የዓለማችን ረዥም ሰዓታትን የወሰደው፤ አስደናቂ የአውሮፕላን ጠለፋ

አንድ የአየር መንገድ ኃላፊ የተጠለፈውን አውሮፕላን በመስኮት ሲመለከት

የፎቶው ባለመብት, Bangor Daily News

Presentational white space

ጊዜው እንደ አውሮፓዊያኑ 1960ዎቹ፤ አሜሪካ ውስጥ ቢያስን በስድስት ቀናት አንዴ አውሮፕላን የሚታገትበት ዘመን። የዛሬ 50 ዓመት ታድያ ራፋዔል ሚኒቺዬሎ የዓለማችን ረዥም ጊዜ የወሰደውን ጠለፋ አካሄደ።

ነሐሴ 1962

ደቡባዊቷ የጣልያን ከተማ ኔፕልስ አንዳች ዱብዳ ወደቀባት፤ ምድር ተንቀጠቀጠች። ነገር ግን የአካባቢው ሰዎች አልተደናገጡም። አካባቢው ምድር መንቀጥቀጥ አያጣውም።

ከከተማዋ 20 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ የሚኒቺዬሎ ቤተሰብ ጎጆ መሥርተው ይኖራሉ። ራፋዔል በወቅቱ የ12 ዓመት ታዳጊ ነበር።

የመሬት መንቀጥቀጡ ድጋሚ ተሰማ። አሁን ነዋሪዎች ተሸበሩ። ብሎም ለሦስተኛ ጊዜ ምድር እንደተሰጣ አንሶላ ተርገበገች። የራፋዔል ቤተሰቦች ከአደጋው ቢተርፉም ብቻቸውን ቀሩ። ሊረዳቸው ብቅ ያለ ባለሥልጣንም ሆነ አቅም ያለው አልነበረም።

በርካቶች ሥፍራውን ለቀው ወጡ። ግማሾች ቤታቸውን እንደ አዲስ እያነፁ ሲመለሱ የራፋዔል ቤተሰቦች ግን ወደ አሜሪካ መሄድን መረጡ፤ ለተሻለ ሕይወት። ነገር ግን አሜሪካ በጊዜው ከሁሉም አቅጣጫ ጦርነት የሚሸታት ነበረች፤ ጊዜው የከፋ ነበር።

ጥቅምት መገባደጃ፤ 1969

በወታደራዊ የደንብ ልብስ ያሸበረቀው ራፋዔል ሚኒቺዬሎ ከሎስ አንጀለስ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ ለማቅናት አውሮፕላን ተሳፈረ። 15 ዶላር ከሃምሳ ሳንቲም 'ሆጭ አድርጎ' የከፈለበትን ቲኬት በእጁ እንደጨበጠ።

የአውሮፕላኑ ጋቢና [የበረራ ክፍል] ውስጥ ሦስት አብራሪዎች አሉ። የበረራ አስተናጋጆቹ ደግሞ አራት ጉብሎች። ከእነዚህ ውስጥ በበረራ አስተናጋጅነት የተሻለ ልምድ የነበራት የ23 ዓመቷ ቻርሊን ዴልሞኒኮ ነበረች።

ቲደብሊዩኤ85 [TWA85] አውሮፕላን ከካንሳስ ከተማ ተነስቶ፤ ካሊፎርኒያ አርፎ ነው ወደ ሳን ፍራንሲስኮ የሚያቀናው። ከካንሳስ ከመነሳታቸው በፊት ግን ዋና አብራሪ ዶናልድ ኩክ ለበረራ አስተናጋጆች ከሌላው ጊዜ የተለየ ትዕዛዝ አስተላለፈ። 'ወደ ጋቢና [ኮክ ፒት] መግባት ከፈለጋችሁ ደወሉን ተጫኑ፤ ማንኳኳት አይፈቀድም' የሚል ቀጭን ትዕዛዝ።

