ካንሰር እንዴት እንደተፈጠረ ለማወቅ የሚተጉት ተመራማሪዎች

የጡት ካንሰር ህዋስ Image copyright Francis Crick Institute

እንግሊዛዊያን እና አሜሪካዊያን ሳይንቲስቶች ካንሰር እንዴት እንደተፈጠረ ለማወቅ ሌት ከቀን እየተጉ ነው።

'ዋናው መድኃኒቱ መገኘቱ ነው እንጂ እንዴት እንደተፈጠረ ቢታወቅ ምን ዋጋ አለው?' ይሉ ይሆናል። የተመራማሪዎቹ ዓላማም ከዚህ የራቀ አይደለም። በሽታውን ከምንጩ ማድረቅ።

"ወንዶች በጡት ካንሠር እንደሚያዙ አላውቅም ነበር"

ከማህጸን ስለሚወጣ ፈሳሽ ምን ያህል ያውቃሉ?

ተመራማሪዎቹ እየታገሉ ያሉት 'ካንሰርን ለመፍጠር' ነው። ካንሰር ከተወለደ ጀምሮ እንዴት አድጎ እዚህ ሊደርስ ቻለ? የሚለውን ጥያቄ ለመፍታት።

ታድያ ውጤቱ ያማረ ከሆነ መድኃኒቱን ለማግኘት አይከብድም ነው ሳንይንቲስቶቹ የሚሉት።

ካምብሪጅ፣ ማንቸስተር፣ ሎንዶን እና ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲዎች ተባብረው 'ካንሰርን እንደገና ካልፈጠርነው' ብለዋል። አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ እና ልምድ ለመካፈልም ተማምለዋል [ወረቀት ላይ በሰፈረ ሰነድ]።

ቀድሞ የነበረ

የካንሰር በሽተኞችን ደም፣ ትንፋሽ እና የሽንት ናሙናዎችን ተጠቅመው ነው ሳይንቲስቶቹ የካንሰርን ዳግም ውልደት እውን ለማድረግ ቆርጠው የተነሱት።

'ግመልን በመርፌ ቀዳዳ እንደማሾለክ ነው' ይሉታል የምርምሩን ክብደት ሲገልፁት። 30 ዓመታት ሊፈጅብንም ይችላል ባይ ናቸው።

ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዴቪድ ክሮስቢ «ትልቁ ችግር ካንሰር በሰውነታችን ውስጥ እንዴት እንደሚፈጠር ማወቅ አለመቻላችን ነው» ይላሉ። «ካንሰር ሰውነታችን ውስጥ አለ ማለት ተወልዷል ማለት ነው። ቀድሞ የነበረ ነው።»

Image copyright Patrick Harrison, Cancer Research UK

እንግሊዝ የሚገኙት ተመራማሪዎች ለምሳሌ የጡት ሥርን [breast tissue] ቤተ-ሙከራ ወስጥ አብቅለው የጡት ካንሰር እንዴት እንደሚከሰት ለማየት ጥረት እያደረጉ ነው።

ጥናቱ ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው። ተመራማሪዎቹ የካንሰር ተጠቂዎችን ዘረ-መል እና አስተዳደግ ሁሉ ማጥናት ግድ ይላቸዋል።

ውዱ ጥናት

እርግጥ ነው ይህ ጥናት የካንሰርን ውልደት ለመድገም የተደረገ የመጀመሪያው ጥናት አይደለም። ነገር ግን ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶች የገንዘብ እና የሰው ኃይል አቅማቸው የተዳከመ ነበር።

ኦ/ር ክሮስቢ የተለያዩ አገራት የሚገኙ ተመራማሪዎች ተባብረው መሥራታቸው ምናልባትም አንዳች ዓይነት ውጤት ቢመጣ ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት ያግዛል ይላሉ።

ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የጡት ካንሰር ተጠቂ ከሆኑ ሰዎች መካከል 89 በመቶ የሚሆኑት በሽታው ደረጃ አንድ ላይ እያለ ከታወቀ ለአምስት ዓመታት እና ከዚያ በላይ ይኖራሉ። ደረጃ 4 ላይ ደረሰ ማለት ግን የመኖር ተስፋቸው ወደ 26 በመቶ ቀነሰ ማለት ነው።

የዘር ከረጢት ካንሰር ከአባት ጅን ጋር የተያያዘ ነው

ኤምአርአይ ምንድነው?

አሁን ባለው መረጃ 44 በመቶ የጡት ካንሰር ተጠቂዎች ናቸው በሽታው ሳይጠና [ደረጃ 1 ሳለ] ምርመራ የሚደርግላቸው። አንዳንድ አገራት በሽታው ገና እንጭጭ እያለ መመርመር የሚቻልበት ቴክኖሎጂ የላቸውም።

ከጡት ካንሰር በዘለለ የጉበት፣ ሳንባ፣ የአንጀት፣ እና ፕሮስቴት [ከወንድ ልጅ ብልት እና የሽንት ከረጢት መሃል የሚገኝ እጢ] ካንሰር ዓይነቶች ሰውነት ውስጥ ብዙም ሳያድጉ የማወቂያው መንገድ አስተማማኝ አይደለም።

ፕሮፌሰር ማርክ ኤምበርተን ፕሮስቴት ካንሰርን ለመመርመር ከመርፌ እና መሰል መመርመሪያቸው ይልቅ ኤምአርአይን ጥቅም ላይ ማዋል መጀመሩ እመርታ ነው ይላሉ።

ይህንን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የካንሰርን ውልደት መመርመር ይቻል እንደሁም ተመራማሪዎቹ እያጠኑ ነው።

ይህ የካንሰር ምርምር ወጪው ከበድ ያለ ነው። የእንግሊዙ ካንሰር ምርምር ጣቢያ ለዚህ ምርምር ይሆን ዘንድ 50 ሚሊዮን ዶላር አዋጥቷል። ሌሎችም እንዲሁ በማድረግ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ጥናቱን ከግብ ለማድረስ ደፋ ቀና እያሉ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