በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ የሞቱ ሰዎች አጽም ለቤተሰቦቻቸው እየተሰጠ ነው

በአደጋው ህይታቸውን ያጡ ኬንያውያን አስክሬን ለቤተሰቦቻቸው እየተሰጠ ነው።
አጭር የምስል መግለጫ በአደጋው ህይታቸውን ያጡ ኬንያውያን አስክሬን ለቤተሰቦቻቸው እየተሰጠ ነው።

ከወራት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ግለሰቦች አጽም ለቤተሰቦቻቸው እየተሰጠ ነው።

እለተ እሁድ መጋቢት 1/2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጠዋት 2፡38 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለሚያደርገው በረራ ጉዞ በጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አደጋው የደረሰው።

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

"እስካሁን ሙሉ የሰውነት ክፍል ማግኘት እንደተቸገርን ለቤተሰብ እያስረዳን ነው" አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

ቦይንግ 737 ማክስ የተከሰከሰው ቢሾፍቱ አቅራቢያ ሲሆን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ነበር።

በወቅቱ ተሳፍረው የነበሩት 157 መንገደኞች ከሰላሳ አገራት የተውጣጡ ሲሆኑ ከአደጋው የተረፈ ሰው አልነበረም። አደጋው በመላው ዓለም ድንጋጤን የፈጠረና ያሳዘነም ነበር።

ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት 32 ኬንያውያን ሲሆኑ አጽማቸውም ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ ነው።

አደጋውንም ተከትሎ "በጣም የሚያሳዝነው ነገር እስካሁንም በጣም የተወሰኑትን የሰውነት ክፍሎች እንጂ ሙሉ የሰውነት ክፍል አላገኘንም፤ ይህ ደግሞ ለቀሪ ሥራዎችም ትልቅ ፈተና እንደሚሆንብን እንጠብቃለን፤ ለሃዘንተኛ ቤተሰቦችም ይህን ችግር እያሰረዳናቸው ነው" በማለት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።

"አደጋውን ስሰማ በረራው ጠዋት እንዳልሆነ ራሴን አሳመንኩኝ" የረዳት አብራሪው ጓደኛ

የሟቾቹን አስከሬን ለመለየት የዲኤንኤ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ የሰባት ወራት ጊዜም ፈጅቷል። በቦሌ አየር ማረፊያ የቤተሰቦቻቸውን፣ የዘመድ ወዳጆቻቸውን አስከሬን ሊወስዱ የመጡ ግለሰቦች በሃዘን ድባብ ውስጥ ነበሩ።

ከአደጋው በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አስከሬናቸውን ማየት የቻሉት። በዛሬው ዕለትም በኬንያ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ግለሰቦች የሃዘን ሥነ ሥርዓትም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለስልጣናት እንደተናገሩት መለየት ያልተቻለ አስከሬን እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች አደጋው በተከሰተበት አካባቢ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ግለሰቦች በሚሰራው የማስታወሻ ስፍራ የሚቀበር ይሆናል።