አውሮፕላኑ ከመሸ በኋላ ሎስ አንጀለስ ደረሰ። የሚወርዱት ወርደው የሚቀጥሉት ቀጠሉ። አዳዲስ ተሳፋሪዎችም ቲኬታቸውን እያሳዩ ወደ ውስጥ ዘለቁ። ከሁሉም አዳዲስ ተሳፋሪዎች የቻርሊን ዓይን ያረፈው ከራፋዔል ላይ ነው፤ እንዲሁም በእጁ ካንጠለጠለው ቦርሳ ላይ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ቲደብሊዩኤ85 [TWA85]፤ ጩኸታሟ ቦይንግ 707 አውሮፕላን በጠለፋው ወቅት

ጥቅምት 31፤ 1969 ከሌሊቱ 7፡30 አውሮፕላኑ ሎስ አንጀለስን ለቆ ጉዞ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ ጀመረ። 15 ደቂቃ ያክል ከተጓዘ በኋላ የእገታው ድራማ ተጀመረ።

አውሮፕላኑ ተደላድሎ መብረር ሲጀምር የበረራ አስተናጋጆች የመብራት መጠኑን ቀነስ አደርጉት። በርካታ መንገደኞች ወደ ሕልም ዓለም እያቀኑ ቢሆንም ራፋዔል ግን ይቁንጠነጣል። የበረራ አስተናጋጆቹ የአውሮፕላኑን ኩችና በማፅዳት ላይ ናቸው። ይሄኔ ራፋዔል ሄዶ ይቀላቀላቸዋል። ከቦርሳው ውስጥ ኤም1 የተሰኘ መሣሪያ አውጥቶ በእጁ ይዞታል።

«ጌታዬ አውሮፕላን ውስጥ መሣሪያ ይዞ መግባት አይቻልም» ቻርሊን በዝግታ ተናገረች። ራፋዔል እጁን ወደ ቻርሊን ዘረጋ። መዳፉ ውስጥ ያሉትን 7.62 ሚሊ ሜትር ጥይቶች አሳያት። መሣሪያው በጥይት መሞላቱንም ነገራት። ከዚያም ወደ በረራ ክፍሉ እንድትወስደው ነገራት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ቻርሊን ዴልሞኒኮ [በስተቀኝ በኩል] እና የሙያ አጋሮቿ

ከተሳፋሪዎች መካከል የአንድ የሙዚቃ ቡድን አባላት ይገኙበታል። ከአባላቱ አንዱ ዓይኑን እያሻሸ ሲነቃ አንድ ሰው የበረራ አስተናጋጇ ላይ መሣሪያ ደግኖ ይመለከታል። የሚሆነውን ባለማመን አጠገቡ ያሉትን ይቀሰቅሳል። አንድ ተሣፋሪ ይነሳና ራፋዔልን ለመሟገት ይሞክራል።

ይሄን ያስተዋለው ራፋዔል ለቻርሊን ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላልፋል። «ቁሚ!»፤ ቻርሊን፤ ይህ ሰው የምርም ወታደር ሳይሆን አይቀርም ስትል አሰበች።

ከራፋዔል ጋር የተፋጠጠው መንገደኛ ነገሩ መረር ያለ መሆኑን ሲረዳ ወደ መቀመጫው ይመለሳል፤ ራፋዔልም ወደ 'ሥራው'።

ቻርሊን ጉልበቷ እየከዳት ነው፤ ብርክ ብርክ ብሏታል። ወደ ደረጃ አንድ [ቢዝነስ ክፍል] ደረሱ። ቻርሊን ከፊቷ ላሉ ሰዎች መልዕክት እያስተላለፈች መንገዷን ቀጠለች። «ገለል በሉ! ከኋላዬ መሣሪያ የታጠቀ ሰው አለ» እያለች።

'ሥራውን' በፀጥታ ሲከውን የነበረው ራፋዔል ቁጣ ይቀድመው ጀምሯል። ልክ በረራ ክፍሉ ሲደርሱ ቻርሊን ካፕቴኑ የሰጣት ትዕዛዝ ትዝ አላት። ነገር ግን ራፋዔል ስላልፈቀዳላት የግዴታውን ታንኳኳለች።

