የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አመራሮች ጋር ተወያዩ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ

የፎቶው ባለመብት, J. Countess

የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ዛሬ እንደተወያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ህዝብ ግነኙነት መላከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሠይፈ ለቢቢሲ ተነገሩ።

የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ዛሬ ዓርብ ከሰዓት በኋላ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ፣ ከሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እና ከፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሸነር ጋር ተወያይተዋል።

መላከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ፤ በውይይቱ ላይ የቤተክርስቲያኗ ተወካዮች በቤተክርስቲያን ላይ የሚቃጣው ጥቃት እንዲቆም እና መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን እንዲያከናውን ጠይቀዋል።

ትናንት የተጀመረውን የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተከትሎ የእምነቱ ተከታዮችና ቤተ ክርስቲያኗ በተለያዩ ስፍራዎች እየገጠሟቸው ናቸው ባሏቸው ጥቃቶችና ችግሮች ዙሪያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲያናግሯቸው የቤተክርስቲያኗ አባቶች በጠየቁት መሰረት ነው ውይይቱ የተካሄደው።

ረቡዕና ሐሙስ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች በነበሩት የተቃውሞ ሠልፎች ላይ ክርስትያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ጥቃት ደርሶባቸዋል ያሉት መላከ ሕይወት አባ ወልደየሱስ፤ "ተቃውሞው የፌደራል መንግሥቱ ላይ ይምሰል እንጂ ጥቃት የደረሰው በአካባቢው የሚኖሩ ክርስቲያኖችና ቤተ ክርስቲያናት ላይ ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

የተቃውሞ ሠልፍ በተካሄደባቸው የኦሮሚያ፣ ሐረርና ድሬ ዳዋ ከተሞች፤ አምቦ፣ ቢሾፍቱ፣ ባሌ ሮቢ፣ አዳማ፣ ሞጆ እንዲሁም በድሬዳዋ እና ሀረር፣ የመከላከያ ሠራዊት መሰማራቱ ዛሬ የመከላከያ ሚኒስትር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ህዝብ ግነኙነት መላከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሠይፈ ለቢቢሲ፤ "'ሕግ የማስከበር ሥራን እንስራለን፣ እናንተም እርዱን በጸሎት አግዙን' ብለውናል" ሲሉ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ስለነበራቸው ውይይት ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር የተሰባሰቡ ከ60 በላይ ሊቃነ ጳጰሳት ለስብሰባ ተቀምጠው የነበሩ ሲሆን በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ አካባቢ፣ ዶዶላ፣ አርሲ ነገሌ፣ ኮፈሌ አካባቢ በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን እንደሰሙ ተደናግጠው ከሰዓት በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ሲወያዩ መቆየታቸውን ተናገግረዋል።

ሊቃነ ጳጳሳቱ በሁኔታው እጅግ ከማዘናቸው የተነሳ "ስብሰባውን በትነን ወደ ሚመለከተው አካል ሄደን ከልጆቻችን ጋር ሰማዕትነትን እንቀበላለን" እስከማለት መድረሳቸውን ይናገራሉ።

ትናንት ከሰዓት በኋላ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገራቸውንና ግጭቶቹ በተነሱባቸው አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊት መላኩ እንደተነገራቸው መላከ ሕይወት ያስረዳሉ።

ግጭቶች በተነሱባቸው አካባቢዎች ሕዝበ ክርስቲያኑ ጥቃቱን በመሸሽ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ መጠለላቸውን የተናገሩት መላከ ሕይወት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተለየ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት እየደረሰባት መሆኑን አስታውሰው ከመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም መወያየታቸውን አስታውሰዋል።

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ ትናንት ከተጀመረ በኋላ በመሃል በአገሪቱ እያጋጠመ ያለውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ ለቤተክርስቲያኗ ምዕመናንና ለመላው ህዝብ የሰላም ጥሪ በማቅረብ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የጸሎትና የምሕላ ዐዋጅ ማወጁ ይታወሳል።

ለቅዱስ ሲኖዶሱ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በተለያዩ ቦታዎች ባለው አለመረጋጋት ሳቢያ መደበኛ ጉባኤውን በማቋረጥ በምዕመናንና በአብያተ ክርስትያናት ላይ ደረሱ በተባሉ "ጉዳቶችና ባሉ ስጋቶች" ላይ በመወያየት መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ሲመክር ማምሸቱ ተነግሯል።

ሲኖዶሱ ያቀረበው የሰላም ጥሪ በዋናነት "መስመር እየለቀቀ የመጣውን በምዕመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን የማያባራ ጥፋት ማስቆምን" የሚመለከት መሆኑን አመልክቷል።

ትናንት የወጣው መግለጫ አክሎም "እስከ አሁን ድረስ በግጭቶች እየደረሱ ካሉት የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ልንማር ባለመቻላችን ችግሩ ቀጥሎ በዚህ ሳምንትም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም ክልሎች እየተከሰተ ያለው ግጭት እጅግ አሳሳቢ ነው" ሲል ገልጿል ሲኖዶሱ።

ችግሩ ጊዜ የማይሰጥና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በሕብረት ችግሩን ካልቀረፍነው መጠነ ሰፊ ጉዳትን የሚያስከትል በመሆኑም ከሌሎች የመወያያ አጀንዳዎች በማስቀደም በጉዳዩ ላይ በስፋት መወያየቱንም አመልክቷል።