". . . ጦርነት ታውጆብን ነበር" ምክትል ፕሬዝደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ትናንት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

ስለፕሬዝዳንት ኢሳያስ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ወደ መቀሌ መምጣትን በተመለከተ "የትግራይ መንግስት የኤርትራ እና የትግራይ ህዝቦች ዝምድና እንዲጠናከር፣ ግንኙነቱ ወደ ንግድና ትብብር እንዲሸጋገር ከፍተኛ ፍላጎት" እንዳለ ጠቅሰው "የፌደራል መንግሥት ያላደረገው ነው እያደረግን ያለነው፤ የፌደራል መንግሥት ከሚሰራው ሥራ አንጻር ሲታይ እኛ እልፍ እየሰራን ነው" ብለዋል ዶክተር ደብረጽዮን።

የተዘጉ የድንበር መተላለፊያዎችን በተመለከተ "ፕሬዝደንቱ በመኪና ነው ወይስ በአውሮፕላን የሚመጡት የሚለው ትተን፤ መንገዱ ሳይከፈት ግን እንዴት ነው የሚመጡት? ብለን እንጠይቅ። እኛ የተዘጋው መንገድ እንዲከፈት እንፈልጋለን፤ መጥተው ለማስተናገድም ዝግጁ ነን። ግን መንገድ ተከፍቶ በመኪና እንጂ በአውሮፕላን እንዲመጡ አንጠብቅም" በማለት የፕሬዝደንት ኢሳይያስን ወደ መቀለ መምጣት እንደሚደግፉት ገልጸዋል።

ዶክተር ደብረጽዮን ጨምረውም ከዚህ በፊት ከፕሬዝደንት ኢሳያስ ጋር እንዲገናኙ ተፈልጎ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ መቅረቱን አንስተዋል።

'የትግራይ ህዝብ አደጋ ላይ ነው'

'የትግራይ ህዝብ አደጋ ተደቅኖበታል' በማለት የክልሉ መንግሥት ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ላለመመለስ ሰበብ እያቀረበ ነው የሚል ትችት ይቀርባል ተብለው የተጠየቁት ዶክተር ደብረጽዮን "ህዝቡ ላይ የተጋረጠ የህልውና አደጋ አለ፤ ለዚህ ነው አንድ እንሁን የምንለው። ህዝቡ በህልውናው የመጡበት ስጋቶች አሉ። የዚህ ህዝብ ደህንነት ካልተጠበቀ ደግሞ" የመልካም አስተዳደርና የመሬት ጥያቄዎች ትርጉም አይኖራቸውም" ሲሉ መልሰዋል።

"በመሆኑም በማንኛውም ጊዜ የትግራይ ህዝብ ሰለምና ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ ነው" ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፤ ከዚህ በፊት ወደ መቀሌ የአየር ማረፊያ መጥተው የነበሩት የፌደራል ፖሊስ የጸረ ሽብር አባላትን ጉዳይ አንስተው ያን ድርጊት "ጦርነት እንደታወጀብን ነው የምንቆጥረው" በማለት "ቃታችንን ያልሳብነው እኛ እንጂ በእነሱማ ጦርነቱ ታውጆብን ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢህአዴግ ውህደት

በኢህአዴግ የውህደት ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የትግራይ ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ደብረጽዮን "ህወሓት በውህደቱ ላይ የተለየ አቋም እንደሌለውና እንዲተገበር እንደሚፈልግ" ተናግረዋል።

"የአራቱ ድርጅቶች የፖለቲካ ፕሮግራም አንድ አይነት ነበር፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነበር። አሁን ግን አንድ አይደለንም። ልዩነታችን አደባባይ ላይ ወጥቷል። ስማቸውን የቀየሩት ድርጅቶችም ፕሮግራማቸውን ለመቀየር አስበው ነበር፤ ከተቀየረው ፕሮግራማቸው ጋር ወደ ሃዋሳ ቢመጡ ኖሮ ያን ጊዜ እንለያይ ነበር" ብለዋል።

አሁን ያለው ልዩነት የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ደብረጽዮን "ህወሓት ሳይሆን ቃሉን ያላከበረው፤ ከሃዋሳው ጉባኤ በኋላ ክዳችሁናል ነው እያልናቸው ያለነው" በማለት ኢህአዴግ ፕሮግራም የመቀየር ፍላጎት ካለው አስቸኳይ ስብሰባ መጥራት እንዳለበት ገልጸዋል።

ስለ ተከለከሉ ሰልፎች

"መንግሥት የሴቶች ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። ሰልፍ ተከልክሏል መባሉን ሰምቻለሁ፤ ለምን ያላሟሉት ነገር ካለ አሟሉ አትሉም? ለምን ትከለክላላችሁ? ጠርታችሁ አናግሯቸው ብያቸዋለሁ። ለትግራይ ይጠቅማል ያለ ሁሉ፤ እኛን ለመስደብም ቢሆን ሰልፍ መውጣት አለበት" ብለዋል።

"ሰልፍ ይጠቅማል ወይ ካላችሁኝ? በእኔ እምነት አይጠቅምም" ያሉት ምክትል ፕሬዝደንቱ "መዋቅራዊ ጽዳት ላይ ባለንበት ወቅት አይደለም ሰልፍ ወሬም አያስፈልግም። እንዴት ወደፊት እናምራ በሚለው ግን መነጋገር እንፈልጋለን" ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በሚመለከት ይካሄዳል ስለተባለው ሰልፍ ደግሞ "መንግሥት በተግባር ሥራ በሚሰራበት ወቅት፤ መንግሥት ላይ ሰልፍ ማካሄድ አስፈላጊ አይደለም" ሲሉ ተችተዋል።