"ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት ዋጋ ያላገኘሁበት ቢኖር ትምህርት ነው" ቸኮለ መንበሩ

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ምሩቁ ሊስትሮ

ለመማር ምን ያህል ዋጋ ከፍለዋል? ምን ያህልስ ስኬታማ ነኝ ብለው ያስባሉ? የልፋትዎትን ያህልስ አግኝቻለሁ ብለው ያስባሉ?

ዛሬ የአንድ ወጣትን የትምህርት ጉዞ እናጫውታችኋለን።

ቸኮለ መንበሩ ይባላል። የተወለደው ናበጋ ጊዮርጊስ በምትባል ቦታ ነው።

በህጻንነቱ ነበር አባቱን በሞት ያጣው። እናቱም ሌላ በማግባቷ ታዳጊው ቸኮለ ከአያቶቹ ጋር መኖር ጀመረ።

ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ መማር እንደሚፈልግ ለአያቱ ቢነገርም 'ማን ያስተምርሃል?' በሚል ውድቅ ተደረገበት።

ከስደት ወደ ባለሃብትነት

ወደ አጎቱ ቤት በማቅናት በእረኝነት ማገልገል ጀመረ። ጓደኞቹ ትምህርት ቤት መግባታቸው በድጋሚ "አስተምሩኝ?" ብሎ እንዲጠይቅ ምክንያት ሆነው።

ካልተማረ አብሯቸው መኖር እንደማይፈልግ ገልጾ ነው ጥያቄውን ያቀረበው። አያቱ ሁለተኛውን ጥያቄ ግን ውድቅ አላደረጉበትም። ትምህርቱንም ጀመረ።

ሁለት ዓመት ያህል አያቱ ዘንድ ተቀምጦ ከተማረ በኋላ መግባባት ባለመኖሩ ምክንያት ከአያቱ ቤት እንዲወጣ ሆነ።

ትምህርት እስኪጀመር ክረምቱን እናቱ ጋር እንዲያሳልፍ ተደረገ። 'እስከመስከረም ድረስ የት ይክረም?' በሚል ሽማግሌዎች ወደ እናቱ ተልከው በመጠየቃቸው "ከእናቴ ጋር 2 ማድጋ ከረምኩ" ይላል። በዚህም ምክንያት "ከእናቴ ጋ ሁለት ክረምት ያሳለፍኩ ብቸኛው ልጅ እንደሆንኩ አስባለሁ" ሲል ያስታውሳል።

የሚረዳው ሰው ባለመኖሩ ራሱን ማስተማር ብቸኛው አማራጭ ሆነ።

አንድ ጫማ የሚጠርግ ጓደኛውን ሲያወያየው አብሮት እንዲሠራ መከረው። አባቱ የተከሉትን ባህር ዛፎች በሃያ ብር ሸጦ ጫማ ለመጥረግ የሚረዱትን ቁሳቁሶችን ገዝቶ ሥራ ጀመረ። "ከዚያ በኋላ መማር ጀምርኩኝ" ይላል ቸኮለ።

ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ከትምህርት ሰዓቱ ውጭ ጫማ እየጠረገ ትምህርቱን መከታተሉን ቀጠለ።

"አካል ጉዳተኛ መሆኔ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል"

"ለመማር የተሻለ ያግዘኛል ብዬ ያሰብኩት ሥራ ጫማ መጥረግ ነው። ግማሽ ቀን እየሠራሁ ግማሽ ቀን ለመማር ማለት ነው። [የሞባይል] ካርድም ሸጫለሁ። አብዛኛውን ሊስትሮ ነው የሠራሁት። [በወቅቱ] ኑሮም ከባድ ስላልነበረ ሊስትሮ ሠርቼ መማር እችል ነበር። አንዳንድ የሚያውቁኝ ሰዎች እያበረታቱ 'እነእከሌ እኮ እንደዚህ ተምረው ነው ዶክተር እና መሃንዲስ የሆኑት' እያሉ ስለሌሎች ስለሚነግሩኝ ከኋላ ያለው ስቃይ አይታየኝም ነበር። የወደፊቱን ነበር የሚታየኝ። "

"ትምህርት ዋጋ ነው ያስከፈለኝ" የሚለው ቸኮለ "ትምህርት ዋጋ ነው ያስከፈለኝ። ስቅይት ብዬ ነበር የተማርኩት። በተለይ በዓል ሲደርስ የነበረው ስሜት ይከብድ ነበር። ዳቦ በልቼ አድር ነበር። ለነገም ከዳቦው ለቁርስ አስተርፍ ነበር። በተለይ 7ኛ እና 8ኛ ከፍል እያለሁ" ሲል ይገልጻል።

የደንብ ልብስ ለመግዛት ጫማ መጥረጉ ብቻ ስለማይበቃው ሥራ ፍለጋ ወደ በረሃ አቅንቷል። ሥራ ስላልነበረ ወደ ሁመራ ያደረገው ጉዞ ስኬታማ አልነበረም። ከጓደኛው ጋር አንድ ሱሪ እና ቲሸርት ብቻ ገዝተው ተመልሰዋል።

