ታንዛኒያ ውስጥ ሥራ ላይ ለግመዋል የተባሉ ቻይናዊያን ታሰሩ

ቻይናውያን ሰራተኞች በታንዛኒያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ቻይናውያን ሰራተኞች በታንዛኒያ

በባሕር ዳርቻዋ የታንዛኒያ መዲና ዳሬ ሰላም አካባቢ በግንባታ ሥራ ላይ የተሰማርተው የነበሩ ቻይናዊያንን መንግሥት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም፤ ሥራውን በፍጥነት ሰርቶ ከማጠናቀቅ ይልቅ ልግመትን መርጠዋል በማለት አስሯቸዋል።

ታሳሪዎቹ በሁለት ኩባንያዎች የተቀጠሩ ሲሆን ሦስት ወንዶችና አንዲት ሴት ናቸው። በከባድ ዝናብ ምክንያት የተጎዳውን ቦይ ለመስራትና ተጨማሪ የማሸጋገሪያ መንገድ ለመገንባት ነበር ቻይናዊያኑ የተቀጠሩት።

ግንባታው የተጀመረበት አካባቢ ወሳኝ የከተማዋ ክፍል በመሆኑ ሥራው ባለመጠናቀቁ ምክንያት የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ከመገደብ አልፎ አንዳንድ ጊዜም ለሰዓታት የተወሰነው የከተማዋ ክፍል ከሌላው የከተማዋ ክፍል እንዳይገናኝ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።

ይህንን ችግር ለመፍታትም በመንግሥት በጀት ግንባታ ተጀምሯል። ነገር ግን ችግሩን ይፈታል የተባለውን ግንባታን በፍጥነት ከመሥራት ይልቅ ልግመትን መርጠዋል የተባሉት አራቱ ቻይናዊያን የግንባታ ሞያተኞች በዳሬ ሰላም ክልል አስተዳደሪ ትዕዛዝ እንዲታሰሩ ተደርጓል።

የዳሬ ሰላም አስተዳዳሪው ፖል ማኮንዳ እንዳሉት አራቱ ታሳሪዎች ሌሊቱን ሙሉ እስር ቤት እያሳለፉ ጠዋት ደግሞ ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ መሆኑን እንዲያረጋግጡ ወደ ግንባታ ቦታው ይላካሉ ብለዋል።

ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ መሆኑን ባለስልጣኑ እስኪያረጋግጡ ድረስም የሌሊት እስራቱና ጠዋት የሚደረገው ግንባታውን የመቆጣጠር ሂደት የሚቀጥል ይሆናል። እስራቱ የሚያበቃው ባለስልጣኑ የግንባታው ፍጥነት 'አርክቶኛል' የሚል ማረጋገጫ ሲሰጡ ብቻ መሆኑም ተገለጿል።

ጉዳዩ የፍርድ ውሳኔ፣ የወንጀል ምርመራ የሚባል ነገርም የለውም። ምርመራውም ውሳኔውም በዳሬ ሰላም ክልል አስተዳዳሪ የተላለፈ እንደሆነ ተነግሯል። ወንጀላቸው ልግመት ነው፤ ፍርዳቸው ደግሞ የግንባታ ፍጥነቱ እስኪስተካከል ድረስ ሌሊቱን እስር ቤት ማሳለፍ ነው።

የፕሬዝዳንት ማጉፉሊ አስተዳደር የውጭ ሀገራት ኮንትራክተሮችን ውል በማቋረጥና ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን በመውሰድ እየተተቸ ይገኛል። የቻይናዊያኑ እስራትም አስተዳደሩ ያተኩርባቸዋል ከሚባሉት ከሕግ ያፈነገጡ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው እየተባለ ነው።