ዩናይትድ ኪንግደም አቋርጣ የነበረውን ወደ ግብፁ ሻርማ ኤል-ሼኽ የሚደረግ በረራ ልታስጀምር ነው

Sharm el-Sheikh Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሻርማ ኤል-ሼኽ በእንግሊዛውያን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የመዝናኛ ስፍራ ስለመሆኑ በስፋት ይነገራል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እ.አ.አ. 2015 አውሮፕላን ላይ የሽብር ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ወደ ሻርማ ኤል-ሼኽ የሚደረግ የቀጥታ በረራን ከልክሎ ቆይቶ ነበር።

የሩሲያው አየር መንገድ ኮግለማቪያ በኤርባስ አውሮፕላኑ 224 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ሩሲያ ለመብረር ከመዝናኛ ስፍራው ሻርማ ኤል-ሼኽ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አየር ላይ ጋይቶ ሁሉም ተሳፋሪዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ጽንፈኛው እስላማዊው ቡድን አይኤስ ለሽብር ጥቃቱ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ብሎም ነበር።

ከሽብር ጥቃቱ በኋላ የግብፅ ባለስልጣናት አየር ማረፊያው በደህንነት ረገድ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ እንዳልነበር አምነዋል።

የግብፅ ባለስልጣናት በአሁኑ ወቅት በአየር ማረፊያዎች የደህነንት ደረጃ ማሻሻላቸውን እየተናገሩ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም ትራንስፖርት ጸሃፊ ግራት ሻፕስ "የዜጎቻችን ደህንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። ይህ ውሳኔ የተደረሰው ከበረራ ደህንነት ባለሙያዎች እና ከግብፅ ባለስልጣናት የተደረገውን ውይይት ተከትሎ ነው" ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት "አሁንም በግብፅጽ በበረራዎች ላይ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል" ሲል ለዜጎች የጉዞ ማስጠንቀቂያን አውጥቷል።

ከግብፅ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በሚደረጉ በረራዎች ላይ ተጨማሪ የደህንነት ምረመራዎች ይደረጋሉም ተብሏል።

ሻርማ ኤል-ሼኽ በቀይ ባህር እና በሲናይ ሰርጥ መካከል የምትገኝ የግብጽ ከተማ ስትሆን፤ የእረፍት ጊዜያቸውን ማሳለፍ ለሚሹ ሰዎች ቅንጡ የሆኑ የባህር ዳርቻ ሪዞርቶችን ጀባ ትላለች።

በግብፅ እና በዩናትድ ኪንግደም የሚገኙ የጉዞ ወኪሎች ወደ ሻርማ ኤል-ሼኽ ቀጥታ በረራ እንደሚጀመር መወሰኑን ተከትሎ ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

ኢዚጄት በረራው መጀመሩን በማስመልከት "ያሉትን አማራጮች እናጤናለን" ያለ ሲሆን አብታ የተሰኘው የንግድ ድርጅት በበኩሉ "ይህ መልካም ዜና ነው" ሲል ውሳኔውን በደስታ ተቀብሎታል።

ሻርማ ኤል-ሼኽ በእንግሊዛውያን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የመዝናኛ ስፍራ ስለመሆኑ በስፋት ይነገራል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጪ ጉዳይ ቢሮ እንደሚለው ከሆነ እ.አ.አ. 2015 ላይ ብቻ 900 ሺህ የሚሆኑ ዜጎቹ ይህችን የመዝናኛ ከተማ ጎብኝተዋል።

ወደ ሻርማ ኤል-ሼኽ የሚደረገው በረራ መከልከሉን ተከትሎ በቀጣዩ ዓመት የሪዞርት ከተማዋን የጎበኙ ዜጎች ቁጥር ወደ 230ሺህ ዝቅ ብሎ ነበር።

Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ አየር ላይ እንዳለ በቦንብ እንዲጋይ በተደረገው አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት 224 ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ጎብኚዎች ነበሩ።

አየር ላይ እንዳለ በቦንብ እንዲጋይ በተደረገው አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት 224 ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ጎብኚዎች ነበሩ። 219 የሩሲያ ዜጎች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል 17ቱ ህጻናት ነበሩ።

የዩናትድ ኪንግደም የበረራ ደህንነት መርማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ወደ አውሮፕላኑ ለመጠጋት ፍቃድ የነበረው ሰው አውሮፕላኑ ከመነሳቱ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት እቃ መጫኛው ውስጥ በቦርሳ አድርጎ ተቀጣጣይ ነገር አስቀምጧል።