ብዙ አስቸጋሪ ወቅቶችን ቢያሳልፍም 8ኛ እና 10ኛ ክፍልን ሲያልፍ አዲስ የደንብ ልብስ ማሰፋት ስለሚያስፈልገው እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ፈተናው ከባድ ነበር። "እነዚህ ሦስቱ [ክፍሎች] ለእኔ ልዩ ናቸው። ማለት በጣም የተጨናነቅኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ" ሲል ያስረዳል።

ከ3ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ድረስ ጫማ በመጥረግ ተምሮ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባውን ውጤት በማምጣቱ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ገባ።

ህይወት "ግቢ [ዩኒቨርሲቲ] ውስጥ የተሻለ ነበር" የሚለው ቸኮለ "ከቀበሌ ረዳት የሌለው የሚል ማስረጃ አጽፌ በወር 200ም ሆነ 100 ብር እየተሰጠኝ፤ ክረምት ደግሞ እዛው [ዩኒቨርሲቲ] እየሠራሁ ተከፍሎኝ እከርም ነበር። ጓደኞቼም አብዛኛውን ይሸፍኑልኝ ነበር። ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተሻለ ነበር። ጥሩ ጓደኞች ነበሩኝ። ደብተር ጭምር ይገዙልኝ ነበር። ስመረቅም ሱፌ እንደተጀመረ ማስጨረሻ ብር ስላጣሁኝ የዶርም ልጆች አግዘው አሰፉልኝ።"

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ የትምህርት ክፍል ለመምረጥ መስፈርት ያደረገው 'ቶሎ የሚያስቀጥረውን' ነበር። በዚህ መሠረትም ኤሌክትሪካል ምህንድስና የመጀመሪያ ምርጫው ነበር። በሁለተኛነት ደግሞ ኬሚካል ምህንድስና። በውጤት እና በተለያዩ መመዘኛዎች መሠረት ሁለተኛ ምርጫው የሆነውን የኬሚካል ምህንድስና የትምህርት ክፍልን ተቀላቀለ።

ከድምፃዊት ቤቲ ጂ እና ቸሊና ጀርባ

"የኢንዱስትሪ ወሬ ነበር። በሃገሪቱ ይህን ያህል መሐንዲስ ያስፈልጋል ሲባል ስለነበር ጥሩ ይሆናል ብዬ ነበር የመረጥኩት። "

"ስለሥራ ዕድልም ማንም የሚነግርህ የለም። ቀደም ሲል የተዘጋጅቼ የመጣሁት ለመቀጠር ነው። . . . ሥራ አለው የለውም አልተነገረንም። የዲፓርትመንት [ትምህርት ክፍል] ምርጫ ጊዜ ሁሉም የውጭ ዲዛይን ያመጣና ኬሚካል ይሄን ይሠራል ስለሚባል በዚያ እየተሳብን ነው የምንገባው።"

"እውነት ለመናገር እኔ የተቀረጽኩትም ሆነ ሊስትሮ ስሠራም ሳስበው የነበረው የመቀጠር ነው አባዜ የነበረኝ" የሚለው ቸኮለ "እሠራለሁ ብልም ገንዘብ ስለሌለኝ ሃሳቡም የለኝም። መቀጠር እና መሥራት ነው የምፈልገው" ይላል።

ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የነበረውን ደስታ ያህል መመረቂያው ሲደርስ ደግሞ "ጭንቀቴ ጨመረ" ይላል። ምክንያቱ ደግሞ "ምን እሠራ ይሆን?" በሚል ነው።

ቀድመዋቸው ከተመረቁት ተማሪዎች ብዙዎቹ ሥራ አለማግኘታቸው ስጋቱን ከፍ አንዳደረገው ቸኮለ ያስረዳል። "ግቢ ስገባ የተደሰትኩትን ያህል ልመረቅ አካባቢ ጭንቀቴ እየጨመረ ነው የመጣው። ምክንያቱም ነገ ደግሞ ሥራ አጥቼ ከዚያ ሊስትሮ ድጋሚ ልቀመጥ ነው። ያሰብኩት ላይሳካ ነው። ተመርቄ ቶሎ ሥራ ላልይዝ ነው። ይኼን ሳስብ ይጨንቀኝ ጀመር" ይላል።

የመጨረሻ ዓመት የዩንቨርሲቲ ተማሪ እያለ ብዙዎች ድጋፍ ያደርጉለት ነበር። "አኔና ጓደኛዬ ሰዎች በሚሰጡን ብር ተመርቀን ስንወጣ [ሊቸግረን ይችላል] በሚል ለአንድ ዓመት የሚበቃ ልብስ ገዝተናል።"

የዘንድሮ ተመራቂዎች እንዴት ሥራ ያገኛሉ?

