#3 እሷ ማናት?፡ ማየትና መስማት የተሳናት የመብት ተሟጋችና የሕግ ባለሞያዋ ሃበን ግርማ

የመብት ተሟጋችና የሕግ ባለሞያ ሃበን ግርማ
አጭር የምስል መግለጫ "አታድግም፣ መማር፣ መስራት አትችልም፤ አታገባም የሚሉኝ ብዙ ሰዎች ነበሩ"

ዛሬም ድረስ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ከሌለባቸው እኩል ተምረው የሚያድጉ፣ ሠርተው የሚቀየሩ የማይመስላቸው አይታጡም። ከዚህ የማህበረሰብ ጎምቱ አመለካከት ጋር ታግለው፣ የእለት ኑሯቸውን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለሌላው አርአያ የሆኑ በርካታ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎችም አሉ።

ከሩቅ ዘመን ሔለን ኬለርን ብንጠቅስ ከቅርብ ደግሞ ሊ ሪድሊይ እማኛችን ነው። የኛዋን የትነበርሽ ንጉሤንም ሳንረሳ ማለት ነው።

'ሎስት ቮይስ' በሚል የሚታውቀው እንግሊዛዊው ሊ ሪድሊይ ለ39 ዓመታት ድምፅ ያልነበረው ኮሜዲያን ነው።

ሰዎች ለአካል ጉዳት ያላቸውን አመለካከትና አገላለፅ ለማረም ሊ፣ እ.ኤ.አ በ2018 በተካሄደው ታዋቂው ልዩ የክህሎት ውድድር 'ብሪቴይን ጋት-ታለንት' ላይ የራሱ አካላዊ ጉዳትን እያነሳ በመቀለድ አሸንፏል።

የኢትዩጵያውያን አካል ጉዳተኞች ፈተናዎች ምን ድረስ?

ኢትዮጵያዊው የ100 ሜትር ክብረወሰን ባለቤት

ይህ መናገር የማይችለው፣ ነገር ግን በሳቅ ጎርፍ የሚያጥለቀልቀው ኮሜዲያን፣ በጋዜጠኝነት ሁለት ዲግሪ ሲኖረው ለቢቢሲ እና ለሌሎች የሃገሪቷ ጋዜጦች በመሥራትም በርካታ ሽልማቶች የተጎናፀፈ ነው።

ለዛሬው የእሷ ማናት ዝግጅታችን የመረጥናት ሐበንም አካል ጉዳት ሞራሏን ሳይበግረው፣ ለራሷም ለሌሎችም አርዓያ መሆን የቻለች ግለሰብ ናት።

ሌላኛዋ ሄለን ኬለር

ስወለድ ጀምሮ የመስማትም ሆነ የማየትም ችግር አብሮኝ ነበር የተወለደው። ለሆነ ነገር 'ገደብ' በማስቀመጥ አላምንም፤ 31 ዓመቴ ነው። ሐበን ግርማ እባላለሁ።

ሁሌም አካላዊ ጉዳት ያላቸው ሰዎች መሥራት የሚችሉት ነገር የተገደበ ነው የሚሉ አስተሳሰቦችን ስታገል ኖሬያለሁ፤ አሁንም በዚሁ የትግል ሜዳ ውስጥ ነኝ።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ። በዚህም በዩኒቨርስቲው ታሪክ የመጀመሪያዋ ማየትና መስማት የተሳናት የሕግ ምሩቅ ሆኛለሁ።

በ2019 ደግሞ ''The Deaf blind Woman who Conquered Harvard Law'' የሚል መጽሐፍ ለንባብ አብቅቻለሁ።

ይህን መጽሀፍ በስሜ የተሰየመ ሲሆን፣ የህይወት ተሞኩሮዬን፤ ውጣ ውረዴንና ስኬቴን ያሰፈርኩበት ነው።

በእራስ ውስጥ ሌሎችን ማየት

በመላው ዓለም እየዞርኩ 'የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች፣ እኩል ተደራሽና ተጠቃሚ መሆን አለባቸው' የሚል ዘመቻ የማደርግ ሲሆን፣ ለዚህ የአካል ጉዳተኞች መብት እንዲከበር ለማደርገው ጥረት ዓለማችን መሪዎችና የተለያዩ አካሎች የማበረታቻ ቃላቸውን፣ እውቅናና አድናቆታቸውን ሰጥተውኝ ያውቃሉ።

ከእነዚህም መካከል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማና ቢል ክሊንተን፣ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ይገኙበታል።

ተወልጄ ያደግኩት በኦክላንድ ካሊፎርኒያ ነው። እናትና አባቴ ግን ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ናቸው።

መጀመሪያ ላይ በትንሹም ቢሆን ማየትና መስማት እችል ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ዓይኖቼም ሆኑ ጆሮዎቼ የማየትና የመስማት አቅማቸው እየደከመ በመምጣቱ በመሳሪያ በመታገዝ ወደ መግባባት ተሸጋግሬያለሁ።

አሁን ድምጽ ቀድቶ በሚይዝ መሣሪያ በመናገር ከሰዎች ጋር እግባባለሁ።

የፈለግኩትን ማይል ብጓዝ የማይለየኝ ማይሎ ነው፤ ማይሎ ውሻዬ ነው፤ የቀኝ እጄ!

