በሩዋንዳ ለነፍሰጡር እናቶች የሚሆን የስፖርት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ነፍሰጡር እናቶች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ

ሩዋንዳ ለነፍሰጡር እናቶች የሚጠቅምና በጋራ የሚደረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደጀመረች ተገለጸ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ በተካሄደው በዚህ የነፍሰጡር እናቶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ የተሳተፉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መደሰታቸውንና ባለስልጣናትም ስፖርታዊ እንቅስቃሴው እንዲቀጥል እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በዋና ከተማዋ ኪጋሊ ውስጥ በተካሄደው የመጀመሪያው የስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ ከ100 በላይ ነፍሰጡር እናቶች የተሳተፉ ሲሆን አላማውም የነፍሰጡር ሴቶችን አካላዊ ሁኔታን በተመለተ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመለወጥ መሆኑን አዘጋጆቹ ተናግረዋል።

አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅትና ስፖርታዊ እንቅስቃሴውን ያስተባበረው መሪ ኔልሰን ሙካሳ እንደገለጹት፤ በርካታ ሩዋንዳውያን አንዲት ሴት ስታረግዝ ከሁሉም አይነት አካላዊ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ አለባት ብለው ያምናሉ።

"ነፍሰጡር እናት እንቅስቃሴ የማታደርግ ከሆነ ለራሷና ለተሸከመችው ልጇ ደህንነት በጣም አደገኛ ነው" ብለዋል ሙካሳ።

በስፖርታዊ እንቅስቃሴው ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ነፍሰጡር እናቶች መካከል አንዷ ሊብሬ ኡዊዜይማና ለቢቢሲ እንደገለጸችው በእርግዝናዋ ጊዜ ፈጽሞ አካላዊ እንቅስቃሴ አድርጋ አታውቅም።

"ስላልለመድኩት በጣም ደክሞኝ ነበር፤ ነገር ግን ከሌሎች ነፍሰጡር ሴቶች ጋር አካላዊ እንቅስቃሴን በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ" ብላለች።

የሰባት ወር እርጉዝ የሆነችው ሩትም ሌሎች ተመሳሳይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ እንደምትፈልግ ተናግራለች።

"በጣም ጥሩ ነገር ነው፤ ልምምድ አድርጌያለሁ። ዘና የማለት ስሜት ፈጥሮብኛል፤ በተጨማሪም የጽንሱ እንቅስቃሴም ደስ የሚል ስሜትን ፈጥሮብኛል" ስትል የተሰማትን ገልጻለች።

በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ውስጥ የማህጸንና ጽንስ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ጂያን ኒይሪንክዋያ ወደ ግል ክሊኒካቸው የሚመጡትን ሁሉም ነፍሰጡር እናቶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመክራሉ።

"የእግር ጉዞ፣ ዋናና ሰዎነትን ማፍታታት ምንም አይነት አሉታዊ ተጽዕኖ በእርጉዝ ሴቶች ላይ የለውም" ይላሉ ዶክተር ጂያን።

የስፖርታዊ እንቅስቃሴው አስተባባሪዎች በዝግጅታቸው ላይ ለታደሙ እርጉዝ ሴቶች የሚሆኑና ምንም አይነት የጎንዮሽ ውጤት የሌላቸውን የእንቅስቃሴ አይነቶችን መምረጣቸውን ገልጸዋል። ጨምረውም ወንዶች በዚሁ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።