የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሦስት ቀናት ጸሎት እና ምሕላ አወጀ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

የፎቶው ባለመብት, Sergei Fadeichev

የምስሉ መግለጫ,

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ. ም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ የምሕላና የሰላም ጥሪ አስተላልፏል።

በአገሪቷ እንኳንስ ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጎሳንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋታቸው እንዳሳሰበው የገለፀው ቅዱስ ሲኖዶሱ፤ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የጸሎትና ምሕላ እንዲደረግ አውጇል።

ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጀምሮ ሁሉም አካላትና ዜጎች በየድርሻው ለአገራዊ ሰላም፣ አንድነት እና ተግባቦት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አድርጓል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች "ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች መነሻነት የተከሰቱ ናቸው" ብሏል።

ከእውነታ የራቁ፣ የሕዝቡን የአንድነት እና የአብሮነት ባህል የሚጎዱ፣ ታሪክን የሚያፋልሱ ሐሰተኛ ትርክቶች ለግጭቶች መንስዔ እንደሆኑም ገልጿል።

አክሎም የፖለቲካ ኃይሎች፣ የብዙኃን መገናኛዎች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዲሁም ምሁራንና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ብሔርንና ኃይማኖትን መሠረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላት ተቆጥበው፤ ለአገራዊ አንድነትና ተግባቦት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አቅርቧል።

የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት፣ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ከመከሠታቸው በፊት ቀድሞ በመከላከል የሰው ሕይወት መጥፋትንና የንብረት ውድመትን በማስቀረት የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጠይቋል።

"እስከ አሁን ድረስ በግጭቶች እየደረሱ ካሉት የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ልንማር ባለመቻላችን ችግሩ ቀጥሎ በዚህ ሳምንትም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልልና በሌሎችም ክልሎች እየተሠከተ ያለው ግጭት እጅግ አሳሳቢ ነው" ሲል ገልጿል ሲኖዶሱ።

ችግሩ ጊዜ የማይሰጥና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በሕብረት ችግሩን ካልቀረፍነው መጠነ ሰፊ ጉዳትን የሚያስከትል በመሆኑም ከሌሎች የመወያያ አጀንዳዎች በማስቀደም በጉዳዩ ላይ በስፋት መወያየቱን ገልጿል።

ከውይይቱ በኋላም ባለ አስራ ሁለት ነጥብ የአቋም መግለጫ እና የሰላም ጥሪ አስተላልፏል።

ሲኖዶሱ በመግለጫው ማንኛውም የተለየ ሃሳብ ያለው ወገን በሰለጠነ እና በሰከነ መንገድ በውይይት ችግሮችን እንዲፈታ፣ የወደፊት የአገር ተረካቢ የሆነው ትውልድ አገራቸውንን ከጥፋትና ካልተገባ ድርጊት እዲታደጉ ጥሪ አቅርቧል።

ልዩ ልዩ ፅሁፎችንና ዘገባዎችን በመገናኛ ብዙኃን አሊያም በማህበራዊ ሚዲያ የሚያቀርቡ የፖለቲካ ተንታኞች እና አክቲቪስቶች ከስሜት፣ ከብሔር፣ ከቋንቋና ከኃይማኖት ልዩነት በጸዳ ሁኔታ ለሰላም የበኩላቸውን እንዲያደርጉ፣ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር ግጭትን ከሚፈጥሩ ነገሮችና ትንኮሳዎች እንዲቆጠቡና ሚዛናዊ የሆኑ መረጃዎችን ለሕዝቡ በማድረስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቋል።

ምሁራን ለአገር እድገት ያላቸውን ሚና የሚጠቅሰው መግለጫው አሁን አሁን ግን አንዳንድ ምሁራን የሚያስተላልፏቸው የኢትዮጵያን ታሪክ መሠረት ያላደረጉ ትርክቶች ለግጭትና ላለመግባባት መንስዔ ሲሆኑ እንደሚስተዋሉ ጠቅሷል።

በመሆኑም ምሁራን ለአገራዊ አንድነትና ሰላም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፏል።

በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎችም ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ከሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ እና ከውይይቱ የሚገኙ ግብዓቶችን የእቅዳቸው አካል አድርገው ለትግበራው በመሥራት ኃላፊነታቸውን እዲወጡ ጠይቀዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያን ሰላም በማይወዱ አካላት የሚከሠቱ ልዩ ልዩ አፍራሽና ግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን ወደ ጎን በመተውና በአርቆ አሳቢነትና በአገር ባለቤትነት መጠነ ሰፊ ትዕግሥት የተሞላበት አገራዊ አንድነትና ኅብረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ላበረከቱት የማይተካ ሚና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ምስጋና አቅርቧል።

በመሆኑም አሁንም ለሰላምና አንድነት በዘር፣ ብሔርና ሃይማኖት ሳይለያዩ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሲኖዶሱ የአደራ መልዕክት አስተላፏል።

መግለጫው አክሎም ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም ለአገራዊ አንድነትና ለእምነት ነጻነት በአንድነትና በሕብረት ለመላው ሕዝባችን የሰላም ጥሪ በማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አድርገዋል።

በመጨረሻም መላው ሕዝብ እንደየእምነቱና ሃይማኖቱ ሥርዓት ከዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ቀን ያህል በጾም፣ በጸሎትና በሐዘን ስለ ሀገር ሰላም በአንድነት ጥሪውን ለፈጣሪው ያቀርብ ዘንድ ጥሪውን አስተላልፏል።