"ዓለምን እዞራለሁ። ማይሎ የሚባል የሦስት ዓመት ዕድሜ ያለው የ'ጀርመን ሼፐርድ' ዝርያ ያለው ውሻዬ፣ እኔን መንገድ መምራት የሚያስችለው የሁለት ዓመት ትምህርት ተሰጥቶታል። አሁን ሁሉንም ነገር ማየት የሚችል ውሻ አለኝ። ደረጃዎች ላይ መቆም፣ አስቸጋሪ ቦታዎችን መለየት፣ መሻገሪያ መንገድ ስንደርስ መቆም እና ሌሎችንም ክህሎቶች ተምሯል። ሁለታችን አብረን እንጓዛለን፤ በአውሮፕላን ይሁን በእግር ጉዟችን አንድ ላይ ነው። ማይሎ ድንቅ የመንገድ መሪ ነው።"

ዐይነ ስውሩ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ሕንፃ ከሰባተኛ ፎቅ የአሳንሰር ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ሞተ

በመጪው ጊዜ በመላው ዓለም ላይ ላሉ 1.3 ቢሊየን የአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሚሆን የመኪና ቴክኖሎጂ ቢፈበረክ ምኞቴ ነው። ምክንያቴ ደግሞ የአካል ጉዳተኞች እኩል ዕድል አግኝተው በነፃነት እንዲማሩ፣ እንዲሠሩና እንዲንቀሳቀሱ የሚፈጥረው ፀጋ በቀላሉ የሚታይ ስላልሆነ ነው።

መደነስ፣ ብስክሌት መጋለብ፣ ተራራ መውጣት እና ሌሎች የአካል እንቅስቃሴዎችን አደርጋለሁ።

አጭር የምስል መግለጫ የፈለግኩትን ማይል ብጓዝ የማይለየኝ ማይሎ ነው፤ ማይሎ ውሻዬ ነው፤ የቀኝ እጄ!

ብዙ ቤተሰቦችም ሆኑ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ከሌላኛው የሕብረሰተብ ክፍል ያነሱ ወይም የተለዩ መሆናቸው እንዳይሰማቸው አሊያም ወላጆቻቸው እንዳያፍሩባቸው ችግራቸውን ይደብቃሉ፤ ይደበቃሉም።

"እኔም በዚህ አልፌያለሁ፤ ከሌሎች ሰዎች የተለየሁ እንደሆንኩኝ እንዳይሰማኝ ያለኝን የአካል ጉዳት የደበቅኩበት ጊዜ ነበር።"

የአካል ጉዳት ማንኛውም ሰው የሕይወት ተግዳሮች እንዳለው እንዲቀበል እንጂ እንዲያፍርበት መሆን የለበትም፤ ተግዳሮቶቹን መቀበል ደግሞ መፍትሄዎች ለማምጣት መሥራት እንዳለብህ እንድታምን ያደርጋል።

"እኔም የአካል ጉዳተኛ መሆኔን ተቀበልኩት። አላይም፣ አልሰማም። ግን ደግሞ ብዙ ክህሎት አለኝ። የአካል ጉዳት አለብህ ማለት ጥንካሬ የለህም ማለት አይደለም"። በመጽሐፌም ውስጥ ማስረጽ የፈለግኩትና ጎልቶ እንዲታይ የፈለግሁት መልዕክት ይህ ነው።

ሐበን ማለት በትግርኛ ኩራት ማለት ነው። ብዙ የአካል ጉዳት ያላቸው ሰዎች ያፍራሉ፣ ችግራቸውንም ይደብቃሉ። በዚህ መጽሐፍ የአካል ጉዳት ኩራት መሆኑን ተቀብለው ያላቸውን ፀጋ ተጠቅመው የተለየ ነገር መሥራት እንደሚችሉ ነው የማስተምረው።

ማየት የሚችሉ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን ተጠቅመው ማንበብ መቻላቸው ለእነሱ የተሰጠ ፀጋ ሲሆን፣ እኔ ብሬይልንና ጣቶቼን በመጠቀም አነባለሁ። ይህ ለእኔ የተሰጠ ፀጋ ስለሆነ ከዓይን ስራ ጋር እኩል ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ 130 አገራትን የጎበኘው ዓይነ ስውር

በኢኮኖሚ ደረጃ የተሻሉ፣ በትምህርትና በሌሎች አገልግሎቶች ተደራሽ የሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ተወልጄ ባድግም የአካል ጉዳትን እንደ ነውር የሚቆጥሩ አንዳንድ ሰዎች ስለማእጠፉ ከባድ የልጅነት ጊዜ አሳልፌያለሁ።

