ወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒና ለመዋጥ ዝግጁ ናቸውን?

Contraceptive pill packets Image copyright Getty Images

ሳይንቲስቶች ለወንዶች የተስማማ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒና ለመፈበረክ ደፋ ቀና ማለት ከጀመሩ ግምሽ ክፍለ ዘመን አለፋቸው።

ምንም እንኳ በጀ የሚያስብሉ ዜናዎች በአለፋ ገደም ቢሰሙም በቀላሉ መድኃኒት ቤት መደርደሪያው ላይ የምናገኘው ክኒና መፈብረክ ግን አልቀለለም።

የፈንድ እጥረት እና የወንዶች ክኒናውን ለመውሰድ ብዙም ፈቃደኛ ሆኖ አለመገኘት መድኃኒቱ በቶሎ እንዳይመረት እንቅፋት ሆነዋል።

ጥናቶች ግን ይህንን ይጠቁማሉ፡ ክኒናው ለገበያ ቢውል ለመዋጥ የተዘጋጁ በርካታ ወንዶች አሉ።

ለምሳሌ እንግሊዝ ውስጥ ከሚገኙ ወንዶች [ወሲብ ማድረግ ከሚችሉ] አንድ ሶስተኛ የሚሆኑቱ አማራጭ የወሊድ መቆጣጠሪያ ከተገኘ ለመውሰድ ምን ገዶን? ሲሉ ለተሰጣቸው መጠይቅ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን መጠቀም ሴቶችና ወንዶች በእኩሌታ ሊጋሩት የሚገባ ኃላፊነት ነው ብለው ያምናሉ።

ወደ አሜሪካ ስናቀና መጠይቁን ከሞሉ ወንዶች [ወሲብ መፈፀም የሚችሉ እና ዕድሜያቸው ከ18-44 የሆነ] መካከል 77 በመቶ የሚሆኑት የወንድ ወሊድ መቆጣጠሪያን ከመሞከር እንደማይቦዝኑ አሳውቀዋል።

የወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒናውን ለመዋጥ ዝግጁ መሆን ምናልባት በስተመጨረሻ የወንዶች ወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒት ፋርማሲ እንዲገባ አብረታች ምክንያት ይሆን?

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አሁን ወንዶች በዋናነት የሚጠቀሟቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶች ሁለት ናቸው፡ ኮንደም እና የዘር ቱቦን መቁረጥ

ተመራጩ የወሊድ መቆጣጠሪያ

የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው አንድ መረጃ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ መውለድ ከሚችሉ ጥንዶች 3/4ኛ የሚሆኑት የወሊድ መቆጣጠሪያ በፍፁም አይጠቀሙም ይላል።

ያም ሆኖ እጅግ በብዛት የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚወስዱት ሴቶች መሆናቸውን ጥናቱ ያክላል።

ትዳር ወይንም ግንኙነት ውስጥ ካሉ ሴቶች 19 በመቶዎቹ የዘር ቱቦን ማስቋጠር፣ 14 በመቶ ቆዳ ውስጥ የሚቀበር፣ 9 በመቶ የሚዋጡ ክኒናዎችን እንዲሁም 5 በመቶዎቹ ደግሞ መርፌን ይመርጣሉ።

የወንድ የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚባሉት በዋነኝነት ሁለት ናቸው፤ ኮንደም እና የዘር ቱቦን ማስቆረጥ። 8 በመቶ ኮንደም ሲጠቀሙ፤ 2 በመቶ ብቻ የዘር ቱቦ ማስቆረጥን ይመርጣሉ።

የሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒት በገፍ መመረት የጀመረው በ1960ዎቹ ነበር።

ዛሬ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ኪኒና ይውጣሉ። ይህ መድኃኒት በአውሮጳ፣ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ አንደኛ ተመራጭ የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ ነው። በአፍሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና ሰሜን አሜሪካ ሁለተኛ በእስያ ደግሞ ሶስተኛው ተመራጭ መንገድ ነው።

መድኃኒቱ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ብርቱ ፈጠራዎች አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል። ለሴቶች መብት ትልቅ አበርክቶ አድርጓል ተብሎም ይታመናል። ሴቶች ከወንድ አጋራቸው ጫና ተላቀው በራሳቸው ሕይወት ራሳቸው እንዲወስኑ አስችሏል ይባልለታል።

ነገር ግን የፆታ እኩልነት ከቀን ቀን ለውጥ እያሳየ ቢመጣም የወሊድ መቆጣጠሪያ እና ወንዶች ብዙም ያለመቀራረባቸው ነገር አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የወንድ ልጅ ዘር [ስፐርም] ፍሬ ጎልቶ ሲታይ

ወሊድ መቆጣጠሪያ ለወንዶች መሥራት ከባድ ነው?

የወሊድ መቆጣጠሪያ ለሴቶች አምርቶ መሸጥ የወሰደው ጊዜ 10 ዓመት ገደማ ነው። እና ለምን ይሆን ለወንዶች የሚሆን የወሊድ መቆጣጠሪያ ሠርቶ መሸጥ እንዲህ የከበደው?

አንዳንድ ሳይንቲስቶች የወሊድ መቆጣጠሪያዎችን ለወንዶች እንዲሆን አድርጎ ማምረት እንደ ሴቶቹ ቀላል አይደለም ይላሉ።

ወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያ የዘር ፍሬን [ስፐርም] በመቆጣጠር ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ከሴቶች በላቀ ውስብስብ እና የጎንዮሽ ጉዳት ያለው ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ለወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያን ለመሥራት ሙከራ ማድረግ የተጀመረው የሴቶቹ ከተፈበረከ ዓመታት በኋላ መሆኑ አንሶ ሙከራው በገንዘብ እጥረት ብዙ ጊዜ ይቋረጣል። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ፋርማሲዎች፣ ተቆጣጣሪዎች እና ወንዶች ራሳቸው ለክኒናው ያላቸው አሉታዊ አመለካከት ነው።

ተያያዥ ርዕሶች