የባላደራ ምክር ቤት ሰልፉን ለመሰረዝ መገደዱን ገለፀ

እስክንድር ነጋ

በአዲስ አበባ የባላደራ ምክር ቤት ለጥቅምት 2 ይዞት የነበረው ህዝባዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ጋር በተያያዘ አባላቶቻቸው መታሰራቸውን የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ ገልጿል።

በትናንትናው ዕለት ለሰላማዊ ሰልፉ ቅስቀሳ በወጡበት ወቅት "ሁከት ፈጥራችኋል" በሚል በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አንዱ መሆኑን በባላደራ ምክር ቤት የጉለሌ አስተባባሪ እንዲሁም የሰልፉ አስተባባሪ የሆነው ናትናኤል ያለም ዘውድ ነው።

ነገ በአዲስ አበባ የሚደረግ ሠልፍም ሆነ ስብሰባ የለም-የአዲስ አበባ ፖሊስ

"የለውጥ አመራሩን ሳይረፍድ ከጥፋት መመለስ ይቻላል" እስክንድር ነጋ

ናትናኤል በቁጥጥር ስር የዋለው በትናንትናው ዕለት ጥዋት አራት ሰዓት ላይ ፒያሳ አካባቢ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲሁም ከተለያዩ ስፍራዎች ተወስደው ለእስር እንደታደረጉ ናትናኤል ያስረዳል።

በተያዙበትም ወቅት እንደሚፈለጉና "ሕገ-ወጥ ቅስቀሳዎችን" እያደረጉ መሆናቸውንና ኃላፊውን ማናገር አለባችሁ ብለው ቢወስዷቸውም ስልካቸውን እንደቀሟቸው ይናገራል።

"ሕጋዊ ሰልፍ ነው፤ መንግሥት እውቅና የሰጠው ሰልፍ ነው" ቢሉም ተሰሚነትን እንዳላገኙና "ከላይ ትእዛዝም እስኪመጣ ጠብቁ" መባላቸውን አስረድቷል።

ናትናኤል የሰልፉ አስተባባሪ በመሆኑ ለብቻው ተለይቶ እንደተጠየቀና "አዲስ አበባ ፖሊስ ሰልፉን ከልክሎታል፤ ቅስቀሳ ማድረግ አትችልም መባሉን" ያስረዳል።

አክሎም አንደኛው መርማሪ "ለአንተ ደህንነት ነው ያሰርንህ፤ ከተለያዩ ቦታ የመጡ ሰዎች በናንተ ሰልፍ መጥራት ተናደው ጉዳት ሊያደርሱባችሁ ስላሰቡ ለእናንተ ደህንነት ነው" እንዳሏቸው ገልፆ "መረጃው ካላችሁና ጉዳት ሊያደርሱ የመጡ ሰዎችን ማሰር አይቀልም ወይ" ብሎ ምላሽ መስጠቱን አስረድቷል።

ከባህር ዳር - አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ዛሬም አልተከፈተም

የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የተዘረፈው ዘውድ ይመለስልኝ እያለች ነው

አመሻሽ አራት ሰዓት ላይም "ሰልፍ የሚባል ነገር አለመኖሩንና አርፈው እንዲቀመጡ" ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውን ለቢቢሲ ገልጿል።

እሱ ታስሮበት በነበረው ጣይቱ ሆቴል አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ወደ ሃያ የሚቆጠሩ ግለሰቦች የነበሩ ሲሆን ጃንሜዳ፣ ፈረንሳይ እና መርካቶ ባሉት ፖሊስ ጣቢያዎች በቁጥር የማያውቃቸው ብዙ አባላቶቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ መሆኑንም አስረድቷል።

ናትናኤልን ጨምሮ አብዛኛዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ትናንት ወደ አመሻሹ መፈታታቸውን ጨምሮ ለቢቢቢሲ አስረድቷል።

የባላደራ ምክር ቤቱ ህዝባዊ ሰልፉን ለመሰረዝ መገደዱንም ገልጿል። እስክንድር ነጋ በትናንትናው እለት በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው ፖሊስ ባደረገው ክልከላ የተቃውሞ ሰልፉን መሰረዙን አስፍሯል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ የተፈቀደም ሰልፍ ይሁን በሰልፉ የሚዘጉ መንገዶች የሉም የሚለውን ክልከላ ተከትሎም ምክር ቤቱ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ "ለሃገሪቱ ሰላምና ለህዝቧ ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ሰልፉን ሰርዟል" ብሏል።

የባላደራው ምክር ቤት ከጥቂት ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ህጋዊ መስፈርቶችን አሟልተው ለአዲስ አበባ መስተዳድር ጥያቄ ማቅረባቸውንና መከልከሉም መፈቀዱም እንዳልተገለፀላቸው ተናግረው የነበሩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ ነገር ግን ሕጉ እንደተፈቀደ ለማሳወቅ አያስገድድም በማለት "ዝም በማለታቸው እንደተፈቀደልን ይቆጠራል" ብለው ነበር።

ህዝባዊ ሰልፉ የተጠራው "ተስፋ የተጣለበት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጅምር በመቀልበሱ ነው" ሲሉም በመግለጫቸው አስታውቀው ነበር።

ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ ነገሮች እንዲስተካከሉ ድምፃቸውን ማሰማታቸውን፤ ነገር ግን ሰሚ በማጣታቸው ሁለተኛውን የሰላማዊ ትግል ስልት ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልፀው ነበር።

በዚህም መፍትሄ ካላገኙ በቀጣይ መንግሥትን ወደሚያስገድዱ የሥራ ማቆም እና ሌሎች የትግል ስልቶች ለመግባት እንደሚገደዱም በመግለጫቸው ላይ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

እስሩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፋንታ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

ተያያዥ ርዕሶች