"የተርባይኖች መቀነስ በሚመነጨው ኃይል ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም" የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ

የሜቴክ ኮንትራት ለፈረንሳይና ጀርመን ኩባንያዎች ሊሰጥ ነው Image copyright Grand Ethiopian Renaissance Dam

ከሰሞኑ በህዳሴ ግድቡ ሊገጠሙ ከታቀዱት አስራ ስድስት ተርባይኖች መካከል ሶስቱ እንዲቀነሱ ምክረ ኃሳብ መቅረቡን የሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሃሮ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የተርባይኖች መጠን መቀነሱ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጉዳዮች ምላሽ የሰጡት ኢንጅነሩ፤ አንድ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ትልቅነት የሚለካው ጄነሬተሮች ወይም ተርባይኖችን በመደርደር አይደለም ይላሉ።

አክለውም ብዙ ተርባይኖችን መደርደር ሁልጊዜም አዋጭ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

ግብጽ በአባይ ላይ ያለኝን መብት ለመከላከል ኃይሉም ቁርጠኝነቱም አለኝ አለች

ሱዳን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ አቋሟን ትቀይር ይሆን?

ስለአዲሱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ጥቂት እንንገርዎ

ኢንጅነሩ እንደሚሉት ከሆነ ለአንድ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ቁልፍ ከሆኑት ነገሮች መካከል የመጀመሪያው ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠንና ውሃው ከምን ያክል ከፍታ ተወርውሮ ተርባይኑን ይመታል የሚሉት ናቸው።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ከዝናብ መጠን ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን እና የውሃው የከፍታ መጠን ሊለያይ እንደሚችል በማስገንዘብ፤ የህዳሴ ግድቡ ያመነጫል ተብሎ የተሰላው በዓመት በአማካይ 15760 ጊጋ ዋት (Gigawatt hours) ወይም አንድ ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሃዎር እንደሆነ ይናገራሉ።

"በዚህ የኢነርጂ (ኃይል) መጠን ላይ የተለወጠ ነገር የለም" የሚሉት ኢንጂነሩ፤ "አሁን ይህን ኢነርጂ (ኃይል) ለተጠቃሚው እንዴት ላድርስ? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ጄነሬተሮች ይመጣሉ'' ይላሉ።

ጄነሬተሮች መካኒካል ኢነርጂን ወደ ኤሌክትሪካል ኢነርጂ እንደሚቀይሩ የሚያስረዱት ኢንጂነር ክፍሌ፤ "ጄነሬተር ወይም ተርባይን መደርደር በሚመነጨው የኢነርጂ (የኃይል) መጠን ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም" በማለት ያስረዳሉ።

የተርባይን እና ጄነሬተር ቁጥር የሚወሰነው፤ ግድቡ በሚይዘው የውሃ መጠን፣ ውሃው ከምን ያክል ከፍታ ላይ በምን ያክል ፍጥነት ተርባይኑን ይመታል፣ የኃይል ፍላጎት፣ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ እና የመሳሰሉት ላይ ነው ይላሉ።

"10፣ 12፣ 20 ጄነሬተሮች ቢደረደሩ ተመሳሳይ የሆነ ኢነርጂ (ኃይል) ነው ማመንጨት የምንችለው" በማለትም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

"ተርባይን ተቀነሰ ብሎ ማውራቱ ትርጉም የለውም። ለአንድ የኃይድሮ ኃይል ማመንጫ ወሳኙ ኢነርጂ (ኃይል) ነው" የሚሉት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ጥቅም ላይ ይውላሉ ከተባሉት ከ16ቱ ተርባይኖች መካከል ሶስቱን ለመቀነስ የታሰበው ከዋጋና አዋጭነት አንፃር እንደሆነ ያስረዳሉ።

ኢንጂነር ክፍሌ ይህ ውሳኔ በምንም አይነት መልኩ ከግብጽ ፍላጎት ጋር የተገናኘ አይደለም ያሉ ሲሆን፤ ይህ ውሳኔ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ብቻ ያስገባ እንደሆነ ያስረዳሉ።

"እንዳውም ብዙ ጀነሬተር ብንደርድር ብዙ ውሃ እንለቃለን ማለት ነው። ይህ ደግሞ የእነሱ ፍላጎት ነው" ብለዋል።

የሆሊውዱ ሃኪም ገብረወልድን ያውቁታል?

"ለእናንተ ደህንነት ነው በሚል እንዳሰሩን ተገልፆልናል" የባላደራ ምክር ቤት አስተባባሪ

ዋና ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 68.58 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። "ይህ የሲቪል፣ የኤሌክትሮ መካኒካል፣ የኃይድሮሊክስ ስትራክቸርን ጨምሮ ነው" ሲሉም ይናገራሉ።

"በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2013 ዓ.ም. ላይ ኃይል ማመንጨት እና 2015 ደግሞ ፕሮጀክቱን ማጠናቀቀ የተያዘ እቅድ ነው" ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል ልዩነቶችን መፈጠሩ ይታወሳል።

ከቀናት በፊት የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሹኩሪ ለግብጽ የህዝብ እንደራሴዎች ባሰሙት ንግግር ግብጽ ከአባይ ወንዝ የምታገኘው ጥቅም እና መብት አስከብራ ለማስቀጠል ቁርጠኝነቱ እንዳላት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ ያደረጉት የሦስትዮሽ ምክክር አለመሳካቱን ተከትሎ ግብፅ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል።

የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ አሜሪካ አደራዳሪ እንድትሆን ፍላጎታቸውን ቢያሳዩም፤ ኢትዮጵያ ግን የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት፤ በሦስቱ አገራት መካከል የተደረሱ አበረታች ስምምነቶችን የሚያፈርስ ከመሆኑ በተጨማሪ ሦስቱ አገራት በመጋቢት 2017 የፈረሟቸውን የመግለጫ ስምምነቶችም ይጥሳል በማለት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል ገልጻለች።

የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር በሩሲያ ተገናኘተው በጉዳዩ ላይ ለመምከር መስማማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ፕሬዝደንቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን በሩሲያ መቼ እንደሚያገኙ ግልጽ ባያደርጉም ሩሲያ ጥቅምት 12 እና 13 ሩሲያ-አፍሪካ መድረክ ታዘጋጃለች።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