በተለያዩ ሥፍራዎች ባጋጠሙ ግጭቶች የሟቾች ቁጥር 67 ደርሷል

ከሰሞኑ የተነሳው ግጭት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሰሞኑ በተከሰቱ ግጭቶች የሟቾች ቁጥር ስልሳ ሰባት መድረሱን ሮይተርስ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ግጭቶቹ በተከሰተባቸው ኦሮሚያ ክልል፣ ድሬዳዋ እና ሐረር ከተሞች ስልሳ ሁለት ንፁኃን ዜጎች እንዲሁም አምስት የፖሊስ አባላት መገደላቸውን ኮሚሽነር ከፍያለው ተፈራ ለሮይተርስ ተናግረዋል። ስለ አሟሟታቸውም ተጠይቀው እንደተናገሩት አስራ ሶስቱ በጥይት ሲሆን ቀሪዎቹ 54ቱ ደግሞ በድንጋይ ተደብድበው መሆኑን ዘገባው አስነብቧል።

ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ አስራ ሦስቱ የሞቱት በፀጥታ ኃይሎች እንደሆነና ቀሪዎቹ የግድያ መንስዔ ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭት መሆኑን ኮሚሽነር ከፍያለው ተፈራን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪ 213 ሰዎች መቁሰላቸውንም ይኸው ዘገባ አትቷል።

ከግማሽ በላይ ለሆነው የግድያ መንስዔ ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭት መሆኑን የየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት፣ የሆስፒታል ምንጮች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትናንት ቢቢሲ ከተለያዩ አካባቢዎች ባለሥልጣናት፣ ከሆስፒታል ምንጮችና ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ የሟቾች ቁጥር 44 መድረሱን ዘግቦ ነበር።

አዳማ

ዶ/ር ደሳለኝ ፍቃዱ በአዳማ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ናቸው። ከረቡዕ እስከ ዛሬ (ዓርብ) ድረስ ወደ አዳማ ሆስፒታል ህይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው የመጣ ሰዎች እና የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቶ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር በጠቅላላው 16 መሆኑን ያስረዳሉ።

ዶ/ር ደሳለኝ እንደሚሉት ረቡዕ ዕለት የ3 ሰዎች አስክሬን ወደ ሆስፒታል መጥቷል። ከእነዚህም መካከል ሁለቱ አፍሪካ ዱቄት ፋብሪካ ዘበኛ ጥይት ተኩሶ የገደላቸው ሰዎች ይገኙበታል።

የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ራውዳ ሁሴን የዱቄት ፋብሪካው ጥበቃ ጥይት ተኩሶ ሁለት ሰዎችን መግደሉን እና በዚህ የተበሳጩ ሰልፈኞች በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ 15 መኪኖች ማቃጠላቸውን ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ዶ/ር ደሳለኝ ትናንት ሐሙስ ሆስፒታሉ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ተጎጂዎችን ያስተናገደበት ቀን እንደሆነ ያስረዳሉ። "ትናንት ጉዳት ደርሶባቸው የመጡት ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ይሆናል" ያሉ ሲሆን የጉዳቱ መጠን ከከባድ እስከ ቀላል የሚባል እንደሆነ ያሰረዳሉ።

"በዱላ የተደበደቡ፣ በስለት ጭንቅላታቸው ላይ የተመቱ፣ በጥይት የተመቱ ሰዎችም አሉበት" የሚሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ትናንት ብቻ ህይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው የመጣ እና በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው የያለፈ ሰዎች ቁጥር 12 ነው ይላሉ።

ረቡዕ ዕለት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከፍተኛ የህክምና ክትትል ክፍል (አይሲዩ) ውስጥ የነበረ ወጣት ዛሬ ጠዋት ህይወቱ አልፏል ብለዋል።

"አሁንም በሆስፒታሉ በአደጋኛ የጤና ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አሉ። የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል። አይኑ የጠፋ፣ አጥንቱ የተሰበረ ብዙ ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ እንደሚሉት በከተማው ውስጥ ያለው ግጭት ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ዘልቆ ስለመግባቱም ይናገራሉ። "ወንድሙ የሞተበት አንድ ልጅ አስክሬን ክፍል አቅራቢያ አምርሮ እያለቀሰ ሳለ፤ የተደራጁ ሰዎች የሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሲያለቅ የነበረውን ልጅ ላይ ጉዳት አድረሰዋል" ይላሉ።

