ዴኒስ ንክሩንዚዛ፡ የብሩንዲ ቀዳማዊት እመቤት በመካኖች ላይ የሚደርስን ጥቃት በመቃወም አቀነቀኑ

የብሩንዲ ቀዳማዊት እመቤት ዴኒስ ንክሩንዚዛ

የፎቶው ባለመብት, Papy Jamaica

የብሩንዲ ቀዳማዊት እመቤት ዴኒስ ንክሩንዚዛ የልጅ እናት መሆን ባልቻሉ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም ለሚካሄደው ዘመቻ አቀንቅነዋል።

የሙዚቃው ትዕይንት አንዲት ሚስት ባሏ ከደጅ ወደ ቤት ሲገባ ስትቀበለውና እራት እንዲመገብ ስትጋብዘው፤ ከዚያም በተጀመረ ጭቅጭቅ ሲደበድባት በማሳየት ይጀምራል።

"በዚህ ቤት ውስጥ አንቺ ምንም እርባና የሌለሽ ሴት ነሽ" ይላል ባልየው።

"የሌሎች ሴቶች ሆድ በህፃናት ሲያዝ፤ የአንች ሆድ ግን ሁል ጊዜ የሚሞላው በጥራጥሬ ነው" ሲልም ይዘልፋታል።

ከዚያም የ49 ዓመቷ ቀዳማዊት እመቤት ዴኒስ፤ ነገር ለማብረድ ወደ ጥንዶቹ ሳሎን በማምራት ጣልቃ ይገባሉ።

"ስለ መካንነት ማወቅ የሚቻለው ዶክተር ካማከርን በኋላ ነው" ሲሉ ሲያሸማግሉ ይሰማሉ።

"መካንነት በሴትም ሆነ በወንድ ላይ ሊከሰት ይችላል" ሲሉም ያክላሉ።

በቀጣዩ ትዕይንት ላይ ደግሞ ቀዳማዊት እመቤቷ ከሌሎች ሙዚቀኞች ፣ ዳንሰኞችና ጋር ሲዘፍኑ ይታያሉ። "ሴቶች የተፈጠሩት እናት ለመሆን ብቻ አይደለም፤ ከዚህ በላይ መሆን ይችላሉ" ተቀባዮቹ ይከተላሉ።

ከጎርጎሳውያኑ 1994 ጀምሮ ከፕሬዚዳንት ፔሬ ኑክሪንዚዛ ጋር በትዳር ተጣምረው የሚኖሩት ቀዳማዊት እመቤት ዴኒስ፤ ባሎች ለሚስቶቻቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

"መካንነት ሁለቱንም ጥንዶች የሚመለከት ሲሆን ፤ የግጭት መነሻም መሆን የለበትም' ሲሉ አዚመዋል።

የአምስት ልጆች ወላጆችና በርካታ ልጆችን በማደጎ ያሳደጉት ጥንዶቹ ፕሬዚደንት ፔሬ ንክሩንዚዛ እና ዴኒስ ንክሩንዚዛ ፤ ኃይማኖታዊ በመሆናቸውና መደበኛ የፀሎት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ይታወቃሉ።

የስደተኛ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት ቀዳማዊት እመቤቷ ሰባኪም ነበሩ።

አሁን በቅርቡ ያወጡትና 'ሴቶች ልጅ ከመውለድም በላይ ናቸው' የሚለው ዜማቸው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በዋትስ አፕ' የተለቀቀ ሲሆን በእንዲህ ዓይነት ተንቀሳቃሽ ምስል ዓለማዊ መዝሙር ሲዘምሩም ይህ የመጀመሪያቸው ነው ተብሏል።

የ4 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ይሄው ሙዚቃ በፌስቡክ ገፆችም ላይ ተንሸራሽሯል።

ቀዳማዊት እመቤቷ አሁን በለቀቁት ሙዚቃ ከማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ምስጋና የተቸራቸው ቢሆንም፤ አንዳንዶች ግን ጥቃቱ በተመሳሳይም በወንዶችም ላይ ይፈፀማል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በብሩንዲ አባታዊ ስርዓት [የወንዶች የበላይነት የሰፈነበት] ማህበረሰብ ጥንዶች ጋብቻ ከመሠረቱ በኋላ ልጆች መውለድ ካልቻሉ በራሳቸው እንዲያፍሩ እና እንዲሸማቀቁ ተፅዕኖ ይደረግባቸዋል። በአብዛኛው የመካንነት ምንጯም ሴቷ ችግር እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል።

አንዳንድ ጥንዶችም በዚህ ምክንያት ለመለያየት ይገደዳሉ።