የመደፈሬን ታሪክ ከስልሳ ሰባት ዓመታት በኋላ የተናገርኩበት ምክንያት

የህፃናት መደፈር

ታዋቂዋ ጋናዊት ጋዜጠኛና፣ የቀድሞ ሚኒስትር እንዲሁም በተለያየ ጊዜ ለቢቢሲ ትፅፍ የነበረችው ኤልዛቤት ኦሄኔ በቅርቡ ከስልሳ ሰባት ዓመታት በፊት የደረሰባትን የተገዶ መደፈር ጥቃት ይፋ አድርጋለች።

ኤልዛቤት ጥቃቱ ሲፈጸምባት የሰባት ዓመት ልጅ የነበረች ሲሆን፤ ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላም ጥቃቱን ለህዝብ ለማሳወቅ የወሰነችበትን ጉዳይ በአንደበቷ እንደሚከተለው ትናገራለች።

የደረሰብኝን የመደፈር ጥቃት ይፋ ባደርግ ምን ያስከትል እንደነበር ብዙም አላሰብኩበትም።

የተነጠቀ ልጅነት

"በወንድሜ ለአምስት ዓመታት ተደፍሬአለሁ"

ባለፈው ረቡዕ ነው በጋና ውስጥ ከፍተኛ ስርጭት ላለውና እኔም በየሳምንቱ በምፅፍበት ደይሊ ግራፊክ ታሪኬን አጋራሁኝ።

የሰባ አራት አመት የዕድሜ ባለፀጋ ነኝ፤ ወደ ኋላ ስልሳ ሰባት ዓመታትን በትዝታ ተጉዤ ነው የሆነውን የምናገረው፤

አንድ የቅርብ ወንድ ጓደኛዬ ለምን በታሪኬ ሸክምን እንደፈጠርኩባቸው ጠየቀኝ። ታሪኩ እንደተነገረኝ ከሆነ ለማንበብ ከባድ ነው። ለስልሳ ሰባት አመታትም ለራሴ ደብቄው ኖሬያለሁ፤ ለምን አሁን መናገር መረጥኩ? ሚስጥሬን ለምን አብሬው አልተቀበርኩም?

መጀመሪያ ምናልባት ታሪኬን ልናገርና ለምን እንዳጋራሁ እገልፃለሁ።

ጊዜው በጎርጎሳውያኑ 1952 ነው፤ ገና የሰባት ዓመት ታዳጊ፤ ደስተኛ ልጅ ነበርኩ። ከአያቴም ጋር በመንደራችን እንኖር ነበር። አንድ ቀን ቤተሰባችን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውና ጎረቤታችን የሆነ ግለሰብ ጎትቶ ቤቱ አስገባኝና ጥቃት አደረሰብኝ።

ምን እንደደረሰብኝ ለመናገር ቃላት ያጥሩኛል። በወቅቱ ሰውየው ምን እንዳደረገኝ አላወቅኩም፤ ይህ ነው ብባልም ስሙንም መጥራት አልችልም ነበር። ጥቃት የደረሰበትንም አካሌንም በትክክል ስም አላውቅም ነበር።

የማውቀው ነገር ቢኖር እጁ ሸካራና ጥፍሩን አስታውሳለሁ፤ ብልቴም ውስጥ ጣቱን ሲያስገባ ጥፍሩ መሰበሩን ትዝ ይለኛል።

ምን እንዳለ አላስታውስም፤ ከባድ ሰውነቱ ሲጫነኝ፤ የሰውነቱ ሽታ ሲሰነፍጠኝ፤ ሸካራ ጣቶቹና የተሰበሩ ጥፍሮቹ ለስልሳ ሰባት አመታት ያህል ትናንት የተፈጠረ ይመስል አእምሮየን በሚጠዘጥዝ መልኩ አስታውሰዋለሁ።

ፆታዊ ትንኮሳን ደርሶብኛል በማለቷ ተቃጥላ እንድትሞት የተደረገችው ወጣት

ዛሬ ምን እንደተፈፀመብኝ አውቃለሁ። አንድ የሚመረኝ ቢኖር ያለው የማህበረሰቡ እሴት የደረሰብኝን ነገር በዝርዝር እንዳወራ አይፈቅድልኝም፤ ተደፈርኩ ወይም ጥቃት ደረሰብኝ በሚል በደፈናው እንድናገር ነው የሚፈለገው።

አያቴ በምትችለው መጠን ተንከባክባኛለች፤ አካላዊ እንክብካቤ። ምን እንደተፈጠረ አልነገርኳትም። በተደፈርኩ በነገታው ገላየን እያጠበችኝ እያለ ከብልቴ ፈሳሽ ሲወጣ አየች፤ ኢንፌክሽንም ፈጥሮ ነበር።

ምን እንደተፈጠረ አልጠየቀችኝም፤ ዝም ብላ ተንከባከበችኝ። የምትወዳት የልጅ ልጇ ላይ እንዲህ አይነት ነገር ይፈጠራል ብላም አላሰበችም።

ልጅነቴን ሌላ የቀማኝ ነገር የተፈጠረው በአስራ አንድ አመቴ ነው፤ ያው ሰው ደፈረኝ።

በዚህም ወቅት ምን እንደተፈጠረ በትክክል ባይገባኝም፤ በህይወቴ የማይሽር ጠባሳን ትቶ አልፏል።

በህይወት መቆየት ደግ ነው፤ መደፈሬ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ አድርጎኛል ማለትም አልችልም።

