አረቄ ከእንቁላል እና ሌሎች ፈሳሾች ጋር ቀላቅሎ በመጠጣት ታዋቂ የሆነው ቻይናዊ

ሊዩ ሺቻዎ

የፎቶው ባለመብት, LIU SHICHAO

ቢራ፣ ፔፕሲ፣ እሳት የሚነድበት ስፕራይት እና ጥሬ እንቁላል ቀላቅለው ቢጠጡ ምን ይሆናሉ?

ሊዩ ሺቻዎ ከላይ የተጠቀሰውን ቅይጥ ጭልጥ አድርጎ ሲጠጣ ራሱን ይቀርፅና ተንቀሳቃሽ ምስሉን ማሕበራዊ ድር-አምባ ላይ ያሠራጨዋል። ይህን ቪዲዮ ትዊተር ላይ ብቻ 12 ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል።

ታድያ ሊዩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲሁ በከንፈሮቹ መሃል አንድ ትንባሆ እንደያዘ ስድስት መለኪያ ኮረንቲ የሚያስንቅ መጠጥ ሲጨልጥ የሚታይበትን ቪዲዮ 800 ሺህ ሰዎች አይተውለታል።

ደግሞ በሌላ ቪድዮ ቮድካ፣ ዊስኪ፣ ቀይ ወይን እና ቢራ እንዲሁም መገለጫው የሆነውን ጥሬ እንቁላል ቀላቅሎ እንደ ቀዝቃዛ በጉሩሮው ሲያወርድ ይታያል። ይህን ምስል ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች አይተውታል።

ለመሆኑ ሊዩ ሺቻዎ ማነው? ሰውነቱስ እንዴት ነው ይህን ሁሉ አረቄያዊ መጠጥ እየዋጠ ዝም የሚለው? የሊዩን ጠባይ ተመልክቶ ቻይናውያን የአረቄ ሱሰኞች ናቸው ማለት ይቻላል?

እንዴት ሲል ጀመረው?

ሊዩ የመጀመሪያ ሙከራው ሰባት ጠርሙስ ቢራ በ50 ሰከንድ መጨለጥ ነበር። አደረገው። የዛሬ ሶስት ዓመት።

«የሆነ ቀን ሰዎች ቢራ ሲጠጡ አየሁና እኔስ ምን ይሳነኛል ብዬ ተነሳሁ» ይላል ለቢቢሲ ቻይና ክፍል ቃሉን ሲሰጥ። ከዚያም እራሱን በራሱ እየቀረፀ ቻይናውያን ቪድዮ የሚጋሩበት አምባ ላይ ይለጥፈዋል።

ኩዋይሹ የተሰኘው ማሕበራዊ ድር አምባ ተጠቃሚዎች ከአንድ ደቂቃ በላይ የሆነ ቪዲዮ እንዲለቁ አይፈቅድም። ይህ ለሊዩ ፈተናም ዕድልም ነበር። ሰባት መለኪያም ጠጣ ሰባት ቡትሌ ከአንድ ደቂቃ በታች ማጠናቀቅ አለበት።

ሊዩ፤ ኩዋይሹ ላይ 470 ሺህ ተከታዮች ነበሩት። በወርም 10 ሺህ ዩዋን [1400 ዶላር] ያገኝ ነበር። ኋላ ላይ ግን ድርጅቱ ሊዩ የሚለጥፋቸው ቪዲዮች ጤናን ከግምት ውስጥ ያስገቡ አይደሉም በማለት ገፁን ዘጋበት።

ነገር ግን የሊዩ ቪዲዮ ሾልኮ ወጥቶ ትዊተር ላይ ደረሰ። ሊዩም ከቻይና ውጭ ታዋቀቂነት አገኘ። «ሰዎች ትዊተር ላይ እኮ ታዋቂ ሆነሃል እያሉ ይነግሩኛል፤ እኔ ግን ትዊተር ምንድነው? ስል እጠይቃቸዋለሁ።»

