ከባህር ዳር - አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ተከፈተ

ከባህር ዳር - አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ተከፈተ Image copyright Veronique DURRUTY

ከባህር ዳር አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ዓርብ መስከረም 30፣ 2012 ከረፋድ 5ሰዓት ጀምሮ ጎሃ ፅዮን ላይ ተዘግቶ የቆየ ሲሆን ትናንት ቅዳሜ አመሻሽ 12 ላይ መከፈቱን የአካባቢው ባለስልጣናት እና መንገደኞች ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የደጀን ወረዳ አስተዳዳርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ካሳሁን አስፋው ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ "ቀድሞውኑ መንገዱ የተዘጋበት ምክንያት አግባብ አልነበረም። ለመንገዱ መዘጋትም ሆነ መከፈት የተነገረን ምክንያት የለም" ይላሉ።

"ኦሮሚያ ላይ ያሉ ሰዎች ጋር ስንደውል መንገዱ አልተዘጋም ክፍት ነው ይሉናል፤ መኪኖችን ስንልክ ደግሞ ተመልሰው ይመጣሉ" በማለት አቶ ካሳሁን የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ከባህር ዳር - አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ዛሬም አልተከፈተም

ነገ በአዲስ አበባ የሚደረግ ሠልፍም ሆነ ስብሰባ የለም-የአዲስ አበባ ፖሊስ

ከጎንደር ተነስታ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘች ያለችው ትዕግስት ደሴ፤ መንገዱ ተከፍቶ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ እያደረገች እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ትዕግስት ትናንት ቅዳሜ ለቢቢሲ ስትናገር አርብ ዕለት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢው አካባቢ መንገድ ተዘግቶ እንደነበረ እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ተደርድረው እንደተመለከተች ገልጻ ነበር።

"ዛሬ ጠዋት [እሁድ] ከደጀን ተነስተን ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እያደረግን ነው። አሁን ፍቼ አካባቢ ደርሰናል" በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ከትናንት ወዲያ [አርብ] ነው እዚህ የደረስኩት። ከዚያ ወደ ደጀን ተመልሰን። ዛሬ ነው እንግዲህ መንገድ ተከፍቶ ጉዞ የጀመርነው" በማለት ለሶስት ቀናት በመንገድ ላይ መጉላሏቷን ታስረዳለች።

አብረዋት ያሉት አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎቹ ተማሪዎች እንደሆኑ የምትናገረው ትዕግስት፤ ትናንት ወደ ደጀን ከተማ ተመልሰው ለማደር እንደተገደዱ ትናገራለች።

ደጀን ከተማ ተመላሽ ተሳፋሪዎችን በሙሉ የሚያስተናግዱ ሆቴሎች ባለመኖራቸው አብዛኛው ሰው በቤተክርስቲያን፣ በሰው ቤት እና ደጅ ላይ ተጠልለው እንዳደሩ ትገልጻለች።

"አንድ ግዜ ከመኪና ወርደን ተፈትሸናል። መንገዱ ሰላም ነው" በማለት ዛሬ ላይ ያለውን ሁኔታ ታስረዳለች።

ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች ተዘግተዋል?

የደጀን ወረዳ አስተዳዳርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ካሳሁን መንገዱ ክፍት የሆነው ትናንት አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ነው ይላሉ።

"አባይ በረሃ ላይ ብዙ መኪኖች በአንድ ጊዜ መተላለፍ ስለማይችሉ ቅድሚያ አባይ በረሃ ውስጥ ቆመው ለነበሩ መኪኖች ቅድሚያ በመስጠት የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ቀርፈናል" ይላሉ።

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ለማ ሆርዶፋ ግን ቀድሞውንም ቢሆን መንገዱ አልተዘጋም ይላሉ።

አቶ ለማ ትናንት ቅዳሜ መኪኖች በሰላማዊ መልኩ እያለፉ እንደሆነ ነው መረጃው ያለኝ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ዛሬ እሁድ ጠዋትም ''መንገዱ ቀድሞም አልተዘጋም፤ ይኸው አሁን ፍቼ ከተማ ነው ያለሁት መኪኖች እያለፉ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች