የሆሊውዱ ሃኪም ገብረወልድን ያውቁታል?

ሳምባ ሹት Image copyright Rodin Eckenroth

ሃኪም ገብረወልድ ማን ነው? ሆሊውድስ ምን ያደርጋል? ስለ ሃኪም ገብረወልድ ለማወቅ ከቀድሞው የኒውዮርክ ምክር ቤት አባል ጋር ካደረገው ጭውውት እስቲ እንጀምር።

የቀድሞ የኒውዮርክ ምክር ቤት አባል የሆነው ጋሬት ኢትዮጵያዊውን ሃኪም ገብረወልድን የኡበር ታክሲ ሲያሽከረክር አግኝቶት መጀመሪያ የጠየቀው ''ይሄ መቼም ከፍተኛ ለውጥ ነው፤ ከኢትዮጵያ ወደ ኒውዮርክ መምጣት'' አለው።

"ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን ወደ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ ማምጣት ፈታኝ ነው" ዘረሰናይ መሐሪ

ሃኪም፡ አዎ ይሆናል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የማገኘውን ገንዘብ ያህል አላገኝም፤ ግን ይሁን እስቲ።

ጋሬት፡ ቆይ፣ ቆይ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ነበር የምትሰራው?

ሃኪም፡ የልብ ቀዶ ህክምና ሐኪም ነበርኩ፤ እናም ዲቪ ሎተሪ አሸንፌ ነው አሜሪካ የመምጣት እድል ያገኘሁት።

ጋሬት፡ ዶክተር ከሆንክ ታዲያ ለምን ታክሲ ትነዳለህ?

ሃኪም፡ ያው ፈቃድ ማግኘት አልቻልኩም፤ እንግዲህ ወረቀቴን ሳገኝ ይረዳኝ ይሆናል። ቢሆንም ያው ዓመታት መውሰዱ አይቀርም፤

ጋሬት፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ጥሩ ህይወት ነበረህ። ለምን ወደዚህ መጣህ?

ሃኪም፡ ምክንያቱም አሜሪካ ከሁሉም የበለጠች ስለሆነች፤ ሁሉ ነገር የሚቻልባት ስለሆነ፤

ሃኪም፡ ይሄን ያህል ምንድነው ያው ታክሲ ብነዳም፣ ፎርም ብሞላም ጄትስኪየን (በውሃ ላይ የሚነዳ ሞተር) ትቼ ብመጣም ፤ ምንም ማለት አይደለም። አሜሪካን በጣም እወዳታለሁ፤ የዚህችም አገር አካል መሆን እፈልጋለሁ።

ጋሬት [በመደነቅ] እንዴ ጄትስኪ አለህ? እኔም እኮ አለኝ።

ይህ በቅርቡ በአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንቢሲ ለዕይታ ከበቃው ሰኒ ሳይድ የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም ውስጥ ዋነኛ ገፀባህርይ የሆነው ሃኪም ገብረወልድና የቀድሞው የኒውዮርክ የምክር ቤት አባል ጋሬት ሞዲ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው።

ኒውዮርክ ውስጥ መቼቱን ያደረገው ይህ ፊልም በስደተኞች ህይወት ላይ ያጠነጠነ ሲሆን አንደኛው ዋና ገፀባህርይ ኢትዮጵያዊው ሃኪም ገብረወልድ ነው።

ሃኪም ገብረወልድ የተሳለበት መንገድ እስከዛሬ በሆሊውድ ውስጥ ከተሰሩና ኢትዮጵያን ከረሃብና ከችግር ጋር ከሚያይዙ ፊልሞች ለየት እንደሚል በፊልሙ ዘርፍ ካሉ አስተያየት ሰጪዎች እየተሰማ ነው።

በፖለቲካው ዓለም ዝናው እየገነነ የነበረው ጋሬት አሳፋሪ ሥራ በመስራቱ ከምክር ቤት አባልነቱ ይባረራል።

ለህይወቱም ትርጉም ሲፈልግ የአሜሪካ ዜግነታቸውን ለማግኘት የአሜሪካን ፖለቲካ ከስር መስረቱና ህገ መንግሥት የሚያጠኑ ስደተኞች ያገኛል። ከስደተኞቹም አንዱ የህክምና ሙያውን፣ ቅንጡ መኪናውንና ቤቱን ጥሎ አሜሪካ የተሰደደው ሃኪም ገብረወልድ ነው።