ምናልባት ትዕዛዝ መጣሷ አብራሪዎቹ የሆነ ነገር ቢኖር ነው ብለው እንዲጠራጠሩ ያግዛል ብላ አሰበች። ነገር ግን በሩ ተከፈተ። ከኋላዋ ተሸክማ የመጣችውን ጉድ ለአብራሪዎቹ ሹክ አለች። ራፋዔል ቻርሊንን ወደ ጎን ገለል አድርጎ አፈሙዙን አብራሪዎቹ ላይ አነጣጠረ። ከዚያም አጠር ያለ ትዕዛዝ ሰጣቸው። «አቅጣጫችሁን ወደ ኒው ዮርክ አድርጉ።»

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የኤፍ ቢ አይ ልዩ መኮንን ስኮት ዌርነር ከቻርሊን የተቀበለው ቀለህ

ታድያ ይሄ ሁሉ ሲሆን እንቅላፋቸውን እየለጠጡ ያሉ ብዙ መንገደኞች ነበሩ። የባንዱ አባላት አንድ ላይ ተሰባስበው በሁኔታው መገረም ያዙ። እንዴት አድርጎ ያን የሚያህል መሣሪያ ይዞ ሊገባ ቻለ? ወደየት ሊወስዳቸው አስቦ ይሆን?

ከተሣፋሪዎቹ መከካል ጁዲ ፕሮቫንስ ትገኛለች። የበረራ አስተናጋጅ ናት። ነገር ግን ሥራ ላይ አይደለችም። በአደጋ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባት ሥልጠና ወስዳለች።

ሌላኛው ደግሞ ጂም ፊንድሌይ ነው። ቀደም ሲል ከራፋዔል ጋር አንገት ለአንገት ካልተናነቅሁ ያለው ግለሰብ። ጂም አብራሪ ነው። ተራ ሰው መስሎ እየተጓዘ ቢሆንም። ወደ ጠላፊው ቦርሳ ያመራና መበርበር ይጀምራል። ማንነቱን ለማጣራት፤ አልፎም ሌላ የጦር መሣሪያ አለመኖሩን ለማወቅ። ጥይት የተሞላ ካርታም አገኘ።

ካፒቴን ኩክ ድምፁ በማጉያው ተሰማ። «አንድ የደነገጠ የሚመስል ወጣት ሰው እዚህ አለ። ወደ ሚፈልገው ቦታ እንወስደዋለን።»

ጊዜው ከላይ እንደተጠቀሰው የአውሮፕላን ጠለፋ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚሰማበት ነው። ለዚህም አየር መንገዶች የነበራቸው የላላ ጥበቃ ዋነኛው ምክንያት ነበር።

የመንገደኞች ሻንጣ የመፈተኛ መሣሪያ ዘግይቶ ነበር ወደ ሥራ የገባው። ለነገሩ በጊዜው አውሮፕላን የጠለፉ ቢበዛ ኩባ ሄደው ቢቀሩ ነው እንጂ ማፈንዳት የሚባል ነገር አልነበረም።

ኋላ ላይ የወጡ ምርመራዎች ራፋዔል መሣሪያውን ከፈታታው በኋላ በቱቦ መሰል ዕቃ ውስጥ አድርጎ ነው ወደ አውሮፕላኗ የገባው። መሣሪያውን የገጣጠመውም የአውሮፕላኑ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ነበር። የቦርሳ ፍተሻ እንደ አሁኑ አለመሆኑ ለራፋዔል መልካም አጋጣሚ ነበር።

በ1969 ላይ ብቻ አሜሪካ ውስጥ 54 አውሮፕላኖች ተጠልፈዋል። የትኛውም ጠላፊ ግን አውሮፕላን ጠልፎ ከአህጉረ አሜሪካ ወጥቶ አያውቅም።