ይህ ወጣት የቀዶ ህክምና ከተደረገለት በኋላ የጤናው ሁኔታ መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ የሆስፒታሉ ባልደረቦች ከታካሚ ብዛት እያጋጠማቸው ካለው የሥራ ጫና በተጨማሪ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት መኖሩን ጠቁመው አልፈዋል።

በአዳማ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ ያለ ቢመስልም በግጭት ሳቢያ ጉዳት አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል የመጡ ሰዎች ስለመኖራቸው ዶ/ር ደሳለኝ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ (ቪኦኤ) የአፋን ኦሮሞ ክፍል ሪፖርተር የሆነው ጋዜጠኛ ሙክታር ጀማል በአዳማ ከተማ 'ጀማል መጋዘን' ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በመንገድ ላይ ቃለ-መጠይቅ እያደረገ ሳለ ድብደባ እና ዘረፋ ተፈጽሞበታል።

ጭንቅላቱ እና ወገቡ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ጋዜጠኛ ሙክታር ሆስፒታል ተኝቶ የህክምና አገልግሎት እየተከታተለ ነው።

ሙክታር ቃለ-መጠይቅ እያደረገ ሳለ የተደራጁ ወጣቶች መጥተው ድብደባ እንደፈጸሙበት ያስረዳ ሲሆን፤ "ቦርሳዬን ሲበረብሩ የኢቮኤ መታወቂያ ካርድ ካዩ በኋላ ትተውኝ ሄዱ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የምስሉ መግለጫ,

ጋዜጠኛ ሙክታ ሆስፒታል ተኝቶ የህክምና አገልግሎት እየተከታተለ ይገኛል።

ኮፈሌ

አብነት አክሊሉ በምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ ከተማ ነዋሪ የነበሩ 2 ዘመዶቹ እና አንድ በዘመዶቹ ቤት ስላደገው ወጣት አሟሟት ለቢቢሲ ተናግሯል።

አቶ ታምራት ጸጋዬ የአብነት አክሊሉ አጎት (የእናቱ ወንድም) ናቸው።

ረቡዕ ዕለት በተፈጠረው ግርግር አቶ ታምራት ጸጋዬ፣ ልጃቸው አቶ ሄኖክ ታምራት ጸጋዬ እና በአቶ ታምራት ቤት ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ ሌላ ወጣት ልጅ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መገደላቸውን አብነት አክሊሉ ይናገራል።

"ተሰብስበው ወደ አጎቴ ቤት መጡ። ከዚያ በመጀመሪያ አጎቴን (አቶ ታምራት ጸጋዬ) ገደሉት። ከዚያ በተመሳሳይ ሁኔታ ልጁን ገደሉት። ከዚያ ቤት ውስጥ ያደገ ሱቅ ውስጥ ይሰራ የነበረ ልጅ ገደሉ" ይላል።

አብነት የሟች አስክሬን ላይም አስነዋሪ ድርጊት መፈጸሙን ለቢቢሲ ተናግሯል።

የአቶ ታምራት ልጅ፤ ሄኖክ ታምራት ጸጋዬ በቅርቡ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ በምጣኔ ሃብት ዘረፍ እንደተመረቀ የሚናገረው አብነት፤ አቶ ታምራት በኮፈሌ ከተማ ወፍጮ ቤት፣ ሆቴል እና መኪኖች እንዳሏቸው ይናገራል።

የቤተሰብ አባላቱን ከተገደሉ በኋላ የአቶ ታምራት መኖሪያ ቤት አና መኪና እንደተቃጠለም አብነት ጨምሮ ይናገራል።

የአቶ ታምራት እና የልጃቸው ትውልድ እና እድገት እዛው ኮፈሌ መሆኑን የሚናገረው አብነት "ተወልደው ባደጉበት ኮፈሌ እንኳ መቅበር አልቻልንም። በስንት መከራ ዛሬ በናዝሬት ከተማ 10 ሰዓት ላይ ቀብራቸው ተፈጽሟል" በማለት አብነት ያስረዳል።