ምንም እንኳን ሃኪም ገብረወልድ የቴሌቪዥን ገፀ ባህርይ ቢሆን ሥራቸውን፣ ቤታቸውን ትተው አሜሪካ ወይም አውሮፓ የከተሙ ዶክተሮች፣ መምህራን፣ ጋዜጠኞችን ቤቱ ይቁጠረው። በዚህ ፊልም ላይ ስደተኛውን ዶክተር ወክሎ የሚጫወተው የሞሪሽየስ ዜግነት ያለው ሳምባ ሹት ነው።

ሳምባ ሞሪሽየስ ቢወለድም ከሁለት ዓመቱ ጀምሮ አስራ ስምንት ዓመት እስኪሆነው ድረስ ያደገው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ የተማረውም እንዲሁ።

ኢትዮጵያውያን 'የሌሉበት' ስለ ኢትዮጵያ የሚዘክረው ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት ፊልም

በዚህ ፊልም ላይ ሆሊውድ አፍሪካ ከምትሳልበት የርስ በርስ ጦርነት፣ እልቂት፣ ችግር፣ ሰቆቃ ከተሞላበት የታሪክ ንግርት ወጥተው የተማሩ ስደተኞችም ይመጣሉ፤ ስደተኞችም ሕይወት አላቸው፤ የሚለውን በቀልድ መልኩ እያዋዛ ይነግራል።

የአሜሪካ ህልምንም በተለይም ለስደተኞች ምን ማለት እንደሆነ በነገር ሸንቆጥ በማድረግ ይነግራል። ምንም እንኳን ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎች ስደተኞች የኢኮኖሚ ዋልታ መሆናቸውን ቢያሳይም ከሚከፈላቸው ዝቅተኛ ገንዘብ አንስቶ እስከ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው ይመለሱ የሚሉ ጉዳዮች የብዙ ሃገራት ፖለቲከኞች የፖሊሲ ክርክሮችን የሚያስነሳ ነው።

ለዚያም ነው ሃኪም ገብረወልድ ረዘም ያለ ጭውውት ከተጨዋወተውና የታክሲ አገልግሎት ከሰጠው ግለሰብ፤ 'አመሰግናለሁ' ብሎ ሊወርድ ሲል ይህንን የሚለው "አሜሪካ ታላቅ እንዲሁም ሌላ ሌላ ብትሆንም ዋናው ነገር ለሰሩበት ስትከፍላቸው ነው" የሚለው።

"የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ አልተጠናም" ዶክተር አሰፋ ባልቻ

የስደተኞችን ህይወት የተወሰሳበ መልኩን በማሳየት፤ ገፀ ባህርዮቹ ህይወት እንዲኖራቸው፤ ባህል፣ አለባበስ፣ ፍቅርና ሌሎች መስተጋብሮችንም ማሳየትም እንደቻለ የፊልም ልሂቃን እየመሰከሩለት ነው።

ታዋቂዋ ፀሀፊ ኤድዊጅ ዳንቲካት ሁሉም ስደተኛ አርቲስት (ጥበበኛ) ነው ትላለች። ለዚህም የምታጣቅሰው ስደተኞች ከተፈናቀሉበት አገር መጥተው ህይወታቸውን ከዜሮ ለመጀመር ሳይፈሩ፤ ራሳቸውን ትልቅ ቦታ ላይ አድርሰው፤ ልጆቻቸውን ለትልቅ ቦታ በማብቃት ህይወትን ይመሰርታሉ።

ሃኪም ገብረወልድም ታዋቂ ዶክተር ቢሆንም እሱን ወደ ጎን በመተው ታክሲ እያሽከረከረ የህክምና ፈቃዱን ሲያገኝ ዶክተር እንደሚሆን ያስባል።

በሃኪም ገብረወልድ ታክሲ ውስጥ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አለ። አገሩም ሆነ የህክምና ሙያው በጣም የሚናፍቀው ይመስላል። በስሜትም ስለ ህክምና ሂደት ለማያቀው ሰው ያወራል።

ለዚያም ነው ጋሬት ስለ ሃኪም ገብረወልድ ሲያወራ ይህንን ያለው፡

"ሃኪም ገብረወልድ ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ዶክተር ነበር፤ አንድ ጊዜ እንዳውም መንገድ ላይ በመኪና የተገጨች አይጥ አግኝቶ ደረቷን በመጫን እርዳታ ሲሰጣት ዳነች" በማለትም በግነት ለሙያው ስላለው ፍቅር ምስክርነት የሚሰጠው።

