በአፋር ክልል በተፈፀመ ጥቃት 17 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል

የኢትዮጵያ ካርታ

በአፋር ክልል፣ አፋንቦ ወረዳ፣ ኦብኖ ቀበሌ ሳንጋ የሚባል ጣቢያ ላይ አርብቶ አደሮች በሰፈሩበት አካባቢ ታጣቂዎች ፈፀሙት ባሉት ጥቃት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን አሊ ለቢቢሲ ገለፁ።

ባሳለፍነው አርብ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እስከ ቅዳሜ ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ ተፈፅሟል ባሉት ጥቃት፤ 17 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የስድስት ወር ህፃንን ጨምሮ ሴቶችና አረጋዊያን ይገኙበታል።

በ34 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል። አራቱ ከ7 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሲሆኑ፤ ዘጠኙ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን አቶ ሁሴን ተናግረዋል። የመቁሰል አደጋ ያጋጠማቸውም በአሳይታና በዱብቲ ሆስፒታሎች ሕክምና እየተከታተሉ ሲሆን የከፋ ጉዳት ያጋጠማቸው ወደ መቀሌ ሆስፒታል መላካቸውን ገልጸዋል።

የነዋሪዎቹ ንብረት የሆኑ በርካታ እንስሳትም ተገድለዋል፤ በንብረትም ላይ ጉዳት ደርሷል።

አቶ ሁሴን የጥቃቱን ምክንያት በውል ባያውቁትም ከዚህ በፊት ከሚደርሱ አንዳንድ ግጭቶች በመነሳት የመሬት ወረራ ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ።

"የመሬት ወረራ ነው፤ ወረዳው በሶማሌ ክልል ስር መሆን አለበት የሚሉ ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ፤ ስለዚህ የመሬት ወረራ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት የለም " ብለዋል።

መሬት ወረራ ለመሆኑ ምን ማስረጃ እንዳለቸው በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ሁሴን፤ ከአሁን በፊት የአርብቶ አደሮችን እንስሳት እየዘረፉና ግለሰቦችን እየገደሉ ይሄዱ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ታጣቂዎቹ በቁጥጥር ሥር አለማዋላቸውን የገለፁልን አስተዳዳሪው ካገኟቸው መታወቂያዎችና ሌሎች ማስረጃዎች ግን የጥቃት አድራሾቹን ማንነት መረዳት እንደቻሉ አስረድተዋል።

ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላም በአፋር ክልል በአብዛኛው የኢሳ ጎሳ አባላት ወደሰፈሩበት 'ሃሪሶ' የተባለ ቦታ መግባታቸውን ይናገራሉ።

"ጥቃት ፈፃሚዎቹ እንደ መትረየስ እና ቦምብ ያሉ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ተጠቅመዋል" የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው በጥቃቱ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋዊያን እና ወጣቶች ሰለባ ሆነዋል።

በወቅቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱን ለመከላከል ካደረጉት ጥረት ውጪ "ጥቃት አድራሾቹ ያሰቡት ከፈፀሙ በኋላ ወደ መጡበት ተመልሰዋል" ሲሉ የክልሉ መንግሥት የወሰደው እርምጃ እንደሌለ ይናገራሉ።

የክልሉ አመራሮች ወደ ሥፍራው አቅንተው የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱ ሲሆን አካባቢውን ለማረጋጋት እየሠሩ እንደሆነ አክለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በምሽት ወደ ሥፍራው በመሄድ እንስሳት መስረቅና አንዳንድ ሰዎችን ገድሎ መሄድ ካልሆነ በስተቀር እንደ አሁኑ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት ተፈፅሞ እንደማያውቅም ገልፀውልናል።

"በወረዳው 400 የሚጠጉ አርብቶ አደሮች ይኖራሉ" የሚሉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ አሎ ያዩ በበኩላቸው፤ በርካታ አርብቶ አደሮች በሚገኙበት ኦብኖ ቀበሌ ጥቃት መፈፀሙን ይናገራሉ።

በጥቃቱም በሰው ሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን የንብረት ውድመትም አስከትሏል። በአካባቢው በሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት እንደሚደርስ ያስረዳሉ።

አቶ አሎ ቦታው ድንበር በመሆኑ ከአዋሽ እስከ ጅቡቲ ያለው መንገድ ተመሳሳይ ጥቃቶችን እንደሚያስተናግድ ገልፀው፤ ከዚህ ቀደም ነፍሰ ጡሮች ሳይቀሩ የተገደሉበት አጋጣሚ መኖሩን አስታውሰዋል።

የአፋር ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሕመድ ካሎይታ፤ በክልሉ ዞን አንድ፣ አፋንቦ ወረዳ ላይ በአርብቶ አደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈፀሙን ይናገራሉ።

ጥቃቱም ከጅቡቲ በመጡ ከባድ መሳሪያ በታጠቁ ኃይሎች መፈፀሙንም ያስረዳሉ። በጥቃቱ ሴቶችና ህፃናትም ሰለባ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

"የደረሰው ጥቃት አሳዛኝና የሚያሳምም ነው" የሚሉት ኃላፊው አካባቢው ድንበር በመሆኑ ሕገ ወጥ ኮንትሮባንዲስቶች መንቀሳቀሻ መሆኑን አመልክተው፤ ታጣቂዎቹ ይህንን ሕገ ወጥ ድርጊት እንደልባቸው ለማንቀሳቀስ በማሰብ አርብቶ አደሮቹ ላይ ጥቃት እንደፈፀሙ ያስረዳሉ።

በጥቃቱም ከጂቡቲ የገቡ እና የኢሳ የታጠቁ ኃይሎች መሳተፋቸውን ይናገራሉ።

"በዋናነት ሕፃናትና ሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው ነው ጥቃቱን የፈፀሙት" የሚሉት ኃላፊው ሕይወታቸው ያለፉ እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና ላይ የሚገኙ እንዳሉ ተናግረዋል።

በአካባቢው ከክልሉ አልፎ ለአገር ስጋት የሆኑና ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ንግድ የሚያንቀሳቅሱ ግለሰቦች አሉ፤ ብዙ ጊዜም ሕገ ወጥ መሣሪያዎች በአካባቢው ይያዛሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።

በመሆኑም የሚመለከተው አካል አስቸኳይ መፍትሔ ሊወስድ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ባለሥልጣናት የአካባቢውን ሰላም ለማረጋጋጥ እየሠሩ መሆናቸውን አክለዋል።

በተያያዘ ዜናም አንዳንድ ወገኖች የጅቡቲ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት ፈጽሟል በሚል ያቀረቡት ክስ ሀሰት መሆኑን የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጹን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የዜና ተቋሙ የመከላከያ ሚኒስትር ምክትል ኤታማዦር ሹም ጽ/ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ አያሌውን ጠቅሶ እንደዘገበው በአፋር ድንበር በኩል የጅቡቲ ጦር የኢትዮጵያ ድንበር ገብቶ በአርብቶ አደሮች ላይ ጉዳት አደረሰ የሚለው መረጃ ሃሰት መሆኑን ገልጿል።

አክሎም በአካባቢው አልፎ አልፎ በግጦሽ፣ በውሃ እና በሌሎች ምክንያቶች ከሚከሰቱ ግጭቶች ውጪ በሁለቱ አገሮች መካከል ለግጭት የሚዳርግ ምንም ምክንያት አለመኖሩን አስረድተዋል።

በክልሉ በዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተም የመከላከያ ሠራዊት በሥፍራው ተገኝቶ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል።