እሷ ማናት #2፡ ዘቢብ ካቩማ የተባበሩት መንግሥት ሴቶች ዋና ኃላፊ

ዘቢብ ካቩማ የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች ክፍል ዋና ኃላፊ Image copyright UN Women Kenya/Kennedy Okoth
አጭር የምስል መግለጫ ዘቢብ ካቩማ የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች ክፍል ዋና ኃላፊ

ዘቢብ ካቩማ እባላለሁ የሁለት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ እናት ነኝ። ባለቤቴ ፖል ካቩማ ይባላል። ነዋሪነቴ ኬንያ ሲሆን ለምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች ክፍል ዋና ኃላፊ ነኝ።

ኑሮን 'ሀ' ብዬ ስጀምር ስለ መድረሻዬ የማውቀው ነገር የነበረ አይመስለኝም። ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስበው ግን እንዲያው የነገሮች ሂደት ነው ቀስ ብለው ዛሬ ያለሁበት ያመጡኝ ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል።

ገና ልጅ እያለሁ ነበር በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያሉትን ልዩነቶች ማየት የጀመርኩት። እርሱም ሰዎች ለሁለቱ ፆታዎች ያሏቸው አመለካከቶች የተለያዩ መሆናቸውን ስላየሁ ነበር። ሁልጊዜ እራሴን፣ የማደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ እና ብቃቴንም ጭምር ማስረዳትም ሆነ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅብኝ እንደነበር ተረዳሁኝ።

እናቴን በትኩረት እየተከታተልኩ በማደጌ ደግሞ ከወንዶች እና ከሴቶች የሚጠበቁት ነገሮች የተለያዩ መሆናቸውን ቶሎ ደረስኩበት። ለእነዚህ ልዩነቶች የነበረኝ ትኩረት ነው አሁን የደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ የገፋፋኝ ብዬም አምናለሁ።

እውነቱን ለመናገር በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ አይደለም በዋና ኃላፊነት በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ እሠራለሁም ብዬ ጠብቄ አላውቅም ነበር። ጭራሽ ትኩረቴን የማይስብ ድርጅት ነበር። ሕይወት ደግሞ የራሷ መስመር አላት መሰለኝ በሂደት እራሴን እዚህ ቦታ ላይ አግኝቼዋለሁ።

ማስተርሴን በኮሎምብያ ዩኒቨርሲቲ እየሠራሁ ሳለ ነበር የሥራ ልምምድ ዕድል ዩኤንዲፒ በተሰኘው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ውስጥ አግኝቼ ለተወሰነ ጊዜ የሠራሁት። ከዚያም ትምህርቴን ጨርሼ በአጋጣሚ ኬንያ ለጉብኝት መጥቼ ሳለ ነው በተባበሩት መንግሥታት ፌምኔት የተሰኘው ክፍል ውስጥ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ሳገኝ አመልክቼ ነው ወደ ድርጅቱ የገባሁት።

ቀስ በቀስም በሥራዬ እድገት እያገኘሁ የኬንያ ዋና ኃላፊ ሆንኩኝ ቀጥሎ ደግሞ አሁን እየሠራሁበት ወዳለው የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ዋና ኃላፊ በመሆን ከፍ ወዳለ ደረጃ ደረስኩ።

Image copyright UN Women Kenya/Kennedy Okoth
አጭር የምስል መግለጫ 'ኔስትሌ' የተሰኘው ድርጅት በኬንያ ለሴቶች ብቃት ፕሮግራም ሲፈርሙ

አሁን ሳስበው ሕልሜን እንዳሳካሁ ነው የምቆጥረው።

ብዙ ሰዎች እዚህ እንደምሠራ ሲያውቁ "እናንተ መሥሪያ ቤት ወንዶች አሉ?" በማለት የሚጠይቁኝ የመጀመሪያ ጥያቄ ነው። ለሴቶች የሚቆም ድርጅት በመሆኑ ሴቶች ብቻ ያለን ይመስላቸዋል። በእርግጥ በቁጥር የምንበዛው ሴቶች ብንሆንም ወንዶችም ግን አብረውን ይሠራሉ።