ስደተኛ ጓደኞቹ ባያውቋቸውም የኢትዮጵያን ከተሞች ይጠራል፤ የመቀሌንና አለታ ወንዶን ቤት ኪራይ በማወዳደር ይናገራል።

በአብዛኛው የሆሊውድ ፊልሞች ላይ የሚሳሉት አፍሪካዊያን ምንም የማያውቁ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የሚናገሩት ቃላቶች የተመጠኑ፤ ማንነት የሌላቸው፣ በችግርና እጦት የተደቆሱ፣ እምነትም ሆነ የራሳቸው የዓለም ዕይታ የሌላቸው ተደርገው ነው። ለፊልሙ ማጣፈጫ (ፕሮብስ) ከመሆን በስተቀር ሌላ አላማንም ሲያሟሉና በአብዛኛው ሲያሳኩ አይታይም።

በዚህ ፊልም ለየት ባለ መልኩ ስለ ኢትዮጵያ የሚያውቅ ገፀባህርይ ተካቶበታል። ሃኪም ገብረወልድ መልካም ስብዕና ያለው፤ አዋቂ እንዲሁም የቡድናቸው ማዕከልም እንዲሆን ተደርጎ ገፀባህርዩ ቢሳልም አንዳንድ ጊዜም የ"መሽቁቅነት" ባሕርይ ያሳያል።

እህትህን ወደ አሜሪካ ለማምጣት እረዳሃለሁ ብሎ ያጭበረበረውን ግለሰብ "በአገራችን 'ይቅርታን የሚሰብክ ክፉ ነህ' የሚል ፅንሰ ሃሳብ አለ፤ ዓለማችንም መልካም የምትሆነው ይቅርታ ስናደርግ ነው። እናም ይቅርታ አድርጌልሃለሁ" ይለዋል ግለሰቡ ክፉ ነህ እያለም አልመሰለውም፤ ይቅርታ ያደረገለት መስሎት ነበር። ሳምባ ይህንንም በማለት ከሸወደው በኋላም ድምፁን በመቅዳት ገንዘቡን ያስመልሳል።

በአስራ ስምንት ዓመቱ ወደ አሜሪካ የሄደው ሳምባ ቲያትር ለማጥናት ሲሆን፤ የፊልሙ ታሪክ ከእርሱ ጋር እንደሚመሳሳል በተለያየ ጊዜ ባደረጋቸው ቃለ መጠይቆች ተናግሯል።

"ታሪኩ ከእኔ ታሪክ ጋር ይመሳሰላል፤ ከስምንት ዓመት በፊት አሜሪካ ስመጣ፤ ህልሜንም ለማሳካት መስዋዕትነት ከፍያለሁ፤ በአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣብያም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ኢትዮጵያዊ ገፀ ባህርይ በፊልም (ሲት ኮም) ላይ ሲታይ። ለእኔ ትልቅ ቦታ ያላትን ሃገርና ባህል መወከሌም ትልቅ ኩራት ይሰማኛል" ብሏል።

ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ በሆሊውድ ፊልሞች

አፍሪካ ላይ ያጠነጠኑ የሆሊውድ ፊልሞችን ብናይ አንደኛ አፍሪካ መንደር ተደርጋ የምትሳልበት፤ ረሃብ፣ ችግር፣ ጦርነትና እርስ በርስ መጨፋጨፊያ ጨለማ ቦታ ተደርጋ ነው የምትሳለው፤ የኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ አይደለም።

በአፍሪካ ላይ የሚያጠነጥኑ አንዳንድ ፊልሞችን ወደኋላ ሄደት ብለን ለምሳሌ "queen of the jungle" ብናነሳ ትንቢት የተነገረላትና ወርቃማ ፀጉር ያላት አንዲት ነጭ አፍሪካን ስታድን የሚያሳይ ነው።

የምዕራቡ ዓለም ከአንድ ቢሊዮን ህዝቦች በላይ የሚኖሩባትን አህጉር በተለይም በፀሀፊያን ዘንድ የምትመሰልበትን መንገድ ሽሙጣዊ በሆነ መልኩ በፃፈበት "ሃው ቱ ራይት አባውት አፍሪካ'' (ስለ አፍሪካ እንዴት መፃፍ እንችላለን) በሚለው ፅሁፉ ቢንያቫንጋ ዋይናይና፡

"የመፅሃፋችሁን ሽፋን በየቀኑ የምናገኛቸውን አፍሪካዊያንን ፎቶ ሳይሆን ኤኬ 47 ጠመንጃን የተሸከመ፤ የሽምቅ ውጊያ፣ የተራቆቱ ጡቶች፤ የገጠጡ አጥንቶችን አድርጉ" በማለት ምዕራባዊያን ስለአፍሪካ ሲፅፉ በተደጋጋሚ የሚያወጧቸውን ፎቶዎች በማየት በነገር ሸንቆጥ አድርጓቸዋል።

