ዝምባብዌ ረሃብ የጎዳቸው ዝሆኖችን ለሌላ ሀገር ሸጠች

ዝሆኖች በሁዋንጌ ብሔራዊ ፓርክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዝምባብዌ 30 ዝሆኖችን ለተለያዩ ሀገራት እየሸጠች መሆኑ የተነገረ ሲሆን ከነዚህም መካከል በቅርቡ ለቻይና መሸጧ በመብት ተሟጋቾች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

የእንስሳት መብት ተሟጋቾች ሽያጩን የተቹ ሲሆን እንስሳቱ እንግልት ሊደርስባቸው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

የዝምባብዌ ብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት ግን፤ በዚህ 55 ዝሆኖችን በገደለው የድርቅ ወቅት ሌሎች የዱር እንስሳትን ለማዳን ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ተነግሯል።

አሁን የተሸጡት ዝሆኖች ከወላጆቻቸው ከተለዩ ዓመት እንዳለፋቸውም ለማወቅ ተችሏል።

የዝምባብዌ ብሔራዊ ፓርክ ቃል አቀባይ የሆኑት ቴናሺ ፋራዎ እንዳሉት ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ በሑዋንጊ ብሔራዊ ፓርክ ያሉ የዱር እንስሳትን ለመታደግ የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር ይውላል።

ቃል አቀባዩ አክለውም የመብት ተሟጋቾች የሕዝብ ቁጣን ለመቀስቀስ ሆን ብለው እየሰሩ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

ነገር ግን የ አድቮኬት ፎር አርዝ ዳይሬክተር የሆነው ሌኒን ቺያስራ ውሳኔውን ይቃወማል።

"ዝሆኖቹ ተይዘው መሸጣቸውና ከባህላቸውና ከለመዱት አካባቢ ውጪ መወሰዳቸው አግባብ አለመሆኑን ስንናገር ነበር። ብዙ ጊዜ ወደ እንስሳት ማሳያ ነው የሚወሰዱት፤ ከዚያም የተለያየ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ይፈፀምባቸዋል" ብሏል።

በብሔራዊ ፓርኩ ዙሪያ የተስፋፋው የማዕድን ፍለጋ የእንስሳቱን የግጦሽ ስፍራ እና የውሃ አቅርቦት በእጅጉ ጎድቶታል ሲል የሚናገረው ቺያስራ ይህም "እንስሳቱ ፓርኩን ጥለው እንዲሸሹና ከሌሎች እንስሳት ጋርም ለውሃ እንዲፎካከሩ እያደረገ ነው" ይላል።

በነሐሴ ወር ላይ የዓለም አቀፉ ንግድ ስምምነት ደህንነታቸው ላይ አደጋ ከተጋረጠ እንስሳት መካከል በአፍሪካ የሚኖሩ ዝሆኖችን በመጥቀስ ከአህጉሪቱ ውጪ እንዳይሸጡ ያለ ቢሆንም እስካሁን ግን ስምምነቱ አልፀደቀም።