በ2010 ዓ.ም ከተመረቀ በኋላ ቀጣዩ ሥራ መፈለግ ነው።

"አዲስ አበባ ሥራ ለመፈለግ 3 ወር ነበርኩኝ። በየኢንዱስትሪ ፓርኩ በእግሬ እየዞርኩ ሥራ ስጠይቅ የነበረው።ወልዲያ እና አዲስ አበባ ድረስ ሄጃለሁ። አንድ ፋብሪካ ውስጥም በሃያ ዘጠኝ ብር የቀን ሥራ ጀምሬ ነበር። ግን አላዋጣኝ አለ" ይላል።

ከመጀመሪያ ዲግሪ በታች የሚጠይቁ ሥራዎች ላይም አመልክቶ ያውቃል። ቀጣይ እድገት ይጠይቃል በሚል ማመልከቻው በተደጋጋሚ ውድቅ ሆኗል።

ሥራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው በየቀበሌው የሚከፈትላቸውን የሥራ ዕድል ለመጠቀም ከጓደኞቹ ጋር ቢያመለክትም "በኬሚካል ምህንድስና የተመረቃችሁ አትመደቡም' ቢባሉም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አዎንታዊ ምላሽ ተሰጣቸው። ሥራውን ለማግኘት ዕጣ ስላልወጣለት በዕድሉ መጠቀም ግን አልቻለም።

የተወሰኑት አብሮ አደጎቹ እና የትምህርት ክፍል ጓደኞቹ ሥራ አግኝተዋል።

ከወራት ሥራ ፍለጋ በኋላ ሥራ ባለማግኘቱ ያለው አንድ አማራጭ ብቻ መሆኑን አወቀ። "አማራጭ ሳጣ ሊስትሮ መሥራት ጀመርኩኝ።"

ሴት ተመራቂዎች ለምን ሥራ አያገኙም?

ጫማ እየጠረገም ቢሆን አሁንም ሥራ መፈለጉን አልተወውም። "ጫማ እየጠረግኩም ሥራ እፈልጋለሁ። የምጠርገውን ጫማ ጨርሼ ማስታወቂያ ለማየት እጓጓለሁ። ማስታወቂያ መለጠፊያው አካባቢ ስለሆንኩኝ አሁንም እፈልጋለሁ። እየዞርኩኝም ሥራ እፈልጋለሁ" ይላል።

ሥራ ያላገኘው ባለው አነስተኛ ነጥብ ምክንያት እንደሆነ ለቀረበለት ጥያቄ "ውጤቴ ለእኔ ምንም አይልም። ወደ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ብቻ የተላከ ይኖራል። እኔ ግን ከትምህርት በተጨማሪ የኑሮ ውጣ ውረድ ስለነበረብኝ የተመረቅኩበት ነጥብ ለእኔ ጥሩ ነበር" ብሎ ምላሽ ሰጥቷል።

ለዚህም ነው "ለእኔ ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት ዋጋ ያላገኘሁበት ቢኖር ትምህርት ነው ብዬ አስባለሁ" የሚለው።

ከዚህ ይልቅ በፖለቲካው አለመረጋጋት ምክንያት የመንግሥት ትኩረት ወደ ፖለቲካ መዞሩ፤ ክፍት የሥራ ቦታዎች በዝምድና መያዛቸው እና ያሉት የሥራ ዕድሎች እና የተመራቂዎች ቁጥር አለመጣጣምን በምክንያትነት ያነሳል።

የወንድሙን ገዳይ ለመበቀል ወደ ፈጠራ ሥራ የገባው ኢትዮጵያዊ

የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዞ ጫማ ሲጠርግ ብዙ አስተያየቶች ይሰጡታል። " የሚያውቁኝ መምህራኖቼ ከእኔ ይልቅ እነሱ ናቸው የሚደነግጡት። ሲያገኙን አንገታቸውን ደፍተው ከእኔ በላይ በጣም ስቅቅ ብለው ይሄዳሉ።አንዳንዶቹ ደግሞ ቀርበው አይዞህ ብለው አበረታተውኝ የተወሰነ ገንዘብ ሰጥተውኝ ይሄዳሉ። ጓደኞቼ ሲያገኙኝ ሳይፈልጉም ቢሆን አሠርተው ያላቸውን ሰጥተውኝ ይሄዳሉ። ይህን ትውልድ ተስፋ ታስቆርጣለህ ከዚህ ተቀምጠህ የሚሉም ሰዎች አሉ።"

በመጨረሻም ቸኮለን 'ለምን ተማርኩ ብለህ አስበህ ታውቃለህ?' ብለን ጠይቀነዋል። "ብዙ ጊዜ ባልማር አልናደድም ብዬ አስባለሁ። ይህን ያህል ዋጋ መክፈል አልፈልግም። ምን አሰቃየኝ?። አንደኛዬን የለየልኝ ጥሩ ወይም መጥፎ ሰው እሆናለሁ ብዬ የማስብበት አጋጣሚ አለ" ሲል ስሜቱን አጋርቶናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