እንደዚህ ዓይነትና ከሥራችን አንፃር 'ለምን' የመሳሰሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡልኝ ያስገርመኛል፤ ምክንያቱም ሴት መሆን በእራሱ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያስከትላል በተለይ በሥራ ገበታ ላይ። ይህን የምልበት ደግሞ ምክንያት አለኝ። ደግነቱ በምሠራበት ቦታ ብዙዎቻችን ሴቶች በመሆናችን ብዙ ሴቶችን ከተቃራኒ ፆታ የሚደርሱባቸው የተለያዩ ችግሮች አይገጥሙንም።

እንደዚያም ሆኖ ግን በዚህ ዓለም ሴት መሆን በእራሱ ችግር ነው። በተለይ ሃሳቧን ያለምንም ችግር ያለምንም ማንገራገር የምትገልፅ ሴት መሆን ፈተና አለው። እኔንም ጭምር 'ጉረኛ ነሽ' እና 'ጠብራራ ነሽ' የመሳሰሉ አስተያየቶችን የሚሰጡኝ ሰዎች ብዙ ናቸው። ሰዎች በትንሽ ምክንያት ያላቸው አመለካከት፣ አነጋገራቸውና ሁኔታቸው ሲቀያየር ማየትም የተለመደ ነው።

ለምሳሌ ብዙ ሴቶች በተሰበሰቡት ክፍል ውስጥ አንድ ወንድ ቢኖር፤ መቃለዱንና አኳዃኑን ያየ ሰው እና የተገላቢጦሽ ሆኖ ደግሞ አንድ ሴት ወንዶች በተሰበሰቡበት ብትቃለድ ሁለቱ ግለሰቦች በተመሳሳይ ዓይን አይታዩም። እራሴም ብሆን ሴትን በማይበት ጊዜ በአለባበሷ፣ በአነጋገሯ እና በምታቀርባቸው ሃሳቦች ላለመገምገም እጥራለሁ። ማንነታችንን ማወቅ አለብን ከዚያም ደግሞ ያለ ምንም ማንገራገር እራሳችንን መሆን አለብን ብዬ ስለማምን ማለት ነው።

ጠንካራ መሆን ብዙ እንደሚጠይቅ አውቃለሁ። ከእራሴ ተሞክሮ የተማርኩትም ይኼንኑ ነው። የማይረሳኝ ተማሪ እያለሁ ሕንድን የማየት ፍላጎት ነበረኝ። ለባህልም፣ ለኃይማኖት ያለን ቦታ፣ ለቤተሰብ የምንሰጠው ቦታና ሌሎችም ነገሮች በጣም ይመሳሰሉብኝ ስለነበር በዓይኔ ማየት ፈልጌ ወደ ሕንድ አቀናሁ።

ብቻዬን ነበርኩኝ። ሃገሪቷንም አካለልኳት። ቀስ በቀስ ግን ነዋሪዎቹ ግራ ይጋቡ እንደነበር ለመገንዘብ አላስቸገረኝም። ሲገባኝ፤ ሴት መሆኔ፣ ወጣት መሆኔ፣ ብቻዬን መሆኔ እና ከዚያም አልፎ ደግሞ የቆዳዬን ቀለም አይተው ከየት መምጣቴም ሆነ ማንነቴ በጣም አወዛግቧቸው ነበር። በባህላቸው ወጣት ሴት ልጅ ለዚያውም ያላገባች ሴት ብቻዋን ሃገር ማቋረጥ አይደለም በሰፈሯ መንገድ አትሄድም።

Image copyright UN Women Kenya/Kennedy Okoth
አጭር የምስል መግለጫ ስደተኞችና በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የብቃትና እርዳታ ፕሮግራም ላይ

አንድ ቀን የሦስት ሰዓት መንገድ ለመጓዝ በአውቶብስ ተሳፍሬ ከአጠገቤ የነበረው ወንድ ሲተሻሸኝና ቀስ እያለ እግሬን ሲነካካኝ፤ የማደርገው ነበር የጠፋኝ። ምክንያቱም የተጠባበቀ ባስ ውስጥ ነን። መቆም፣ መነሳትም ሆነ መንቀሳቀስ አልቻልኩም በዚያ ላይ ላነጋግረው ብሞክር እንኳን በቋንቋ መግባባት አልቻልንም።