በማህበረሰቡ የተሳካለት አይነት ህይወት ኖሮኛል። ጋዜጠኛ፣ ፀሐፊ እንዲሁም የመንግሥት ባለስልጣን ለመሆን በቅቼያለሁ።

አሁን በዚህ እድሜየ ብሞትም እንግዲህ በጋና ባለው የማህበረሰቡ አስተያየት መቃብሬ ላይ ከፍተኛ ስራ እንዳበረከትኩ ነው የሚፃፍልኝ።

በሌላ ቋንቋ ኑሮየን በደንብ አጣጥሜ የኖርኩ ሰው ነኝ።

እናም ለዛ ነው ብዙዎች አሁን ለምን እንዲህ አይነት አሰቃቂና ቆሻሻ ርዕስ ይዘሽ መጣሽ ያሉኝ፤

በእርግጠኝነት የምናገረው ነገር ቢሆን የሴት ህፃናት መደፈር በማህበረሰቡ ዘንድ በተወሰነ መልኩ ተቀባይነት እንዳለው ልምዴ አሳይቶኛል። በተለይ ትንንሽ ሴት ህፃናት በትልልቅ ወንዶች አደጋ ላይ ናቸው። እንደ ማህበረሰብም በጉዳዩ ላይም ለመነጋገር ፍቃደኛ አይደለንም።

ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት ትንሽ መሻሻሎች ቢኖሩም አንዲት ህፃን ተደፍራ ሪፖርት ያደረገ ሰው በማህበረሰቡ ከፍተኛ ጫና ይደርስበታል፤ ከፖሊስም ክሱን እንዲተውና በቤት ውስጥ ስምምነቶች እንዲደረስ በተደጋጋሚ ጫናዎች ይደረጋሉ።

ደፋሪውን ወደ ፍርድ የሚወስዱ ከቤተሰብ ጋር ለመቆራረጥ የወሰኑ ናቸው፤ ለዛም ነው ችሎት የሚመጡ የመደፈር ጉዳዮች በጣም ጥቂት የሆኑት።

ፍራቻየም ሰባት አመት ኧረ እንዲያውም ሶስት አመት የሆናቸው ህፃናት ሴቶች እኔ ከዘመናት በፊት ባለፍኩበት ስቃይ ውስጥ የሆኑ አሉ።

ቁጣ በደፋሪዎች ሳይሆን በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን

በጥቃት ላይ መነጋገር ካልቻልን ሁኔታዎች አይቀየሩም። እንደ ማህበረሰብ ስለ ወሲባዊ ግንኙነት ለማውራትም ፍቃደኛ አይደለንም፤ በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ጋር በተያያዘ ሁኔታ ብቻ ቁጣችንን ለማሰማት ካልሆነ በሌላ መንገድ ወሲብን አንጠቅሰውም።

Image copyright Getty Images

በጋና ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን አንድ ጥናትም የሚያሳየው 97% የሚሆነው የማህበረሰቡ አካል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን በጋና ውስጥ አሉ ብሎ አያምንም።

ለዛም ነው በጋና ውስጥ ባሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የወሲብ ትምህርት ይሰጥ ሲባል ከባህል የራቀ፣ ፀረ ሃይማኖት፣ ፀረ ጋናና የተመሳሳይ ፆታን በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረፅ የሚደረግ አሻጥር ነው ብለው ብዙዎች የሚያምኑት።

"ለእናንንተ ደህንነት ነው በሚል እንዳሰሩን ተገልፆልናል" የባላደራ ምክር ቤት አስተባባሪ

በቅርቡም ጋና ውስጥ በትምህርት ስርአቱ ውስጥ የወሲብ ትምህርት ይካተት ተብሎ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። ሁኔታውንም ለማቀዝቀዝ ፕሬዚዳንቱም መግለጫ መስጠት ነበረባቸው።

ብዙዎችም የሴቶች መደፈርንም እንደተለመደ ነገር ማየታቸውም ችግሩን ለመቅረፍ አልተቻለም።

በሠርግ ዕለት ማታ በጉጉት የሚጠበቀው 'የደም ሸማ'

አንድም ሰው መርዳት ከቻልኩ ደስተኛ ነኝ

ታሪኬን ከሰሙ ብዙዎች ያገኘሁት ምላሽ ከጠበቅኩት በላይ ነው። ምቾት የሚነሳ ታሪክ ነው፤ ምቾት እንዲነሳም ተደርጎ ነው የተነገረው። ስለዚህ ምቾት ቢነሳቸውም ብዙ አይደንቀኝም።

ብዙዎችም እንደ ጀግና አይተውኛል። ለኔ ግን ይህንን ታሪክ ለመንገር የፈጀብኝ 67 አመታት መሆኑን ነው የማውቀው እናም ስለ ጀግንነቴ አላውቅም።

አንዳንዶች እንዲህ አይነት ታሪክ በይፋ መናገሬ ከቆሻሻነትና ከማዋረድ ጋር ያያዙት አሉ- ለነሱ ምንም አይነት አስተያየት የለኝም።

ብዙ ሴቶች አመስግነውኝ እንዴት ድፍረት እንደሰጣቸውና ከራሳቸውም ታሪክ ጋር ያያዙት አሉ፤ በሱ ተሰምቶኛል።

ታሪኬ ስለ ወሲብ በግልፅ እንድናወራ ካደረገንና ጥቃት የደረሰባቸውንም ህፃናት አቅም የሚፈጥርላቸው ከሆነ በደስታ ወደ መቃብሬ እወርዳለሁ።

ተያያዥ ርዕሶች