በረሃብ፣ በችግር፣ በጦርነት፣ በእርስ በርስ ግጭት ብቻ በተሞላችው በሆሊውዷ አፍሪካ ላይ ይህንን ሲቀርፉ የሚታዩትና ሲያድኑ የሚታዩትም ነጭ ሰዎች ናቸው።

ከእነዚህም ውስጥ ብዙዎች የሚጠቅሷቸው "ብለድ ዳይመንድ" ዘረኛ ነጭን ወክሎ የሚጫወተው ቅጥረኛው ነፍሰ ገዳይ ሊዮናርድ ዲካፕሪዮ ጥቁሩን ሴራሊዮናዊና ልጁን ከጥቁር ነፍሰ ገዳዮች ሲያድንም ይታያል። የፊልም ልሂቃን ቆጥረው ከማይዘልቋቸው መካከልም አምስቴድ፣ ቲርስ ኦፍ ዘ ሰን፣ ክራይ ፍሪደምና ሌሎችም ይገኙበታል።

ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገው የተሰሩ ጥቂት የሆሊውድ ፊልሞችን ብናይ ከረሃብና ከድርቅ ጋር የተገናኘ ነው። ከነዚህም ውስጥ 'ቢዮንድ ቦርደርስ' እንዲሁም ታዋቂው ተከታታይ የካርቱን ፊልም 'ሳውዝ ፓርክ' ውስጥ አንደኛውን ክፍል 'ስታርቪንግ ማርቪን (የተራበው ማርቪንን) ማስታወስ ይቻላል።

በዚህ ፊልም ላይ ረሃብን በቴሌቪዥን ሲከታተሉ የነበሩ ታዳጊዎች ታይኮ የስፖርት ሰዓት ሽልማት እናገኛለን በሚል ገንዘብ ቢረዱም በስህተት የተራበ ኢትዮጵያዊ ልጅ ይላክላቸዋል።

የገረጣ፣ የከሰለ ልጁንም በየተራ ለማሳደግ ይወስናሉ። ስሙንም ስታርቪን ማርቪን ብለው ይሰይሙታል፤ ትምህርት ቤትም ይወስዱታል። በኋላም ስህተት መሰራቱ ይታወቅና እንደ እቃ አፍሪካ ለመላክ ይወስናሉ።

በቅርቡ ኔትፍሊክስ ላይ ለዕይታ የበቃው 'ዘ ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት' ኢትዮጵያዊያንን አለማሳተፉ፣ አማርኛ እየተኮላተፉ የሚያወሩበት እንዲሁም የታሪክ ግድፈቶች አሉበት በሚልና የነጭ አዳኝነት (ዋይት ሴቪየር)ን በማቀንቀን ትችቶች ቀርበውበታል።

በዚህም ፊልም ላይ ነጮች ኢትዮጵያዊያንን ማዳን ብቻ ሳይሆን ሱዳን ውስጥ ያለን አንድ ማህበረሰብ የሰው ስጋ እንደሚበሉ የሚነገርበት፤ የፀጥታ ኃይሉ ምንም ርህራሄ የሌለውና (ያልተፈጠረ ታሪክ በመጨመር) ሱዳናዊያን ኢትዮጵያዊያንን ሲጨፈጭፉ የሚያሳየው ዝም ብሎ የሚወሰድ ሳይሆን ለዘመናት የተካኑበት የታሪክ አነጋገር ዘያቸው እንደሆነ ተችዎች ፅፈዋል።

የባርነትን ታሪክ እንደገና ከመፃፍ ጀምሮ፣ ቀደምት አሜሪካዊያንን ሰው በላ አድርጎ መሳል፣ አፍሪካዊያንን ነፃ በማውጣትና በመርዳት ነጮችን የአዳኝነት ታሪክ ስፍራ ሆሊውድ እንደፈጠራላቸው ተችዎች ይተነትናሉ።

ጥቁርም ሆኑ ግሎባል ሳውዝ (ከነጩ ዓለም ውጪ) ታሪክን እንነግራለን የሚሉ ፊልም ሰሪዎችም ዋነኛ ፈተናቸው በተለይም ከበጀት ጋር ተያይዞ፤ የታሪኩን ማዕከል ወይም ዋነኛ ገፀ ባህርዩን ነጮችን (የነጮችን አዳኝነት) ታሪክ እንዲያስገቡ መገደዳቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