ሴትነቴ በጣም ተሰማኝ። ይህን ለማድረግ የገፋፋው ምንም ይሁን ምን ማንነቴን እየተጋፋ ነው። እዚያ ቦታ ላይ መገኘቴ ውስጤን እንዲከፋው ቢያደርግም እንደ ማንኛውም ሰው እዚያ የመሆን መብቴ ግን መጠበቅ አለበት። ለዚያ ነው ሁሌም ለሌሎች "የመተንፈስ፣ የመኖር እና ያላችሁበትን ቦታ የመያዝ መብት አላችሁ" የምለው።

ከሥራዬ አንፃር አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችን በሙሉ ወደ እኩልነት የምንገፋፋ ሊመስል ቢችልም ይህ አለመሆኑን ግን ማስረዳት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም እያልን ያለነው ወንዶች የሚያደርጉትን በሙሉ ወይም ባሉበት ቦታ ሁሉ ሴቶችም እኩል ቦታ ይያዙ ሳይሆን ማድረግ የሚፈልጓቸውንና መሆን በሚፈልጉባቸው ቦታዎች የመሆን መብታቸው ይጠበቅ ነው፤ ይህ ነው እኩልነት።

አንዳንድ ሴቶች በርግጥ ልጆቻቸውን ማሳደግ ሊመርጡ ይችላሉ ይህም ቢሆን መብታቸው ነው። ሌሎች ተቀጥረው መሥራትን፣ ሌሎች ደግሞ በእራሳቸው የንግድ ሥራ መሰማራት ሊፈልጉ ይችላሉ፤ ይህም ቢሆን መብታቸው ነው። በስመ ሴት ሁሉንም ሴት በአንድ ላይ መፈረጅ ተገቢ አይደለም።

ሴቶችን ማብቃት ሲባል በቢሮ ሥራ ውስጥ ወይንም በንግድ የተሰማሩት ብቻ ላይ ያተኮረ መሆን የለበትም። ሁሉም ሴት በየራሳቸው መንገድ የተለያዩ ችግሮችን መወጣታቸው ስለማይቀር ክብርም ሆነ አድናቆት የምናደርገው ለተወሰኑ ሴቶች ብቻ መሆን የለበትም ማለት ነው። የማብቃት ሥራችን ግን ብቻውን ትርጉም አይሰጥም። ምክንያቱም ፖሊሲ የሚነድፉ እና በመንግሥት ደረጃ ውሳኔ የሚወስኑ ንግግሩም ላይ ሆነ ሥራው ላይ ካልተሳተፉ የምናስቀምጣቸው ፕሮግራሞች ፕሮጀክቱ ሲያልቅ መቋረጣቸው አይቀርም። ለዚህም ነው ብቻችንን አንሠራም የምንለው።

ከድሮም የሚያስገርመኝ ነገር ቢኖር ወንዶች በሙሉ የሚያደንቁትን ሰው ሲጠየቁ ከእናቶቻቸው ወይም ከአያቶቻቸው አያልፍም። ለምንድን ነው ታድያ ይህን ፍቅርና አድናቆት ለሌሎች ሴቶች ማሳየት የማይችሉት እያልኩ እራሴን እጠይቃለሁ። ይህም ብዙ ጊዜ ደግሞ ከአስተዳደጋችን አያልፍም። ለምን ቢባል ወንዶችን ጠንካራ እንዲሆኑ ሴቶችን ደግሞ አሳቢ እንዲሆኑ እያደርግን ነው የምናሳድጋቸው። ይህ በእራሱ መጥፎ ነው ለማለት ሳይሆን ሁለቱም ፆታዎች ሁለቱንም እንዲሆኑ ብናደርጋቸው ምን አለበት ነው ይምለው።

እሷ ማናት? የሚለው ጥንቅራችን ያሰቡበትን ዓላማ ለማሳካት ብዙ ውጣውረዶችን ያሳለፉ ሴቶችን ታሪክ የምናስቃኝበት ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