"አታድግም፣ ትምህርት ቤት አትሄድም፣ አትሰራም፣ አታገባም የሚሉኝ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ወላጆቼ እኚህ አስተሳሰቦች ይታገሉ ነበር፣ እኔም እነዚህ መልዕክቶች ሲደርሱኝ መታገል ግድ ይለኝ ነበር።"

የአካል ጉዳት፣ ሰዎች በህይወት ሲኖሩ የሚገጥማቸው ነገር ነው። የአካል ጉዳት 'ሃበን ነው' [ኩራት ነው] በማለት ነው የማምነው።

የአካል ጉዳት ኖሮብን በተለያዩ ውጣ ውረዶች የምናልፍ ሰዎች ሊኖረን የሚገባው አማራጭ፣ ተቀብሎን የሚሄድ ማህበረሰብ ስላለ የአካል ጉዳታችን ልንኮራበት እንጂ ልናፍርበት አይገባም።

"አትዘኑልኝ፤ ሌሎች አማራጮች ተጠቅሜ መንቀሳቀስ እችላለሁ። እኛ ደግሞ ክብር ይገባናል፤ በሁሉም መልኩ ተጠቃሚዎች መሆን አለብን" የሚል ዘመቻ የጀመርኩት ለዚህ ነው።

"የአካል ጉዳት ያለብኝ ሰው ነኝ፤ ሴትም ነኝ። እስከ አሁን በባህላችን፣ ሴት ልጅ ላይ የሚደርስ መድልዎ አለ። በተለይ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርስ 'ኢቦሊዝም' የሚባል መድልዎ አለ። ይህም የአካል ጉዳተኞች፣ ከሌላው የህብረሰተብ ክፍል የበታች ናቸው የሚል አመለካከት ያለ በመሆኑ ነው፤ ልንታገለው ይገባል።"

"ማየት የተሳናቸው ሰዎች ምርጫ የላቸውም የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም፣ ቤተሰቦቼ ጠንክረሽ ስትሰሪ ታሸኒፊያለሽ ብላው ስላሳደጉኝ ትምህርቴን ጠንክሬ ነው የተማርኩት።"

"አካል ጉዳተኛ መሆኔ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል"

ነገር ግን ለእኔ ስራ መስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩ ነበሩ። የዩኒቨርሰቲ ትምህርቴን ካጠናቀኩ በኋላ ስራ መፈለግ ግድ ነበር፤ ግን የትምህርት ማስረጃዬንና ልምዴን የሚገልጽ ወረቀቴን አይተው ለቃለ መጠይቅ የሚጠሩኝ ተቋማት፣ የአካል ጉዳት እንዳለብኝ ሲያዩ 'ስራውን' ለመስጠት አይደፍሩም ነበር።

"ለቃለ መጠይቅ ስቀርብ፡ የአካል ጉዳተኛ መሆኔን ሲያውቁ ይቅርታ ይሉኛል። ስራውን ሊሰጡኝ ፍቃደኞች አይሆኑም። የአካል ጉዳተኞች ይህንን ስራ መስራት አይችሉም የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ። ብዙ ተቋማት ስራ መስራት እንደማልችል በማሰብ ብዙ እድል ነፍገውኛል"

Image copyright Getty Images

ማንኛውም ዓይነት የአካል ጉዳት ያለበት ሰው፣ በተለይ ደግሞ ማየት የተሳነው ከሆነ፣ ሌሎች ክህሎቶችን ለማሳደግ መንገድ የሚከፍት ስለሆነ፣ 'የቤት ስራ' ተብለው የሚወሰዱ ስራዎች ተምሮ ማደግ አለበት።

ሴቶች አቅማቸው በማሳደግ በህይወታቸው ብዙ አማራጮች እንዳሉ መገንዘብ አለባቸው። አካል ጉዳተኛ ሴቶች ደግሞ፣ ልዩ ክህሎታቸውን ማዳበር ላይ ትኩረት መስጠት አለባቸው።

የሴቶች ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ጾታዊ መድልዎ አሁንም ትልቁ ፈተና ነው። ሁል ግዜ መሰናክል ሆኖ የሚቀጥል ጉዳይ በመሆኑ አሁን የምናደርገው ትግል ለመጪው ትውልድ ሊያግዝ ይችላል።

"እኔ ራሴን፣ ልዩ ነሽ፤ ልዩ ፍጡር ለመሆን አትፈሪ እላታለሁ። አብዛኛዎቻችን ልዩ የሆንንበት ምክንያት ለመደበቅ ስለ ምንሞክር፡ ልዩነታችን ደብቀን ለመመሳሰል እንፈልጋለን። ይህ ልክ አይደለም፤ ራሴን መምሰል ነው የምፈለገው። የአካል ጉዳት ያለባችሁ ከሆናችሁም ኩራት ነውና አክብሩት።"

እሷ ማናት? የሚለው ጥንቅራችን ያሰቡበትን ዓላማ ለማሳካት ብዙ ውጣውረዶችን ያሳለፉ ሴቶችን ታሪክ የምናስቃኝበት ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