ጠላፊው ራፋዔል ወደ ኒው ዮርክም ወደ ሮምም መሄድ ፈልጓል። ግራ ተጋብቶ አብራሪዎቹን ግራ አጋብቷቸዋል። ታድያ ሁለቱም የሚቻል አልነበረም። ወደ ኒው ዮርክ እንዳይሄዱ በቂ ነዳጅ የላቸውም፤ ወደ ሮም እንዳይገሰግሱ ሁሉም ከአህጉረ አሜሪካ ውጭ አብርረው አያውቁም፤ ልምዱ የላቸውም።

ኋላ ላይ ግን ስምምነት ላይ ደረሱ። ዴንቨር፤ ኮሎራዶ አርፈው ነዳጅ ለመቅዳት። ታድያ ነዳጅ እየቀዱ ሳለ ካፕቴን ኩክ ለበላይ አለቆቹ ችግር እንዳጋጠመው ሹክ ይላል።

ራፋዔል ዕቅዱን ቀየረ። 39 ተሣፋሪዎችን ዴንቨር ላይ እንዲወርዱ ማድረግ። ትሬሲ ኮልማን ከአንዷ በስተቀር የበረራ አስተናጋጆችንም እንዲሁ።

መንገደኞች መውረድ ሲጅምሩ ፊንድሌይ መውጭው ላይ ሲደርስ ''ዕቃ ረሳሁኝ፤ ተመልሼ ልውሰድ ወይ?'' ሲል ጠላፊውን ይጠይቃል። ጠላፊውም ይፈቅድለታል። ሰዓቱ ሌሊት 10 ሰዓት ገደማ በመሆኑ ይህ ሁሉ ሲካሄድ ገና ጎህ አልቀደደም ነበር።

መንገደኞቹ ሲወጡ የጠበቃቸው የወዳጅ ዘመድ ፈገግታ አልነበረም። የኤፍቢአይ መኮንኖችና ብዕራቸው እንጂ።

የፎቶው ባለመብት, Denver Post/Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የሙዚቃ ቡድኑ አባላት በዚህ ጠለፋ ምክንያት ታዋቂ መሆን ችለዋል

አውሮፕሏኑ ከዴንቨር ከተነሳ ሦስት ሰዓት አለፎታል። አውሮፕሏኗ ውስጥ የቀሩት አምስት ሰዎች ብቻ ናቸው። ዋና አብራሪ ኩክ እና ሁለት ረዳቶቹ፣ የበረራ አስተናጋጇ ትሬሲ እና ጠላፊው ራፋዔል።

አውሮፕሏኑ ኒው ዮርክ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አውሮ ፕላን ማረፊያ በሰላም አረፈ። ከሌሎች አውሮፕላኖች ራቅ ብሎም እንዲቆም ተደረገ። 100 ግድም የኤፍቢአይ መኮንኖች አለባበሳቸው እንደ መካኒክ እንዲሁም ዕቃ አውራጅ እና ጫኝ መስለው በተጠንቀቅ ቆመዋል። ሃሳባቸውም እንደ እባብ ተሹለኩልከው ወደ አውሮፕላኑ መግባት ነው።

አውሮፕላኑ ነዳጅ ሊሞላ ዝግጅት ላይ ሳለ አንድ መኮንን ወደ አውሮፕላኑ ጠጋ አለ። ጠላፊው አነጣጥረው እንዳይነድሉት በማሰብ ወደ መስኮቶች ቀረብ ላለማለት ወስኗል። ካፒቴኑም ለመኮንኖቹ ወደ አውሮፕላኑ እንዳይጠጉ በዓይኑ ምልክት ሰጠ። ድንገት የጥይት ድምፅ ተሰማ።

የፎቶው ባለመብት, Bangor Daily News

ድንጋጤው በረድ ሲል ታድያ ጠላፊው ጥይት እንደባረቀበት ታወቀ። ነገር ግን በሰውም ላይ ሆነ አውሮፕላኗ ላይ ጉዳት አልደረሰም። ጥይቱም የአውሮፕላኗን ጣራ ዘልቆ መሄድ አልቻለም። ይህ ቢሆን ኖሮ ግን የራፋዔል ዕቅድ በእንጭጩ በቀረ ነበር። አሁን አብራሪዎቹ ድንጋጤ ገባቸው። ነገሩ ቀላል እንዳልሆነ ይገባቸው ጀመር።