የምስሉ መግለጫ,

አምቦ የነበረው ገጽታ

አምቦ

ረቡዕ እና ሐሙስ ዝግ ሆነው የነበሩት መንገዶች ከዛሬ ጠዋት(ዓርብ) ጀምሮ ክፍት ተደርገዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት በነበሩት ግጭቶ 5 ሰዎች ተገደሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንድ የፖሊስ አባል ይገኝበታል። ይህ የፖሊስ አባል የተገደለው ሐሙስ ዕለት ሲሆን ረቡዕ ዕለት በነበረው ግጭት 'ሰው ገድለሃል' ተብሎ በበቀል እርምጃ እንደተገለ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶዶላ

በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ ረቡዕና ሐሙስ በነበሩ ግጭቶች በጠቅላላው 6 ሰዎች መገደላቸውም ታውቋል።

ሐሙስ በነበረ ግጭት 4 ሰዎች ሞተው ወደ ዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል መምጣታቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቶላ ቢዮ ተናግረዋል።

ረቡዕ ደግሞ ሁለት ሰዎች ተገድለው ነበር።

ራቅ ሐረርጌ

ረቡዕ እና ሐሙስ በምስራቅ ሃረርጌ በነበሩ ግጭቶች የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 6 መድረሱን ሰምተናል።

በዞኑ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ አየለ ዴሬሳ፤ በጉሮ ጉቱ 5 እንዲሁም በሃማሬሳ 1 ሰው መገደሉን ተናግረዋል።

አቶ አየለ፤ ትናንት 5ቱ ሰዎች የተገደሉት ጉሮ ጉቱ በምትባል ከተማ ወደ ብሄር በተቀየር ግጭት ስለመሆኑ ይናገራሉ። "አንድ ባለሃብት የደህንነት ስጋት ተሰምቶት ሁለት ሰዎችን በጥይት ተኩሶ ገደለ። ከዚያም በቂም በቀል ግለሰቡ እና ሁለት የቤተሰብ አባላቱ ተገደሉ" ሲሉ ሁኔታውን ለቢቢሲ አስረድተው ነበር።

የአወዳይ ከተማ ነዋሪ የሆነ ወጣት ከመከላከያ ሠራዊት በተተኮሰ ጥይት ስለመገደሉ የአወዳይ ከተማ ከንቲባ ጃፋር ሙሐመድ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ሐረር

በሐረር ከተማ ረቡዕ ዕለት 3 ሰዎች መገደላቸውን ከነዋሪዎች ሰምተናል።

ድሬ ዳዋ

በድሬዳዋ ከተማም ረቡዕ 1 ሰው የተገደለ ሲሆን ዛሬ ደግሞ 4 ሰዎች ተገድለዋል። የድል ጮራ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አብዱራሃማን አቡበከር ለህክምና ከመጡት ሰዎች መካከል 4ቱ ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ባሌ ሮቤ

በባሌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ሮቤ ከተማም ባለፉት ሁለት ቀናት ግጭት ተከስቶ በሰው እና በአካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል። ቢቢሲ በዞኑ በተከሰቱት ግጭቶች በሰው እና በአካል ላይ የደረሰውን ጉዳት ከገለልተኛ አካል ለማጣራት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ይህ የሟቾች አሃዝ ከሆስፒታል ምንጮች፣ ከመንግሥት አካላትና ከሟች ቤተሰቦች የተገኘ ሲሆን ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ስጋት አለ።

መንግሥት በግጭቱ ምክንያት የደረሰው የጉዳት መጠን ምን ያክል እንደሆነ ግልጽ ባያደርግም፤ ግጭት በተከሰተባቸው ስፍራዎች የመከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ መደረጉን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ዛሬ ከሰዓት አስታውቀዋል።

የተቃውሞ ሠልፍ በተካሄደባቸው የኦሮሚያ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ከተሞች በክልሎችና በአስተዳደሩ ጥያቄ መሰረት በአምቦ፣ ቢሾፍቱ፣ ባሌ ሮቤ፣ አዳማ፣ ሞጆ እንዲሁም በድሬ ዳዋ እና ሐረር የመከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ መደረጉን ተናግረዋል።