ተማሪዎች የካርቶን ሳጥን አጥልቀው ፈተና እንዲፈተኑ ያደረገ የህንድ ትምህርት ቤት ይቅርታ ጠየቀ

ተማሪዎች በፈተና ሰዓት የካርቶን ሳጥን ጭንቅላታቸው ላይ አጥልቀው ያሳያል Image copyright ANI

ተማሪዎች ጭንቅላታቸው ላይ የካርቶን ሳጥን አጥልቀው ፈተና እንዲፈተኑ ያደረገው የህንድ ትምህርት ቤት ባለሥልጣን ይቅርታ ጠየቀ።

ትምህርት ቤቱ ይቅርታ የጠየቀው ያልተለመደውና ተማሪዎች የካርቶን ሳጥን አጥልቀው የሚያሳየው ፎቶ በርካታ ሰዎችን ካነጋገረ በኋላ ነው።

ፎቶው የተነሳው በካርናታካ ግዛት በባጋት ቅድመ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የኬሚስትሪ ፈተና ሲፈተኑ ነበር።

ለተማሪ ሲፈተኑ የተያዙት ርዕሰ-መምህር 5 ዓመት ተፈረደባቸው

ክፍያ ባልከፈለ ተማሪ እጅ ላይ ማህተም የመታው ትምህርት ቤት ተወገዘ

በፎቶግራፎቹ ላይ እንደሚታየው ተማሪዎቹ በአንድ በኩል የተሰነጠቀ የካርቶን ሳጥኖች አጥልቀው የነበረ ሲሆን እንዳይኮራረጁ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ ነው።

ይህንን ተከትሎ የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ በተፈጸመው ድርጊት የግዛቷ ባለሥልጣናትን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ሳቲሽ፤ ኩረጃን ለመከላከል ያልተለመደ መንገድ በመጠቀማቸው ይቅርታ መጠየቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉት ተማሪዎችን እንዳይኮራረጁ ለማስቻል ይህንን ዘዴ የተጠቀሙት የሆነ ቦታ ስለ ጠቀሜታው በመስማታቸው ለመሞከር በማሰባቸው ነው።

ተማሪዎቹ ፈቃደኛ በመሆናቸው የራሳቸውን የካርቶን ሳጥን ይዘው በመምጣት ውሳኔውን ተግባራዊ እንዳደረጉም አስተዳዳሪው አክለዋል።

"በምንም ዓይነት መልኩ አልተገደደዱም፤ በፎቶግራፉ ላይ ጥቂት ተማሪዎች ካርቶኑን ሳያጠልቁ ይታያሉ። ካርቶኑንም ከ15 ደቂቃ በኋላ፤ አንዳንዶች ደግሞ ከ20 ዲቂቃ በኋላ አውልቀውታል፤ እኛ ራሳችን ከአንድ ሰዓት በኋላ እንዲያወልቁት ጠይቀናቸዋል።" ብለዋል።

የግዛቷ ባለሥልጣናት ፎቶግራፉን እንዳዩ በፍጥነት ወደ ትምህርት ቤቱ በመሄድ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

1550 ተማሪዎች ለኩረጃ ሲሉ ስማቸውን ለውጠዋል

ህንዳዊቷ ተማሪ ራሷን በማጥፋቷ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን አቃጠሉ

የቅድመ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት የቦርድ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ፒርጃደ፤ ድርጊቱን "ሰብዓዊነት የጎደለው ነው" ሲሉ አውግዘውታል።

"በዚህ ጉዳይ ላይ መልዕክት ሲደርሰኝ፤ ወዲያውኑ ነበር ወደ ኮሌጁ ስከንፍ የደረስኩት። ከዚያም የኮሌጁ አስተዳደር ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ነግሬያቸዋለሁ" ብለዋል።

"ለኮሌጁ አስተዳደር አሳውቄያለሁ፤ በተማሪዎቹ ላይ ይህንን ድርጊት በመፈፀማቸውም ሥነ ምግባር በመጣስ እንዲቀጡ እናደርጋለን" ማለታቸውን ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ እርሳቸውን ጠቅሶ ዘግቧል።

የትምህርት ቤቱ ባለሥልጣን በበኩላቸው ድርጊቱን እንዳቆሙ ገልጸው፤ በትምህርት ቤቱ ቦርድ መርህ በመከተል በትብብር እየሠሩ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