ኑስራት ጃሃን ራፊ፡ ወሲባዊ ትንኮሳን ሪፖርት ያደረገችውን አቃጥለው የገደሉ 16 ግለሰቦች ሞት ተበየነባቸው

ኑስራት ጃሃን ራፊ

የፎቶው ባለመብት, family handout

የምስሉ መግለጫ,

ኑስራትን የገደሏት በላይዋ ላይ ነጭ ጋዝ አርከፍክፈው በማቃጠል ነበር

የባንግላዴሽ ፍርድ ቤት በመምህሯ ወሲባዊ ትንኮሳን እንደተፈፀመባት ሪፖርት ያደረገችውን ተማሪ በእሳት አቃጥለው የገደሉ 16 ግለሰቦች ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈ።

ኑስራት ጃሃን የተባለችው ተማሪ፤ የትምህርት ቤቷ ርዕሰ መምህር ፆታዊ ትንኮሳ እንዳደረሰባት ሪፖርት ማድረጓን ተከትሎ ነበር ጋዝ አርከፍከው እሳት በመለኮስ አቃጥለው የገደሏት።

በትንሽ መንደር የተወለደችው የአስራ ዘጠኝ ዓመቷ ኑስራት የመድረሳ ወይም የእስልምና ትምህርትን ትከታተል ነበር።

የተገደለችውም ከባንግላዴሽ ዋና መዲና ድሃካ 160 ኪሎ ሜትር በምትርቅ ፌኒ በተባለች ትንሽ ከተማ ነው።

ግድያዋ በአገሪቷ ከፍተኛ ድንጋቴን የፈጠረ ሲሆን ለኑስራት ፍትህ በመሻትም ተከታታይ የሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።

ተመሳሳይ ጥቃቶች ላይ ፍትህ ለመስጠት ዓመታትን ይፈጅ የነበረው የፍርድ ሂደት አሁን ግን በጣም በፍጥነት ከተሰጡት ፍርዶች ይህ አንደኛው ነው ተብሏል። አቃቤ ሕግ ሃፌዝ አሕመድ ለጋዜጠኞች "ፍርዱ በባንግላዴሽ አንድን ሰው ገድሎ ማምለጥ እንደማይቻል ያረጋገጠ ነው" ብለዋል።

የተከሳሾች ጠበቃ በበኩላቸው ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

በኑስራት ሞት ላይ የተደረገው ምርመራ፤ የክፍል ጓደኞቿን ጨምሮ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንዶች እርሷን ዝም ለማሰኘት ሙከራ ማድረጋቸው አመላክቷል።

ፖሊስ ግድያው እንዲፈፀም አዘዋል ያላቸውን ርዕሰ መምህር ሲራጅ ኡድ ዶዩላን ጨምሮ ሦስት መምህራን በፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ተብለዋል። የአዋሚ ሊግ ፓርቲ የአካባቢ መሪዎች የሆኑ ሌሎች ሁለት ተከሳሾች፤ ሩሁል አሚንና ማክሱድ አላም ጥፋተኛ ሆነዋል።

በርካታ የአካባቢው ፖሊሶችም በኑስራት ላይ የተፈፀመው ግድያ አስመልክቶ ራሷን እንዳጠፋች ተደርጎ ሲነዛ የነበረው ሀሰተኛ መረጃ በማሠራጨት ተባብረዋል።

ፖሊስ ጥበቃ እንደሚያደርግላት ከተነገራቸው በኋላ ለፖሊስ ሄዳ ሪፖርት እንድታደርግ እንዳበረታቷት የኑስራት ቤተሰቦች ለአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። በአስቸኳይ ፍትህ እንዲሰጣቸውም ሲጠይቁ ቆይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ለኑስራት ቤተሰቦች ልባቸውን የሰበረ ሐዘን ነው

በኑስራት ላይ የሆነው ምን ነበር?

ከመሞቷ በፊት ኑስራት በሰጠችው መግለጫ "የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ባልተገባ መልኩ ሰውነቴን ነክቶኛል፤ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈፅሞብኛል" ስትል ሪፖርት ካደረገች ከ11 ቀናት በኋላ ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር በትምህርት ቤቱ ጣሪያ ላይ ተወስዳ ነበር።

አንዲት ሴት ተማሪ አንድ ጓደኛዋ እንደተጎዳ ነግራት ነበር ጣሪያው ላይ የወሰደቻት። ጣሪያው ላይ ስትደርስ ግን አምስት ተማሪዎች እንደከበቧትና በርዕሰ መምህሩ ላይ ያቀረበችውን ክስ እንድትተው ጫና ሊያደርጉባት ሞክረዋል። እምቢ ስትልም በእሳት እንደለኮሷት ተናግራለች።

እንደተጎዳችና እንደማትተርፍ ስታውቅ ስለተፈጠረው ነገር በዝርዝር የተናገረች ሲሆን፤ ወንድሟም ንግግሯን በስልኩ ቀረጾታል።

"መምህሩ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈፅሞብኛል፤ እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሴ ድረስ ይህንን ወንጀል እጋፈጣለሁ" በማለት ድርጊቱን የፈፀሙባትን ጥቂት ሰዎች ስም ጠርታለች።

