ከልክ በላይ በወፈሩ ሰዎች ሳንባ ውስጥ ስብ እንደሚፈጠር ተደረሰበት

የሳንባ ባለ ሦስት አውታር ምስል Image copyright Getty Images

ላልተመጣጠነና ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት የተጋለጡ ሰዎች ሳንባ ውስጥ ስብ ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘቱ ተገለፀ።

አውስትራሊያዊያን ተመራማሪዎች ከ52 ሰዎች የተወሰደ ናሙና ላይ ተመስርተው ባካሄዱት ምርምር በሳምባቸው ውስጥ የተገኘው የስብ ክምችት መጠን እንደ ሰውነታቸው የክብደት መጠን መጨመሩን ያመለክታል።

"ወፍራም ሴቶች ለአገርም ለቤተሰብም ሸክም ናቸው" የግብፅ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ

ቁርስ የቀኑ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነውን?

አጥኚዎቹ እንዳሉት ግኝቱ ላልተመጣጠነና ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት የተጋለጡ ሰዎች፤ እንደ አስም ላሉ የመተንፈሻ አካል የጤና ችግሮች የመጋለጣቸው እድል ሰፊ እንደሆነ ያስረዳል።

የመተንፈሻ አካል ባለሙያዎች በበኩላቸው ሰዎቹ ክብደት ሲቀንሱ ችግሩ ይስተካከል እንደሆነ ጥናቱ ቢመለከተው መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአውሮፓ ሪስፓራቶሪይ ጆርናል ላይ የታተመው ይህ ጥናት፤ ተመራማሪዎቹ ለምርምራቸው ከሞቱ ሰዎች የተለገሱ ሳንባዎችን በናሙናነት ተመልክተዋል። በዚህም መሠረት 15 የሚሆኑት አስም ያልታየባቸው ሲሆን 21ዱ የጤና ችግሩ ታይቶባቸዋል።

ይሁን እንጂ ሕይወታቸው ያለፈው በሌሎች ምክንያቶች ነበር። 16 የሚሆኑት ግን በዚሁ ችግር ሕይወታቸው ማለፉን ጥናቱ አሳይቷል።

ተመራማሪዎቹ በዝርዝር ለማጥናት ከተወሰዱ የሳንባ ናሙናዎች 1400 የሚሆኑ የአየር ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ላይ በማይክሮስኮፕ ጥልቅ ምርመራ አድርገዋል።

በዚህም መሠረት ተመራማሪዎቹ በአየር ማስተላላፊያ ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ የስብ ክምችት ያገኙ ሲሆን ችግሩ በተለይ ከመጠን በላይ የወፈሩ ሰዎች ላይ ታይቷል።

በመተንፈሻ ቧንቧው ላይ የስብ ክምችቱ እየጨመረ መምጣቱም፤ ጤናማ ለሆነው የአተነፋፈስ ሥርዓት መዛባትና የሳንባ መቆጣት እንደሚከሰት የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ተብሏል።

በጥናቱ ላይ የተሳተፉት በምዕራብ አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ፒተር ኖቤል "ያልተመጣጠነ ወይም ከመጠን በላይ ውፍረት ከአየር ቧንቧ ከሚከሰት የጤና ችግር ጋር የተያያዘ ሲሆን በጣም ከባድ የሆነ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል" ብለዋል።

የጤና እክሉ ከመጠን በላይ በሆነ ውፍረት ምክንያት በሳንባ ላይ በሚፈጠር ጫና ወይም ከውፍረቱ ጋር ተያይዞ በሚመጣ የሳንባ መቆጣት ጋር ሊያያዝ ይችላል። ይሁን እንጂ ዶክተር ፒተር እንደሚሉት ሌላ ምክንያትም ሊኖረው እንደሚችል በጥናቱ ተጠቁሟል።

"በአየር ቧንቧ ግድግዳ ላይ ያለው የስብ ክምችት፤ የአየር መተላለፊያ ቦታን በመያዝ በሳንባ ላይ መቆጣትን እንደሚያስከትል በጥናቱ ደርሰንበታል" ብለዋል ዶክተር ኖቤል።

ሳናውቀው በሰውነታችን ውስጥ የሚከማች አደገኛ ስብ

በፈረንሳይ ክብደት ይቀንሳል በተባለ መድሃኒት እስከ 2ሺህ ሰዎች ሞተዋል ተባለ

ይህም የአየር ቧንቧው እንዲወፍር በማድረግ ወደ ሳንባችን የሚገባውንና የሚወጣውን አየር መጠን በመገደብ፤ የመተንፈሻ አካል የጤና ችግር አመላካች ነው ብለዋል።

የአውሮፓ የመተንፈሻ አካላት ጤና ማህበር አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ቴሪ ትሩስተር እንዳሉት በክብደት መጠን መጨመርና በመተንፈሻ አካል የጤና ችግሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳየት ጥናቱ ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም ከልክ በላይ ውፍረት ለእንደዚህ ዓይነት የጤና ችግሮች ምልክት መሆኑን ሲያመላክት በተለይ አስም ላለባቸው ሰዎች ችግሩ የከፋ ይሆናል።

ጉዳዩ በጣም ወፍራም ሰዎች ሥራ ሲሠሩና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ እንደሚፈልጉ ከመመልከትም በላይ ነው ይላሉ።

በመሆኑም ክብደት ሲቀነስ የስብ ክምችቱም እየቀነሰ ይመጣ እንደሆነ ለማወቅ ሌላ ጥናት መሥራት ቢያስፈልግም፤ በተለይ የአስም ታማሚዎች ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖራቸውም ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲል ጥናቱ አሳስቧል።

በእንግሊዝ ቶራሲስ ሶሳይቲ ኮሚቴ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ኦልሳቤት ሳፔይ በበኩላቸው የሰውነት ክብደት ከአየር ቧንቧ ችግር ጋር መገናኘቱን ያሳየ የመጀመሪያው ጥናት መሆኑን ገልፀዋል።

"በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ የሚታየውን ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር መጨመርን ስንመለከት፤ የአስም ሕመም ምን ያህል ከባድ የጤና እክል እንደሆነ ለመረዳት ያስችላል" የሚሉት ዶክተር ኤልሳቤት፤ የአስም ሕመምን ለማከምም የሚረዱ ዘዴዎችን ለመለየት ጥናቱ ያግዛል ብለዋል።

"ጥናቱ በተወሰነ መልኩ የተሠራ ነው፤ ነገር ግን ሰፊ ቁጥር ባላቸው ህሙማን ላይ እና በሌሎች የመተንፈሻ አካል የጤና ችግሮች ጋር በስፋት መመልከት አለብን" ሲሉ አክለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