'የሰው ግደሉልኝ ቅጥር' አንዱ ለሌላኛው ያስተላለፉት 5 'ገዳዮች' በቁጥጥር ሥር ዋሉ

The six defendants in court in Nanning Image copyright Nanning Intermediate People's Court

በጉዋንዢ ቻይና፤ የተሰጣቸውን 'የሰው ግደሉልኝ ቅጥር' አንዱ ለሌላኛው ያስተላለፉ 5 ቅጥረኛ ገዳዮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

ጉዳዩ ይሆነው እንዲ ነው፤ እ.አ.አ. 2013 ላይ በሁለት ተፎካካሪ ነጋዴዎች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል። እኚህ ነጋዴዎች ዊህ እና ታን ይባላሉ። ዊህ አለመግባባቱ በሕግ እንዲፈታ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይወስዱታል።

በዚህ የተበሳጩት ታን የንግድ ተፎካካሪያቸውን ዊህን ለማስገደል ይወስናሉ። ከዚያም ዢ ጉዋንጋን የሚባል ቅጥረኛ ገዳይ ይቀጥራሉ።

ዢ ጉዋንጋን በ282,000 የአሜሪካ ዶላር ክፍያ ዊህን ለመግደል ይስማማል።

ዢ ጉዋንጋን 'ሥራውን' ከመፈጸም ይልቅ ቀጣሪው ሳያውቁ በድብቅ ሞ ቲአንዢንግ የተባለ ሌላ ገዳይ ይቀጥራል። ዢ ጉዋንጋን ለቀጠረው ገዳይ 141,000 የአሜሪካ ዶላር እንደሚከፍለውም ተስማማ።

ሞ ቲአንዢንግ የተባለው ገዳይ በበኩሉ ከቀጣሪው እውቅና ውጪ እንደገና ሌላ ያንግ ካንግሼንግ የተባለ ገዳይ ይቀጥራል፤ 'ለሥራው' 110,000 የአሜሪካ ዶላር እንደሚከፍለው በማስማማት።

ያንግ ካንግሼንግ እንደገና ሌላ ያንግ ጉዓንሼንግ የተባለ ገዳይ ነጋዴውን ዊህን እንዲገድል በ100,000 የአሜሪካ ዶላር ቀጠረ።

ያንግ ጉዓንሼንግ የተባለው ቅጥረኛ ገዳይ በተራው አምስተኛ ገዳይ የሆነውን ሊንግ ዢአንሲ በ14,000 የአሜሪካን ዶላር ይቀጥራል።

አምስተኛው ቅጥረኛ፤ ሊንግ ዢአንሲ ነጋዴውን ከመግደል ይልቅ በአንድ ካፍቴሪያ ከቀጠራቸው በኋላ በእርሳቸው ላይ የግድያ ትዕዛዝ መውጣቱን እና የተገደሉ በማስመሰል የግድያ ትዕዛዙን እንዲያመልጡ ሃሳብ ያቀርባል።

ነጋዴው በሃሳቡ ቀድመው ቢስማሙም ዘግይተው ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጋቸውን የፖሊዝ መዝገብ ያትታል።

ጥፋተኛ ናቸው የተባሉት የስድስቱ ግለሰቦች ጉዳይ የፍርድ ሂደት ሲታይ ቆይቶ የፍርድ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

በዚህም ነጋዴው እንዲገደሉ ገዳይ የቀጠሩት ነጋዴው ታን አምስት ዓመት የተፈረደባቸው ሲሆን፤ የመጀመሪያው ገዳይ ቅጥረኛ 3 ዓመት ከ6 ወር በእስር እንዲያሳልፍ ተፍዶበታል።

ሁለተኛው እና ሶስተኛው ገዳይ ቅጥረኞች እያንዳንዳቸው 3 ዓመት ከ3 ወር የተፈረደባቸው ሲሆን አራተኛው 3 ዓመት እንዲሁም የመጨረሻው 2 ዓመት ከ7ወር እስራት ተፈርዶበታል።