በዚህም ኃይሌ ገሪማ አድዋን ለመስራት ከፍተኛ በጀት ጠይቀው በነበረበትም ወቅት የሚኒልክን አማካሪ ነጭ ሰው እንዲያደርግ መጠየቁ እንደ ምሳሌ የሚነሳ ነው። "የእኔ እናት ወይም አያት በፊልሞች ላይ እንድትኖር ለማድረግ አንድ ነጭ ሰው ሊኖር ይገባል" በማለትም በአንድ ወቅት ተናግረዋል።

ምዕራባዊያን ወይም ነጭ የፊልም ጸሀፊዎችና አዘጋጆች ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካን ታሪክ የሚያዩት በራሳቸው መነጽር (ዋይት ጌዝ) ነው ተብለው ይተቻሉ። የአፍሪካዊያን ታሪክ በነጮች ሲፃፍ ወይም ሲዘጋጅ ባህሉን ካለማወቅ በደንብ መንገር አይችሉም ይባላል።

በአንድ ወቅትም የድፍረት ዳይሬክተር ዘረሰናይ መሐሪ ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ይህንን ብሏል

''ለምሳሌ የማልረሳውና ያስደነገጠኝ ትልቅ ነገር አለ። "ድፍረት" ሰን ዳንስ እንዳሸነፈ ስርጭት እየተስማማን እያለ አንድ ጣልያናዊት አሰራጭ በጣም ፊልሙን ስለወደደችው ተደራደረች። ፊልሙን በዓለም ለማሳየትም የ "ወርልድ ዋይድ ራይትስ'' መብቱንም መውሰድ ፈለገች። ድርጅቷ ያለው ጣልያን ቢሆንም ጣልያን ሀገር ማሳየት አልፈለገችም። ለምን? ስላት፣ ፊልሙ ውስጥ ምንም ነጭ ገፀባህርይ ስለሌለ ፊልሙን ጣልያን ሀገር ለማሳየትና ለመሸጥ በጣም ይከብዳል አለች።

ያላቸው አስተሳሰብ ወይም አንድን ነገር ለመገንዘብ እነሱን የሚመስል ሰው እዚያ ውስጥ መኖር አለበት የሚለው ነገር ነው። በጣም አስደነገጠኝ። ከዚያ በተጨማሪ ጃፓን ሀገር "ድፍረት" በየቴአትር ቤቱ ለማሳየት የስርጭቱን መብት ከወሰዱ በኋላ ፖስተሩን መቀየር ፈለጉ። ፖስተሩ ላይ የ13 ዓመት ኢትዮጵያዊት ታዳጊ ነው ያለችው። ተመልካች እሱን ካየ አያይልንም ብለው የአንጀሊና ጆሊን ፎቶ እናድርግበት ወይ? ብለው ጠይቀውናል''ብሏል።

አፍሪካ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ችግር ብቻ ሳይሆን፤ ከሃምሳ በላይ አገራት፣ ከ2000 በላይ ቋንቋዎች፤ ባህል፣ ጥበብ፣ ታሪክ ያላት በመሆኑ የራስን ታሪክ ራስ መንገር በሚልም ብዙ እንቅስቃሴዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ አፍሪካዊያንና ከነጩ ዓለም ውጭ ያለውን የደቡቡ ዓለም (ግሎባል ሳውዝ)ን ታሪክ በሲኒማ ለመንገር ያጠነጠነው ሰርድ ሲኒማን መጥቀስ ይቻላል።

ገና ሁለት ክፍል በወጣው በዚህ ፊልም ላይ ኢትዮጵያን በትንሽ ለማየት ያስቻለ ሲሆን በሚቀጥሉትም ክፍሎች በዋነኛው ገፀ ባህርይ ሳምባ በኩል ስለኢትዮጵያን ብዙ ልናይ እንችላለን።

ሳምባ ሹት ከዚህ ቀደምም በኔት ፍሊክስ የወጣው ታይገር ሃንተር፤ እንዲሁም ታዋቂውን የቪዲዮ ጌም ባትል ፊልድ ፅፏል። ከፊልሞችም በተጨማሪ ሽልማትን በተንበሸበሹ የቪዲዮ ጌሞች ላይ 'ስታር ዋርስ ጄዲ፡ ፎለን ኦርደር'፤ ኮል ኦፍ ዲዩቲ፡ ብላክ ኦብስ ተውኗል።