ሁለት የዓለም አቀፍ በረራ ልምድ ያላቸው አብራሪዎች ወደ አውሮፕላኗ ዘለቁ። ጠላፊው ሁሉም አብራሪዎች እጃቸውን ወደ ላይ ሰቅለው አብራሪ ክፍል ውስጥ አርፈው እንዲቀመጡ አዘዘ።

አውሮፕላኑም አኮብኩቦ ተነሳ። የያዘው ነዳጅ ግን ሮም የሚያደርስ አልነበረም። አትላንቲክን ማቋረጥ የሚያስችል ነዳጅ ለመሙላት ሜይን የተሰኘ ከተማ ላይ አረፈ። ከዚያም በማስከተል ጉዞ ወደ ሮም ሆነ።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ከጠለፋው ውጭ ለሌላ ርዕስ ዓይንና ጆሮ የለንም አሉ። አዲሶቹ አብራሪዎች አውሮፕላኑን መዘወር ያዙ። ዋና አብራሪ ኩክ ጠላፊው ጋር ቁጭ ብሎ ወጉን ይጠርቅ ያዘ።

ራፋዔል መሣሪያውን ጭኖቹ ላይ አስደግፏል። ማንም የጠላፊውን መሣሪያ ደፍሮ መቀማት አልሻተም። ነገሮች እንዳልነበር እንደሚሆኑ ሁሉም ገብቷቸዋል። ጠላፊው አብራሪዎቹ አግብተው እንደሆነ ሲጠይቅ ኩክ "አዎ ሁላችንም አግብተናል" ሲል መለሰለት። እንደው ቢራራልን ብሎ እንጂ ከአንዱ በቀር ሁሉም ጎጆ ያልወጡ ናቸው።

ከሜይን ወደ ሻነን፤ አየርላንድ፤ የስድስት ሰዓታት በረራ። ሻነን ማረፍ ያስፈለጋቸው ነዳጅ ለመቅዳት ነበር። አውሮፕሏኗ ውስጥ ብስኩታብስኩት እንጂ ደህና ምግብ አልነበረም። ነገር ግን ማንም በሕይወት ስለመቆየት እንጂ ስለ ምግብ አላሰበም።

አውሮፕላኑ አየርላንድ ሲደርስ ጥቅምት አልፎ ኅዳር ገባ። አውሮፕላኑ ከተጠለፈ 18 ሰዓታት አልፏል።

ኅዳር መባቻ ቲደብሊዩኤ85 [TWA85] አውሮፕላን ሮም ፊዩሚቺኖ አየር ማረፊያ ደረሰ። የ20 ዓመቱ ራፋዔል ሚኒቺዬሎ አውሮፕላኑ ራቅ ብሎ እንዲቆምና ያልታጠቀ ፖሊስ መጥቶ እንዲያናግረው አንድ የመጨረሻ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

18 ሰዓት ሰላሳ ደቂቃ በኋላ ጠለፋው ሊጠናቀቅ ሆነ። ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ክስተቱን 'የዓለማችን ረዥም ሰዓት የወሰደ፤ አስደናቂ አውሮፕላን ጠለፋ' ሲል በፊት ገፁ አተመ።

በጠላፊው ጥያቄ መሠረት አንድ ያልታጠቀ ሰው ቀረበ። ጠብመንጃውን እንደታጠቀ ሰውዬውን ተከትሎ ወደ አንድ መኪና ሄደ። ታድያ ራፋዔል አውሮፕላኑን ለቆ ሲወጣ ግን አብራሪዎችን ይቅርታ ጠይቆና አመስግኖ ነበር።

