጥቃት እንድትከፍት እድሉን ሰጥቷታል ሲሉ የሚከስሱ አሜሪካውያን ቁጥርም ቀላል አይደለም።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ግን ወታደራዊ ዘመቻው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

እንደተባበሩት መንግሥታት ከሆነ የቱርክ ጦር ጥቃት ከከፈተበት ረቡዕ እለት ጀምሮ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሸሽተዋል።

በአካባቢው እየደረሰ ያለው ቀውስ እየበረታ በሄደበት በአሁን ሰዓት የአሜሪካ ጦር የቱርክ ጦር ጥቃት እንዳሳሰበው መናገር ጀምሯል።

አርብ ዕለት ፔንታጎን እንዳለው በሰሜናዊ ሶሪያ አቅራቢያ በሚገኝ የጦር ካምፑ አቅራቢያ ከቱርክ የተተኮሰ መሣሪያ ወድቋል።

የባህር ኃይሉ ካፒቴን ብሩክ ዴዋልት እንዳሉት ደግሞ አካባቢው "የአሜሪካ ጦር እንዳለበት ይታወቃል።"

ካፒቴኑ"ሁሉም የአሜሪካ ጦር ባልደረቦች ላይ ጉዳት አለመድረሱን አረጋግጠናል" ብለዋል በመግለጫቸው ላይ፤ "አሜሪካ ከቱርክ የምትፈልገው ወዲያውኑ ራሳችንን ወደ መከላከል የምንገባበት ነገር እንዳይከሰት ነው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ቱርክ ግን ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም ስትል አስተባብላለች።

በኩርዶች የሚመራው የሶሪያ ዲሞክራሲያው ኃይል ጦር በቀጠናው የአሜሪካ ዋነኛ አጋር ነበር። አሁን ግን ከቱርክ ምድር ጦርና አየር ኃይል ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል።

ቱርክና ሶሪያ በሚጋሩት 120 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው ድንበር ላይ ጥቃቱ እንደተከፈተ ማወቅ ተችሏል።

በርካታ የሶሪያ ዲሞክራሲያው ኃይል ጦር እና የሌሎች አማፂያን ጦር ታጣቂዎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ቱርክ ላይ የሚጣለው ማዕቀብ ባለሥልጣናቷ ላይ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን ይህንን ጥቃት ይደግፋሉ የሚባሉ ባንኮችም እጣው ሊደርሳቸው እንደሚችል የዲሞክራቶችና የሪፐብሊካን ተወካዮች ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በበኩላቸው "ከግራም ከቀኝም ይህንን ጉዳይ አቁሙ የሚል ማስፈራሪያ እየደረሰን ነው" በማለት " ነገር ግን ከአቋማችን ፈቀቅ አንልም" ብለዋል።