ወደ አውስትራሊያ ሲያቀኑ ለነበሩ ስደተኞች ሞት ምክንያት ነው የተባለው ኢራቃዊ ተከሰሰ

የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ አርማ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በጎርጎሮሳዊያኑ 2001 በተፈጠረው አደጋ ክስ ሲቀርብ የ43 ዓመቱ ኢራቃዊ ሦስተኛው ግለሰብ ነው።

የአውስትራሊያ ፖሊስ ከ350 በላይ ስደተኞች ሞት ምክንያት ለሆነው የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እጁ ነበረበት ያለው ኢራቃዊ ግለሰብ ላይ ክስ መሠረተ። በጎርጎሮሳዊያኑ 2001፤ ጥገኝነት ፈላጊ ስደተኞች ከኢንዶኔዥያ ወደ አውስትራሊያ ለመሄድ የተሳፈሩባት ጀልባ የመስጠም አደጋ አጋጥሟታል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ረቂቅ ህግ የሞት ቅጣት ተካቶበታል

በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ረቂቅ ጥፋተኛና አቃቤ ህግ ይደራደራሉ

ፖሊስ እንዳለው የ43 ዓመቱ ኢራቃዊ የስደተኞቹን ጉዞ በማቀነባበር እና ከስደተኞቹ ገንዘብ በመቀበል የዝውውሩ አካል ነበር።

ኢራቃዊው በኢንዶኔዥያ ባህር ዳርቻ ለተፈፀመው የጀልባ መስጠም አደጋ ክስ የቀረበበት ሦስተኛው ግለሰብ ነው።

ይህ ግለሰብ ከኒውዚላንድ ተላልፎ በመሰጠት በቢርስቤን አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል። ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም እስከ 10 ዓመታት እስር ይጠብቀዋል ተብሏል። ከ11 ቀናት በኋላም በብሪስቤን ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተገልጿል።

ምንም እንኳን ባለሥልጣናት የግለሰቡን ስም ባይጠቅሱም 'የሲይድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ጋዜጣ' ግለሰቡ ሜይዜም ራዲሂ እንደሚባል ገልጿል።

በጎርጎሮሳዊያኑ 2009 ከአገሩ በአስገዳጅ ሁኔታ መሰደዱን፣ የስደተኛ ሁኔታ ተመዝግቦ ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር በኦክላንድ ይኖር ነበር።

ራዲሂ የቀረበበትን ክስ የተቃወመው ሲሆን ላለፉት አስርት ዓመታትም ተላልፎ እንዳይሰጥ ሲሟገት ቆይቷል።

የአገሪቷ ፖሊስ ኮሚሽነር ሬሲ ኬርሻው በበኩላቸው "ከ350 በላይ ስደተኞች የሞቱበትን አሳዛኝ አጋጣሚ እውነታ መማየት አለብን" ሲሉ በመግለጫቸው አስረድተዋል።

የሰሀራ በረሐን በክራች ያቋረጡት ስደተኞች

ከመስመጥ አደጋ የተረፉት ሁለት ኤርትራዊያን ስደተኞች

ኮሚሽነሩ አክለውም "ፍትህ ማግኘት አለባቸው፤ በዚህ ንግድ በመሰማራት በሰው ሕይወት የሚነግዱ ሰዎችን ለማዳከምም እንሰራለን" ብለዋል።

ወደ ክሪስማሷ ደሴት እያመራች በነበረችው ጀልባ የደረሰውን ይህንኑ አደጋ አስመልክቶ ምርመራውን መቀጠሉን የአውስትራሊያ ፖሊስ አስታውቋል።

ከዚሁ አጋጣሚ ጋር በተገናኘ በጎርጎሮሳዊያኑ 2003 ከስዊድን ለአውስትራሊያ ተላልፎ የተሰጠው ኢራቃዊው ካሊድ ዳኦድ ለፈፀመው የሕገ ወጥ ዝውውር 9 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ ተወስኖበታል።

ሌላኛው የጉዞው አቀናባሪ ግብፃዊው የሰዎች አዘዋዋሪ አቡ ቋሰይ በትውልድ አገሩ በጎርጎሮሳዊያኑ 2003 የሰባት ዓመታት እስር ተበይኖበታል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ፈላጊዎች በየዓመቱ ወደ አውስትራሊያ ለመግባት የሚሞክሩ ሲሆን እንዲያሻግሯቸውም ለሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በርካታ ገንዘብ ይከፍላሉ።

ስደተኞቹ በአካባቢው ለቁጥጥር አስቸጋሪ የሆነውን የኢንዶኔዥያ ድንበር እንደመሻገሪያ ይጠቀሙበታል።

ጉዞው በጣም አደገኛ በመሆኑም በባህር ላይ የሚቀሩ ስደተኞችን ለመታደግ የአውስትራሊያ መንግሥት የነፍስ አድን ሥራዎችን በተደጋጋሚ ለማድረግ ይገደዳል።

ይሁን እንጂ አሁንም ስደቱ እንደቀጠለ ሲሆን በአውስትራሊያ ፖለቲካም አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል። አውስትራሊያ ያለ ቪዛ ወደ አገሪቷ የሚገቡ ስደተኞችን እንዲታሰሩ በሚያዘው ሕጓም ትተቻለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