ለኢንዶኔዢያው ላየን አየረ መንገድ አውሮፕላን አደጋ አየር መንገዱ፣ ቦይንግና አብራሪዎች ተጠያቂ ሆኑ

ኢንዶኔዢያ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የላየን አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የተከሰከሰው አጋጥመውት በነበረው በርካታ ብልሽቶች ነው ሲል የአደጋውን መንስዔ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ጠቆመ።

በአውሮፕላኑን ተሳፍረው የነበሩት 189 በሙሉ የሞቱበት የመከስከስ ምክንያት ቦይንግ፣ አየር መንገዱ እና አብራሪዎቹ በፈጸሟቸው ስህተቶች ነው ብሏል ሪፖርቱ።

የላየን አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከተከሰከሰ ከአምስት ወራት በኋላም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተመሳሳይ አውሮፕላን መከስከሱ ይታወሳል።

ለሁለቱም አውሮፕላኖች መከስከስ የአውሮፕላኑ ዲዛይን እንደ ምክንያት ቀርቦ ነበር።

ዛሬ ረፋድ አውሮፕላኑ የተከሰከሰበትን ምክንያት ሲያጠኑ የነበሩ የኢንዶኔዢያ መርማሪዎች የአደጋው መንስዔ ምን እንደሆነ የሚጠቁመውን የመጨረሻውን የምርመራ ውጤት ይፋ አድርገዋል።

"ለአደጋው ምነስኤ የሆኑ ዘጠኝ ጉዳዮችን ለይተናል" ሲሉ መርማሪ ኑርቻሆ ኡቶማ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"ከዘጠኙ ጉድለቶች አንዱ እንኳ ባይከሰት ኖሮ አደጋው ላይደርስ ይችል ነበር" ሲሉም ተደምጠዋል።

በርካታ ችግሮች የነበሩበት አውሮፕላን በረራ እንዲያደርግ ፍቃድ ሊሰጠው አይገባም ነበር ያለው ሪፖርቱ፤ በአውሮፕላኑ ላይ ሲታዩ የነበሩ ቴክኒካዊ ችግሮች በአግባቡ ተመዝገበው አለመቀመጣቸው ጉድለቶቹ ሳይታዩ አንዲልፉ ሆኗል።

ባለ 353 ገጹ ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ ከአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ከአንድ የጥገና መደብር የተገዛ የአውሮፕላኑ ወሳኝ አካል ፍተሻ ሳይደረግበት አውሮፕላኑ ላይ ተገጥሟል።

ከፍሎሪዳ ተገዝቶ ሙከራ ሳይደረግበት አውሮፕላኑ ላይ እንዲገጠም ተደርጓል የተባለው ቁስ ከኤምካስ ሥርዓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለውም ተጠቁሟል።

ኤምካሳ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ የተገጠመ ሲሆን፤ አውሮፕላኑን በፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ ወደላይ እንዳይወጣ ወይም ወደታች እንዳያሽቆለቁል ለመቆጣጠር እንዲቻል ተብሎ የተሰራ ሥርዓት ነው።

የኢንዶኔዢያ መርማሪዎች እንደሚሉት ከዚህ ሥርዓት ጋር በተያያዘ አውሮፕላኑ በተደጋጋሚ አፍንጫውን ይደፍቅ ነበር። በዚህም አብራሪዎች የአውሮፕላኑን አፍንጫ ከፍ ለማድረግ ብዙ ታግለዋል።

ሪፖርቱ ረዳት አብራሪው በቃሉ ሊያስታውስ ይገባው የነበረውን የአደጋ ጊዜ መመሪያዎች ሳያስታውስ ቀርቷል ይላል። በስልጠና ወቅት ደካማ አቋም አሳይቷል የተባለው ረዳት አብራሪ አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ሲያበር የነበረው እርሱ ነው ተብሏል።

የቦይንግ ምላሽ

ኢንዶኔዢያዊያን መርማሪዎች ቦይንግ ኤምካስ የተባለው ሥርዓቱ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እንዲሁም ስለ መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ በአብራሪዎች መመሪያ ላይ በዝርዝር እንዲያስቀምጥ እና ለአብራሪዎች ስልጠን እንዲሰጥ ምክረ ሃሳብ አቅርበውለታል።

ቦይንግ ከኢንዶኔዢያ መርማሪዎች የተሰጠውን ምክረ ሃሳብ እንደሚቀበል ባውጣው የጽሁፍ መግለጫ ላይ አስታውቋል።

ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን በፈረንጆቹ ቀጣይ ዓመት ወደ በረራ እንደሚመለስ በዚህ ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።

ቦይንግ 737 ማክስ ከሁለቱ አደጋዎች በኋላ ሰማይ ላይ እንዳይታይ እግድ ተጥሎበት ይገኛል።