ኮንታ ልዩ ወረዳ፡ የ22 ሰዎች ሕይወትን የቀጠፈው የመሬት ናዳ

በደቡብ ክልል ኮንታ ልዩ ወረዳ አደጋው የደረሰበት ሥፍራ የሟቾችን አስከክሬን ፍለጋ ተጠናክሮ ቀጥሏል Image copyright Facebook/SEPD Facebook page

በደቡብ ክልል ኮንታ ልዩ ወረዳ ጥቅምት 2/2012 ዓ.ም ከሌሊቱ አስር ሰዓት ተኩል አካባቢ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የአምስት ቤተሰቦች አባላት መሞታቸውን የልዩ ወረዳው አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፋሲካ ሙሉጌታ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

እነዚህ አምስት ቤተሰቦች ይኖሩባቸው የነበሩ አምስት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሰጥመው የ22 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ኃላፊው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የልዩ ወረዳው ኮሚዩኑኬሽን ኃላፊ እንደገለፁት እነዚህ አምስት ቤተሰቦች ያረቧቸው የነበሩ እንስሳቶችም ሙሉ በሙሉ ሞተዋል፤ ሰብልም ወድሟል።

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት የማግባታቸው ወሬ ቢነፍስም ቀዳማዊቷ እመቤት ወደ ሃገራቸው ተመለሱ

"የተርባይኖች መቀነስ በሚመነጨው ኃይል ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም" የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ

የዩሮ 2020 ማጣሪያ ጨዋታ በዘረኛ ስድብ ሁለቴ መቋረጡ ተሰማ

የአካባቢው ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገው አቶ ፋሲካ እንደሚናገሩት በቤቶቹ ውስጥ በእንግድነት መጥተው የነበሩ ሰዎች ከነበሩ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

የአስራ ሰባት ሰዎች አስክሬን በሰው ጉልበት ተቆፍሮ መውጣቱንና የቀሩትን ለማውጣት ኅብረተሰቡ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አቶ ፋሲካ ጨምረው ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓት የልዩ ወረዳው አስተዳደር ኃላፊዎች፣ የካቢኔ አባላትና በልዩ ወረዳው አቅራቢያ በኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ሥራ ላይ የተሰማራው ሳሊኒ ባለሙያዎቹንና ኤክስካቫተር በማምጣት ቀሪ አስክሬኖችን ለማውጣት እየተረባረቡ ነው።

በልዩ ወረዳው ዱካ ዛሌ ቀበሌ 03 በተባለው ስፍራ በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ላይ የደረሰው ይህ አደጋ ነዋሪዎች በእንቅልፍ ላይ እያሉ በሌሊት በጣለ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱንም ኃላፊው ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳው ባለፈው ዓመት ነሐሴ 4 በተከሰተ ናዳና ጎርፍ የሁለት ሰው ሕይወት ማለፉን የሚያስታውሱት አቶ ፋሲካ፤ በተጨማሪም በዚህ ዓመት መስከረም 24 ደግሞ በተከሰተ ሌላ ናዳ በርካታ ሰብል የወደመ ሲሆን 130 ሰዎችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የመደፈሬን ታሪክ ከስልሳ ሰባት ዓመታት በኋላ የተናገርኩበት ምክንያት

ይህ ጥቅምት 2 ንጋት ላይ የደረሰው ናዳ የ22 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ በመሆኑ የአካባቢው አስተዳደርና ህብረተሰብን ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ እንደጣለ ተናግረዋል።

ኮንታ ልዩ ወረዳ አብዛኛው የመሬት አቀማመጥ ተዳፋት መሆኑን አስታውሰው በአካባቢው አሁንም የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ስፍራዎች ስላሉ የክልሉና የፌደራል መንግሥት ዘላቂ መፍትሄ ሊፈልጉ ይገባል ሲሉ ይማፀናሉ።

ዛሬ ማለዳ ከደቡብ ክልል የተለያዩ ድጋፎችን ይዘው የመጡ ባለሙያዎች መኖራቸውን አቶ ፋሲካ ገልጸው ዘላቂ መፍትሄ ግን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል መንግሥት የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ አስመልክቶ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን ወደ ስፍራው ያንቀሳቀሰ መሆኑን እና ለተጎጂ ቤተሰቦች አልባሳት እና መድሀኒቶች ወደ ስፍራው መላኩንም በፌስቡክ ገፁ ላይ አስታውቋል።

በቀጣይ ተጨማሪ ድጋፍ ወደ ስፍራው እንደሚላክና በአካባቢው በሚጥለው ከባድ ዝናብ የተነሳ ለመሰል አደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከአደጋ የመከላከል ስራ ትኩረት የሚሰጠው እንደሚሆንም የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬቴሪያት መናገሩን ዘግቧል።

ተያያዥ ርዕሶች