«ወደ ኔፕልስ ውሰደኝ» ራፋዔል አዲሱን ታጋች አዘዘው።

መኪናዋ ጉዞዋን ቀጠለች። ነገር ግን አንድ ቦታ ላይ መፈናፈኛ ስታጣ ጊዜ ራፋዔል ከመኪናዋ በመውጣት ይጠፋል። ከመቶ በላይ ፖሊሶች ፍለጋቸወን በሄሊኮፕተር እና በውሾች ታግዘው ቢያደርጉም ደብዛው ጠፋ። አምስት ሰዓታት አለፉ።

ታድያ ራፋዔልን ያገኙት ፖሊሶች ሳይሆኑ አንድ ቄስ ነበሩ። ቤተክርስትያን ተጠልሎ የነበረው ራፋዔል በጣልያን የፖሊስ ኃይል ተከበበ። ይሄኔ ጠላፊው ለአገሩ ሰዎች አንድ ጥያቄ ሰነዘረ።

«የሃገሬ ሰዎች ስለምን ልታሰሩኝ ፈለጋችሁ?»

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ሚኒቺዬሎ ከታሠረ በኋላ ሮም ውስጥ፡ "የምን አውሮፕላን? ምን እንደምታወሩ አላውቅም"

ራፋዔልን ጋዜጠኞች ከበው ሲጠይቁት 'እኔ ስለምን ጠለፋ እንደምታወሩ አላውቅም' ሲል ካደ። ኋላ ላይ ግን ለምን አውሮፕላን መጥለፍ እንዳስፈለገው እውነቱን አወጣ።

ራፋዔል ሚኒቺዬሎ የቪዬትናም ጦርነት ላይ የአሜሪካን ወታደራዊ የደንብ ለብሶ ተዋግቷል።

የፎቶው ባለመብት, Raffaele Minichiello

የምስሉ መግለጫ,

ራፋዔል ሚኒቺዬሎ የቪዬትናም ጦርነት ላይ የአሜሪካን ወታደራዊ የደንብ ለብሶ ተዋግቷል

ራፋዔል አሜሪካ የገባው ግንቦት 1967 (እአአ) ነበር። ማረፊያው ደግሞ ሲያትል። ከአምስት ዓመታት በኋላ ታድያ በውዳጅ ወታደር ሆኖ ለአሜሪካ ለመዋጋት ወደ ቪዬትናም ያቀናው። ቪዬትናም ካቀና በኋላ ታድያ ያሰበው አልጠበቀውም። በጣም አሰቃቂ ጊዜ አሳልፏል።

ይህን የሚተርኩት አብረውት የተዋጉት የትግል አጋሩ ተርነር ናቸው። 'ያሳለፍነው አይነገር' ይላሉ ተርነር። የዚያን ጊዜው ወጣት ተርነር፤ ራፋዔል አውሮፕላን ጠለፈ የሚለውን ዜና ሲሰሙም ብዙ አልደነቃቸውም። በእርግጠኝነት በጦርነቱ ምክንያት አዕምሮው ተነክቷል ብለው ነው ያሰቡት።

የአሜሪካ የቀድሞ ወታደሮች ማሕበር ቢያንስ 30 በመቶው በቪዬትናም ጦርነት ላይ የተሳተፉ ወታደሮች የአዕምሮ ጤና መቃወስ አጋጥሟቸዋል ሲል ግምቱን ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ ወደ 810 ሺህ የሚጠጋ ወታደር ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ራፋዔል 2008 ዓመተ ምሕረት ላይ ነው የአዕምሮ ጤና ሕክምና የተደረገለት።

በካንሰር በሽታ ምክንያት ወደ ኔፕልስ ተመልሰው ኑሯቸውን በመግፋት ላይ የነበሩት የራፋዔል አባት ሉዊጂ ሚኒቺዬሎ ያኔ እንዲህ ብለው ነበር። «ልጄ ይህን ለምን እንዳደረገ አውቀዋለሁ። ጦርነቱ አዕምሮውን አቃውሶታል። ወደ ቤቱ መመለስ ፈልጎ ነው።»