የወንጀል መርማሪ ፖሊስ ኩማር ማጁምደር እንደገለፀው ገዳዮቿ ራሷን ያጠፋች ለማስመሰል ቢሞከሩም እቅዳቸው ሳይሳካም ለጥቂት ቀናትም ቢሆን በሕይወት ተርፋ መግለጫ መስጠት ችላለች።

ይሁን እንጅ 80 በመቶ የሆነው የሰውነት ክፍሏ የተቃጠለው ኑስራት፤ ከአራት ቀናት በኋላ በሚያዚያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

አክሽን ኤድ የተባለ ድርጅት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት፤ በባንግላዴሽ የልብስ ፋብሪካ የሚሠሩ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ወሲባዊ ትንኮሳ ሲፈፀም አይተዋል አሊያም ራሳቸው ላይ ተፈፅሞባቸዋል ይላል።

ይሁን እንጅ እንደ ኑስራት የደረሰባቸውን ወሲባዊ ትንኮሳ ሪፖርት ማድረግ የሚያስከትለው መዘዝ ስላለ መናገሩ የተለመደ አይደለም።

የተለያየ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ከማህበረሰቡ በአካል፣ በተለያዩ ድረገፆች ከቃል ዘለፋ ጀምሮ አካላዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ኑስራትም ከዚህ አላመለጠችም።

ለፖሊስ ሪፖርት ካደረገች በኋላ ርዕሰ መምህሩ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተከትሎ ለኑስራት የከፋ ነበር። ግለሰቡ እንዲለቀቅ የሚጠይቁ ሰዎች አደባባይ ወጡ።

ተቃውሞውን ያደራጁት ሁለት ወንድ ተማሪዎች ሲሆኑ የአካባቢውም ፖለቲከኞችንም ድጋፍ ማግኘት እንደቻሉ ተገልጿል።

ምንም እንኳን ተጠቂዋ እሷ ብትሆንም ብዙዎች እሷን መወንጀል ጀመሩ። ቤተሰቧም የደህንነቷ ሁኔታ እንዳስጨነቃቸውም መናገራቸው ተዘግቧል።

ጥቃቱን ሪፖርት ካደረገች ከአስራ አንድ ቀናት በኋላ ፈተና ልትፈተን ትምህርት ቤት ሄደች።

"እህቴን ትምህርት ቤት የወሰድኳት እኔ ነኝ። ወደ ግቢው ለመግባት ስጠይቅ እንደማይፈቀድልኝ ነገሩኝ" በማለት የሚናገረው ወንድሟ ማህሙዱል ሃሰን ኖማን " ከመግባት ባያስቆሙኝ ኖሮ እንዲህ አይነት ሰቅጣጭ ጉዳይ በእህቴ ላይ አይፈፀምም ነበር" ብሏል።

በኑስራት ግድያ ሕዝቡ ስሜቱን ንዴት ገለፀ?

የኑስራት ሞት ከፍተኛ ተቃውሞን የቀሰቀሰ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችም ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ንዴታቸውን ገልፀዋል።

ኑስራት የደረሰባትን ትንኮሳ በመናገሯ ድፍረቷን ብዙዎች ቢያደንቁትም ከቀናት በኋላ ግን ሰቅጣጭ የሆነው አገዳደሏ ብዙዎችን አስደንግጦ ነበር። ፆታዊ ትንኮሳን ሪፖርት የሚያደርጉ ሰዎች ምን ያህል ለጥቃት ተጋላጭ እንዳደረጋቸውም የሚያሳይ ነው ተብሎም ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር።።

"ሴቶች የደረሰባቸውን ፆታዊ ትንኮሳ ሪፖርት ማድረግ ማለት ሌላ ትንኮሳን ማስተናገድ ማለት ነው። ጉዳዩ ለዓመታት ይጓተታል፤ ማህበረሰቡ ያሸማቅቃቸዋል። ከፖሊስ በኩል ጉዳዩን ለመርመር ፍቃደኝነት አያሳዩም። ወንጀለኞቹም ሳይቀጡ ይቀራሉ፤ ተጠቂዎቹም ፍትህ አያገኙም" በማለት የሰብአዊ መብት ጠበቃና የቀድሞ የሴቶች የሕግ ባለሙያ ማህበር ዳይሬክተር ሳልማ አሊ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሀሲናም ጥፋተኞቹ ሁሉ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው "ጥፋተኛ የሆነ ሁሉ ከሕግ አያመልጥም" ሲሉም በአደባባይ ተናግረው ነበር።

መጀመሪያ ላይ ኑስራት ያቀረበችውን ወሲባዊ ትንኮሳ ክስ የሰረዘው ፖሊስ ግንቦት ወር ላይ በ16 ግለሰቦች ላይ ክስ መስርቷል፤ አቃቤ ሕግም የሞት ቅጣት እንዲበየንባቸው ሲከራከር ቆይቷል።