የፎቶው ባለመብት, LIU SHICHAO

«ሚስቴ ትናደዳለች»

ቤይጂንግ አቅራቢያ ካለች መንደር የሚኖረው የ33 ዓመቱ ሊዩ ስለ ማሕበራዊ ድር አምባዎች የሚያውቀው ነገር አልነበረም። «እኔ የገጠር ሰው ነኝ። እንዴት አድርጌስ ላውቅ እችላለሁ» ይላል።

ትዊተር እና መሰል ድር አምባዎች ቻይና ውስጥ የተከለከሉ ናቸው። ቪዲዮቹ የሚጫኑለት ውጭ ሃገር ባለ ሰው ነው። በስድስት ወራት ብቻ 60 ሺህ ተከታዮች ማፍራት ችሏል።

«ውጭ ሃገር ያሉ አድናቂዎቹ በጣም ደጋግ ናቸው። ባለፈው አንኳ አንድ ቱርካዊ አድራሻዬን ፈልገ የቱርክ ቢራ ላከልኝ።»

ሊዩ አሁንም በቪዲዮዎቹ አማካይነት ገንዘብ ያገኛል። የትዊተር ገፁ 'ፔይ ፓል' ከተሰኘ የበይነ መረብ ገንዘብ መላላኪያ ጋር የተገናኘ ነው። ነገር ግን ሕይወቱን የሚመራው ከትዊተር በሚያገኘው ገቢ ብቻ አይደለም፤ ስጋ በመሸጥ እንጂ።

«ብዙዎቹ አድናቂዎቼ ወንዶች ናቸው። ምናልባት እነሱም መጠጣት ይወዱ ይሆናል። ይቀኑበኝም ይሆናል። ሚስቴ ግን ትናደዳለች። ለጤናዬ በመስጋት ነው። አንዳንዴ እንጨቃጨቃለን።»

ሊዩ እኔ የአልኮል ሱሰኛ አይደለሁም ይላል። «እንደ ሰሜና ቻይናውያን ብቻዬን ቁጭ ብዬ ኮረንቲ ስጎነጭ አልገኝም።»

ሊዩ ጤናው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት ይናገራል። ቪዲዮዎቹን ሲለጥፍም ከማስጠንቀቂያ ጋር ነው። በተለይ ታዳጊዎች እንዳይሞክሩት ይመክራል።

የሎንዶኗ ዶክተር ሳራ ካያት ግን ምን ቢሆን አልኮል አልኮል ነው ይላሉ። አሁን ምን ዓይነት ጉዳት ላይመጣ ይችላል። ቆይቶ ግን መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። አልፎም አልኮል ሲበዛ የአእምሮ መቃወስ ሊያመጣ እንደሚችል ያሰስባሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ቻይናውያን ወንዶች በጣም ጠጪዎች ናቸው ሲል በመረጃ አስደግፎ የሁኔታውን አሳሳቢነት ይፋ አድርጓል። 36 በመቶ ወንድ ቻይናውያን አንድ ጊዜ የብርሌ አንገት ካነቁ አይነሱም ይላል መረጃው።

ለጊዜው ሊዩ የሚለጥፋቸው አዳዲስ ቪዲዮዎች ሳይሆኑ የቀደሙትን ነው። ለመጨረሻ ጊዜ በለጠፈው ምስል ላይ እንዲህ ሲል ለአድናቂዎቹ መልዕክት አስተላልፏል። «እኔ አንድ የገጠር መንደር የምኖር ቻይናዊ ነኝ። ስለተዋወቅን ደስ ብሎኛል። እወዳችኋለሁ»

ወረድ ብሎ ያለውን ቪዲዮ ሲጫኑት ሊዩ ቢራ፣ የሩዝ ወይን፣ ስፕራይት፣ ሬድ ቡል እና የማትለየውን ጥሬ እንቁላል ቀላቅሎ ሲጨልጥ ይታያል። በስምንት ሰከንድ ውስጥ።