ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄዱ የነበሩ ስብሰባዎች በቡድን በመጡ ወጣቶች መስተጓጎላቸው ተነግሯል

አዲስ አበባ Image copyright Sean Gallup

ትናንት የአማራ ወጣቶች ማህበር እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሥፍራዎች ሲያካሂዷቸው የነበሩ ስብሰባዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ወጣቶች መስተጓጎላቸው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ትናንት ጥቅምት 9፣ 2012 ዓ.ም. በዓላማ እና ግቦች፣ የፖለቲካ አመለካከቶች እንዲሁም የምርጫ ዝግጅት ዙሪያ በአዲስ አበባ የተለያዩ ወረዳዎች ከአባላት ጋር ውይይት ማካሄዱን የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ይሁን እንጅ ስብሰባው ከተካሄደባቸው ሥፍራዎች መካከል ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 (በምርጫ ወረዳ አጠራር 'ምርጫ ወረዳ 19') የነበረው ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት የተወሰኑ ወጣቶች "ስብሰባው አይደረግም፤ ሰዎች ወደ አዳራሹ አይገቡም" የሚል ክልከላ አድርገው እንደነበር ይገልፃሉ።

"በወቅቱ አባላቶቻችን ተረጋግተው፤ ሰዎችን ለማረጋጋት ሞክረዋል።" የሚሉት የህዝብ ግነኙነት ኃላፊው፤ ሁኔታውን መቆጣጠር እንደማይቻል ሲገነዘቡ ፖሊስ እንዲጠራ መደረጉን ተናግረዋል።

"ውስኪ ጠጪ ኢህአዴጎች እባካችሁ ውሃ የናፈቀው ሕዝብ እንዳለ አትርሱ" ጠ/ሚ ዐብይ

"አሁን ያለው ሁኔታ ከቀጠለ ነገ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንደሚገባ ግልጽ ነው" አቦይ ስብሃት

አቶ ናትናኤል ስብሰባውን ለማካሄድም ፍቃድ አግኝተው በወረዳ 06 ግቢ ውስጥ የሚገኝ አዳራሽ መጠቀማቸውን ይናገራሉ።

"እኛ ማሳወቅ የነበረብንን ሰዎች አሳውቀን ነው አዳራሹን የተከራየነው፤ ለፖሊስም ቀደም ብለን አሳውቀን ነበር። ማድረግ ያለብንን አድርገናል" ይላሉ።

ወጣቶቹ ስብሰባው አይካሄድም ያሉበትን ምክንያት ምን እንደሆነ የተጠየቁት የህዝብ ግነኙነት ኃላፊው፤ 'እንዲሁ በደፈናው እዚህ ስብሰባ አታደርጉም' የሚል ምክንያት እንጂ ዝርዝር ነገር አለመናገራቸውን ያስረዳሉ።

ስብሰባው እንዳይካሄድ ያስተጓጎሉት ወጣቶች አዳራሹ ላይ የነበሩ ባነሮችን እና ሰንደቅ አላማዎችን እንዳወረዱ እና የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ በቦታው ደርሶ ወጣቶቹን ገለል ስላደረገ ስብሰበባው መካሄዱን ይገልፃሉ።

ወጣቶቹ ቁጥራቸው 20 ይሆናል የሚሉት ኃላፊው፤ የፓርቲው አባል ያልሆኑ እና በአካባቢው የሚታወቁ ሰዎች እንዳልሆኑ በአካባቢው አባል የሆኑ ሰዎች እንዳረጋገጡላቸው ገልፀው፤ "ሌላውን ሥራ ለፖሊስ ትተናል" ብለዋል።

በዕለቱ በሌሎች ወረዳዎች የተካሄዱት የኢዜማ ስብሰባዎች ችግር ሳያጋጥማቸው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በንፋስ ስልክ የነበረውም ውይይት መጀመሪያ ላይ ቢስተጓጎልም በመጨረሻ መካሄዱን የህዝብ ግነኙነት ኃላፊው አክለዋል።

አቶ ናትናኤል በተፈጠረው ችግር በሰው አካል ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስረድተዋል።

በተያያዘ ትናንት በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 09 ልዩ ስሙ ኮዬ ፈጨ ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ የአማራ ወጣቶች ማኅበር አባላት ሲያደርጉት የነበረው ስብሰባ በሌሎች ወጣቶች እንዲበተን መደረጉ ተነግሯል።

ከስብሰባው አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆነው በለጠ ተገኘ ለቢቢሲ ሲናገር፤ ስብሰባው የአማራ ወጣቶች ማህበር ሪፖርት መስማትና የጠቅላይ ሚንስትሩን የሰላም የኖቤል ሽልማት በማስመልከት ደስታ ለመግለጽ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ እንደነበር ይገልጻል።

ስብሰባውን በማገባደድ ላይ እያሉ ከቀኑ 6፡30 አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ወጣቶች መጥተው የግቢውን ዘበኛ ጥሰው በማለፍ "እኛ ወደ ተሰበሳብንበት አራተኛ ፎቅ መውጣት ጀመሩ" የሚለው ወጣት በለጠ፤ ደረጃው ላይ የስብሰባው ተሳታፊ ወጣቶች እንዲያግዷቸው መደረጉን ይገልጻል።

በተሰብሳቢዎቹና ከውጭ በመጡት ሰዎች መካከል በተፈጠረ ፍጥጫ ለመውጣትም አስቸጋሪ በመሆኑ "ጠዋት አንድ ሰዓት እንደገባን ቁርስም ምሳም ሳንበላ እስከ ከሰዓት ድረስ እዚያው ታግተን ለመዋል ተገደናል" ይላል።

ከታች ሆነው ድንጋይ ሲወረውሩባቸው እንደቆየ የገለጸው በለጠ፤ የሚወረወረው ድንጋይ የህንጻውን መስኮት መሰባበሩን ተናግሯል።

ግቢው ውስጥ ህጻናት የያዙ እናቶችና በተሽከርካሪ ወንበር [ዊልቸር] የሚሄዱ ሰዎች ስለነበሩ እነሱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በማሰብ ቀሪዎቹ ወጣቶች የሚደርስባቸውን ጥቃት መከላከላቸውን ተናግሯል።

ፖሊስ ነገሮችን ካረጋጋ በኋላ 'ኤፍኤስአር' የጭነት መኪና እና ከኋላው ክፍት በሆነ ፒክ አፕ ተሽከርካሪዎች እየታገዘ ተሰብሳቢዎችን ከስፍራው ማስወጣቱን በለጠ ይናገራል።

"ስብሰባው ሕጋዊ ነው፤ ለስብሰባውም ፍቃድ አለን"ሲል በለጠ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጠን የፌደራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ እና ችግር ተፈጥሮባቸዋል በተባሉ የክፍለ ከተማ ፖሊስ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።

ዛሬም ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የጸጥታ መደፍረስ አጋጥሞ የጸጥታ አስከባሪዎች በቦታው ተሰማርተው እንደነበረ እና አምቡላንሶችም በሥፍራው በስፋት መታየታቸውን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ለመጠየቅ የምናደርገው ጥረት ይቀጥላል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