በዓለማችን የተበራከቱት የተቃውሞ ሰልፎች የሚያመሳስላቸው ነገር ይኖር ይሆን?

የተቃውሞ ሰልፈኞች Image copyright AFP/Getty/Reuters

በቅርብ ሳምንታት ከሌባኖስ እስከ ስፔን፣ ከቺሊ እስከ ግብጽ ድረስ ብዙዎችን ያሳተፉ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። ሁሉም የተለያዩ የሚመስሉ ጥያቄዎች ነው የሚያነሱት። ነገር ግን ሁሉንም የሚያመሳስሏቸው የጋራ ጉዳዮች አሉ።

እነዚህን ጉዳዮች በአራት ዋና ዋና ነጥቦች መክፈል ይቻላል።

ፍትሃዊነት

በዚህ በኩል ያሉ የተቃዋሚ ሰልፈኞች የሃገራቸው ሃብቶች በእኩል መንገድ እየተከፋፈሉ አይደለም ብለው የሚያስቡና ወሳኝ አገልግሎቶች ዋጋ መጨመሩን የሚቃወሙ ናቸው።

የደቡብ ኮርያ ፖለቲከኞች ለምን ጸጉራቸውን በአደባባይ ይላጫሉ?

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ ትናንት እና ዛሬ

ለዚህ ቀዳሚ ምሳሌ ደግሞ ኢኳዶር ናት። በያዝነው ጥቅምት ወር የተጀመረው ተቃውሞ መነሻው መንግስት ከዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር ለማግኘት ሲል የነዳጅ ዋጋ ላይ ያደርገው የነበረውን ድጎማ እንደሚያቆም ማስታወቁ ነበር።

ውሳኔው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምርና ከዜጎች አቅም በላይ እንዲሆን አድርጎታል።

አንዳንድ ዜጎች የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ የመጓጓዣ አገልግሎቶች ላይ ጭማሪ ስለሚያስከትልና ተያይዞ ደግሞ የምግብ ዋጋም እንዲንር ስለሚያደረግ ዋነኛ ተጎጂ የሚሆኑት አነስተኛ ገቢ ያላቸው ኢኳዶራውያን የሚኖሩባቸው የገጠር ክፍሎች ናቸው ሲሉም ተከራክረዋል።

የተቃውሞ ሰልፈኞችም ዋና ዋና መንገዶችን ዘግተዋል፣ የሃገሪቱን ፓርላማ ወርረዋል እንዲሁም ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል። ሰልፈኞቹ ባደረጉት ተከታታይ ተቃውሞ መንግስት ውሳኔውን ቀልብሶ የነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገውን ድጎማ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

Image copyright Reuters

በዚሁ ዙሪያ የምትነሳዋ ሌላና ሃገር ደግሞ ቺሊ ናት። የመጓጓዣ ክፍያዎች በእጅጉ መጨመራቸው ያማረራቸው ቺሊያውያን በዋና ዋና መንገዶች በመውጣት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

ምንም እንኳን መንግስት የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችና የባቡር አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረግኩት ለኃይል ማመንጨት የማወጣው ወጪ ከፍ በማለቱና የሃገሪቱ ምንዛሪ ደካማ በመሆኑ ነው ቢልም ዜጎች ግን ደሃውን ለመጫን ተብሎ የተደረገ ነው ሲሉ ብሶታቸውን አደባባይ ወጥተው ገልጸዋል።

ቺሊ በላቲን አሜሪካ ሃብታም ከሚባሉት ሃገራት ብትመደብም ከፍተኛ ኢፍትሃዊነት እንደተንሰራፋ ይገለጻል።

"ሰልፍ የዜጎች መሰረታዊ መብት ነው" መስፍን ነጋሽ

በመጨረሻ የቺሊ መንግስት ዋጋ ጭማሪውን ትቼዋለው ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ብሎ ለዜጎች መልእክቱን ቢያስተላልፍም እንደውም ሌሎች ብዙ ያልተመለሱልን ጥያቄዎች አሉ በማለት ተቃውሟቸውን ቀጥለውበታል።

ሊባኖስም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎችን አስተናግዳለች። መንግስት በሃገሪቱ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው የማህበራዊ ሚዲያና የጥሪ አገልግሎት የሚሰጠው 'ዋትስአፕ' ላይ ግብር እጥላለሁ ማለቱን ተከትሎ የተጀመረው ተቃውሞ አድጎ ወደ ኢፍትሀዊነት፣ ሙስናና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ከፍ ብሏል።

ሙስና

ሊባኖስ አሁንም በዚህ ምድብ ውስጥ ትገባለች። የተቃውሞ ሰልፈኞች እንደሚሉት ደሃው ዜጋ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በወደቀበት ሰአት መሪዎች የራሳቸውን ሃብት ለማካበት ሲሰሩ ነበር።