ታድያ ትንሽ ቆይቶ ራፋዔል አውሮፕላኑን ሊጠልፍ የቻለበት ሌላ ምክንያት ብቅ አለ። ጦርነት ላይ ሆኖ ያጠራቀመው 800 ዶላር ወደ ቤቱ ሲመለስ 600 መቶ ሆኖ ጠበቀው። ይህ ደግሞ በካንሰር ምክንያት ሊሞቱ እያጣጣሩ የነበሩትን አባቱን ለማዬት በቂ ገንዘብ አልነበረም።

200 ዶላር ጨምሩልኝ ብሎ ለበላይ አለቆቹ ቢያመለክትም በዚያ ቀውጢ ዘመን የሚሰማው አልነበረም። ወደ አንድ ሱቅ ሄዶ 200 ዶላር ለመስረቅ ሞክሮም አልተሳካለትም። ይልቁንም ተይዞ የካቴና ሲሳይ ሆነ።

ክስ ቀርቦበት፤ በቀጠሮ ዳኛ ፊት እንዲቀርብ ተወስኖ ተለቀቀ። የቀጠሮው ቀን ደግሞ ከጠለፋው አንድ ቀን በኋላ ነበር። ይሄኔ ነው ከቪዬትናም ይዞት የመጣውን ጠብመንጃ ይዞ ወደ ሎስ አንጀለስ የሸሸው።

ታድያ ራፋዔል ጣልያን ውስጥ እንደ ጀግና ነበር የታየው። የአዕምሮ ጭንቀት እንዳለበት አንድ ወጣት ሳይሆን በምድር ገስግሶ፤ ዳመናውን ጥሶ፤ አገሩን ብሎ የመጣ ወጣት። ቢሆንም ከፍርድ አላመለጠም። ነገር ግን ወደ አሜሪካ መልሰው ሊሰዱት አልፈቀዱም።

ራፋዔል በጣልያን የአየር ክልል ውስጥ ብቻ የፈፀመው ወንጀል ታይቶ የሰባት ዓመት ተኩል ቅጣት ተፈረደበት። ወዲያውም ፍርዱ እንዲቀል ተደርጎ ከሁለት ዓመት በኋላ [ግንቦት 1971] ተለቀቀ።

የፎቶው ባለመብት, Otis Turner

የምስሉ መግለጫ,

ራፋዔል ሚኒቺዬሎ [በስተግራ በኩል] እና ኦቲስ ተርነር [በስተቀኝ] ከሌሎች የጦር አውድማ ጓዶቻቸው ጋር

ከዚያም መኖሪያውን ሮም በማድረግ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ሰራተኛ ሆኖ ኑሮውን ይገፋ ጀመር። የመጠጥ ቤቱን ባለቤት ልጅም አግብቶ ልጅ ወልደ። አንድ ሰሞን ፒዛ ቤት ከፍቶ ነበርም ይባላል። የፒዛ ቤቱን የንግድ ስም 'ሃይጃኪንግ' [መጥለፍ] ብሎ ሰይሞትም ነበር።

ከጠለፋው 30 ዓመታት በኋላ በ1999 (እአአ) ራፋዔል ሚሊቺዬኖ ወደ አሜሪካ ተመለሰ። እዚያም ከጠለፋው ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ክስ አልጠበቀውም። ነገር ግን ከጠለፋው በፊት በፈፀመው አነስተኛ ወንጀል ምክንያት ወታደራዊ ታሪኩ እንዲፋቅ ተደረገ።

ታድያ አሜሪካ የመጣው በዓላማ ነበር፤ በጠለፈው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ሰዎችን እያገኘ ይቅርታ መጠየቅ። ይህን ማድረግ ያሰበው ደግሞ ከጦር አውድማ ጓደኞቹ ጋር በመሆን ነበር።

የበረራ አስተናጋጆች እና የተወሰኑ አብራሪዎችን አግኝቶ ይቅርታ ጠይቆ ይቅርታ መቀልም ቻለ። ቢቢሲ ራፋዔልን ለማናገር ጥረት ቢያደርግም ታሪኩን በፊልም መልክ ለመሰነድ ዕቅድ ከያዘ ድርጅት ጋር በመዋዋሉ ምክንያት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።