ባሳለፍነው ሰኞም የሊባኖስ መንግስት የተቃውሞ ሰልፎቹን ተከትሎ የተለያዩ የጥቅማጥቅም አሰራሮችን ያበጀ ሲሆን የመንግስት ኃላፊዎችን ደሞዝ ለመቀነስም ሃሳብ አቅርቧል።

በኢራቅም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች ተበራክተዋል። ሰልፈኞቹም በሃገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ስርአት ህዝቡን ችግር ውስጥ ከቶታል ሲሉ ተደምጠዋል። ሌላኛው ጥያቄያቸው ደግሞ የመንግስት ሃላፊዎች በእውቀታቸውና በልምዳቸው ሳይሆን በዘርና ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ነው የሚል ነው።

ይህ አሰራር ደግሞ ሃላፊዎቹ የሃገሪቱን ሃብት እንዲበዘብዙና በደሃው ህይወት እንዲቀልዱ በር ከፍቶላቸዋል በማለት ነው ለተቃውሞ አደባባይ መውጣትን የመረጡት።

የአፍሪካዋ ግብጽም የዚሁ ሰለባ ሆናለች። ባሳለፍነው መስከረም ወር የጀመረው የግብጽ ተቃውሞ ከአንድ ባለሃብት ይጀምራል። ሞሀመድ አሊ የተባለው በግዞ ስፔን ውስጥ የሚኖረው ባለሃብት ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲሰ እና የወታደራዊ ሃላፊዎች በሙስና ተዘፍቀዋል ማለቱን ተከትሎ ነው።

Image copyright AFP

ፖለቲካዊ ነጻነት

ከፖለቲካዊ ነጻነት ጋር በተያያዘ ለወራት የቆየው የሆንግ ኮንግ የተቃውሞ ሰልፍ የዓለም መነጋገሪያ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩት እና ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡት ሰልፈኞች ከቻይና ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲያበቃ የሚሹ ናቸው። የቀድሞዋ የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት የሆነችው ሆንግ ኮንግ የቻይና አካል ስትሆን፤ ነዋሪዎቿም የዘረ ሃረጋቸው ከቻይና የሚመዘዝ ይሁን እንጂ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ራሳቸውን እንደ "ቻይናዊ" አይመለከቱም።

በሆንግ ኮንግ ተቃውሞው የተጀመረው በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ከሆንግ ኮንግ ወደ ቻይና ተላልፈው እንዲሰጡ የሚያስችል ሕግ ተግባራዊ ሊደረግ መታሰቡን ተከትሎ ነበር።

ምንም እንኳ ሆንግ ኮንግ የቻይና አካል ብትሆንም፤ የቻይና እና የሆንግ ኮንግ የሕግ ስርዓት የተለያየ ነው። ቻይና በበኩሏ ሌሎች ሃገራት በጉዳዩ ላይ እጃቸውን እንዳያስገቡ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።

በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ረቂቅ ጥፋተኛና አቃቤ ህግ ይደራደራሉ

በስፔኗ ባርሴሎናም የካታላን መሪዎች መታሰራቸውን የተቃወሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተዋል።

የካታላን ግዛት ከስፔን መገንጠል አለባት የሚል ሃሳብ ይዘው የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ፖለቲከኞች ለእስር የተዳረጉት እ.አ.አ. በ 2017 ሲሆን ነዋሪዎቹ የሆንግ ኮንግ የተቀውሞ ሰልፈኞችን አካሄድ ተከትለዋል።

ቦሊቪያ ውስጥ ደግሞ ፕሬዝዳንት ኢቮ ሞራሌስ በድጋሚ በምርጫውን እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው ህዝባዊ ተቃውሞዎች የተጀመሩት።

የአየር ጸባይ ለውጥ

Image copyright Reuters

'ኤክስቲንክሽን ሪቤሊየን ሙቭመንት ' የተባለ በአየር ጸባይ ለውጥ ላይ የሚሰራ ቡድን በብዙ የዓለማችን ከፍሎች የተቃውሞ ሰልፎችን አካሂዷል። መንግስታትም አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ ቀርቧል።

የተቃውሞ ሰልፉ ከተካሄደባቸው ሃገራት መካከል ደግሞ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ ኦስትሪያ፣ ፈረንሳይና ኒውዚላንድ ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ በአውስትራሊያ እና በህንድ የሚገኙ ወጣቶች በየሳምንቱ ከትምህርት ቤት በመቅረት አካባቢያችንን አድኑልን የሚል ጥሪ ሲያሰሙ ከርመዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