ግሬታ ተንበርግ፡ አዲስ የጥንዚዛ ዝርያ በአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ስም ተሰየመች

አዲስ የተገኘችው የጥንዚዛ ዝርያ በአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ግሬታ ተምንበርግ ስም ተሰየመች። ግሬታ ተንበርግ የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ ሰልፍ በመጥራት ያስተባበረች ታዳጊ ስትሆን፤ ሰልፉ ከአውስትራሊያ እስከ ኒውዮርክ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንደተሳተፉበት ተነግሯል።

ይህ ሰልፍ፤ የሠው ልጅ ያስከተለውን የዓለም ሙቀት መጨመር በመቃወም የተደረገ ትልቁ ሠልፍ ነው ተብሏል። የተመራውም በታዳጊዋ ግሬታ ተንበርግ ነበር።

የ16 ዓመቷ ግሬታ በዘንድሮው የኖቤል የሠላም ሽልማትም ያሸንፋሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል ነበረች።

በአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ስም የተሰየመችው 'ኒሎፕቶድስ ግሬቴ' የተሰኘችው ጥንዚዛ ቁመቷ ከአንድ ሚሊ ሜትር ያነሰች ስትሆን፤ ክንፍም ሆነ ዐይን የላትም።

እንደ አንቴና ያሉ ሁለት ረጅም የአሳማ ዓይነት ጅራቶች አሏት።

ተመራማሪው ዶክተር ማይክል ዳርቢይ ስያሜውን ለምን እንደመረጡት ሲናገሩ፤ በስዊድናዊቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአጭሩ 'ኤን ግሬቴ' የተባለችው ነፍሳት ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓዊያኑ 1960 በዊሊያም ብሎክ በኬንያ የተገኘች ሲሆን፤ ናሙናዎቹንም እአአ በ1978 በለንደን ለሚገኝ የተፈጥሯዊ ታሪክ ሙዚየም ለግሰዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሙዚየሙ ውስጥ ተቀምጣ ትገኛለች።

ዶክተር ማይክል ስም ያልተሰጣቸው [ስም የለሽ] የሆኑ ዝርያዎችን በሚያጠኑበት ወቅት የእነዚህንም ነፍሳቶች ዝርያ ስብስብ ሲያጠኑ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ግሬታ ተንበርግ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ የተቃውሞ እንቅስቀሴን መርታለች

አዲስ የተገኘችውን ጥንዚዛ በታዳጊዋ ግሬታ ስም በመሰየም አካባቢን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ያደረገችውን አስደናቂ አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠት እንደፈለጉ ተመራማሪው አስረድተዋል።

አሁን ጥንዚዛዋ በ'ኢንቶሞሎጅስቶች' [የነፍሳት ተመራማሪዎች] ወርሃዊ መፅሔት ላይ ስሟ በይፋ ሰፍሯል።

ሙዚየሙ ውስጥ ያሉትን ጥንዚዛዎች ላይ ክትትል የሚያደርጉት ዶክተር ባርክሌይ በበኩላቸው፤ የተሰጠው ስም ተገቢ ነው ይላሉ። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም "ያልተለዩ ዝርያዎች ሁል ጊዜ የመጥፋት እድላቸው የሰፋ ነው ፤ የሚጠፉትም ተመራማሪዎች ለእነሱ ስም ከመስጠታቸው በፊት ነው" ምክንያቱም የብዝሃነት እጦት ነው" ብለዋል።

በመሆኑም ይላሉ ዶክተር ባርክሌይ "አዲስ ግኝቱ ለአደጋ የተጋለጡ ዝርያዎችን ለመጠበቅ ለአየር ንብረት ለውጥ ተግታ በሠራችው ታዳጊ ስም መሰየሙ ተገቢ ነው" ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።

ስማቸው ለእንስሳት መጠሪያ የዋለ ዝነኞች እነማን ናቸው?

ለተመራማሪዎች አዲስ የተገኙ ዝርያዎችን ስያሜ መስጠት ቀላል አይደለም ፤ አዲስ ፈጣሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

"አንድ ጥገኛ ተህዋስ የእውቁን ጃማይካዊ የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ የቦብ ማርሌን ስያሜ አግኝቷል 'ግናሺያ ማርሌይ' በሚል። ሌላ የአሳ ዝርያም ከእንግሊዛዊው የእንስሳት ባህርይ፣ ዝግመተ ለውጥ እና የሥነ ሕይወት ተመራማሪ ሪቻርድ ዳውኪንስ ስም 'ዳውኪንሺያ' ተብሎ ይጠራል። በአንድ አነስተኛ ፓርክ የሚገኙ በሕይወት የሚገኙና የጠፉ ዝርያዎችም በእንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ዴቪድ አቶንቦሮው ተሰይመዋል።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ዴቪድ አቶንቦሮው ተከታታይ በሆኑትና የተፈጥሮ ታሪኮችን በተመለከቱ ዘጋቢ ፊልሞች ይታወቃሉ።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተመራማሪዎቹ በሚያደንቋቸው ዝነኞችን እና እውቅ ሰዎች እንስሳትን ይሰይማሉ። ለምሳሌ በአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግ እንደተሰየመችው 'ኤን ግሬቴ' የተሰኘች ይህችን ጥንዚዛ ወይም በእውቁ አሜሪካዊ ተዋናይና የአካባቢ ጥበቃ አምበሳደር ሊኦናርዶዲካርፒዮ ስም 'ስፒንታረስ ሊኦናርዶዲካርፒዮ' እንደተባለው ሸረሪት።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ዝነኞች በተለየ ከሚወዷቸው እንስሳት ጋር በማያያዝ ስያሜው ይሰጣሉ። 'ሌሙር' ተብለው የሚታወቁት እንስሳት በእንግሊዛዊው ተዋናይ እና ኮሜዲያን ጆን ክሊስ ስም 'አቫሂ ክሊሲ' ተብለው ይጠራሉ።

ሌላኛው ደግሞ የእንስሳቶቹ መልክ ከዝነኞቹ ጋር ተቀራራቢነት ካለው በዚያ ሰው ስም ይሰየማሉ።

ለምሳሌ ወርቃማ ፀጉር ያለው ዝንብ በአሜሪካዊቷ ድምፃዊና ተዋናይት ቢዮንሴ 'ስካፕሺያ ቢዮንሴ' ተብሎ ተሰይሟል።

'ኒኦፓልፓ ዶናልድ ትራምፒ' ም ተብሎ በአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስም የተሰየመ የእሳት እራት አለ። ስያሜው በሥነ ሕይወት ተመራማሪው ቫዝሪክ ናዛሪ ከሁለት ዓመታት በፊት የተሰጠ ነው። የእሳት እራቱ ወርቃማ ጭንቅላት ያለው ሲሆን በአንፃራዊነት ትንሽ የመራቢያ አካል ያለው ነው።

ባሳለፍነው ዓመት ሌላ እንስሳም በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ተሰይሟል። እንስሳው በአሸዋ ውስጥ ጭንቅላቱን በመቅበር የሚታወቀው የውሃ ውስጥ እንስሳ ነው። 'ዘ ደርሞፊስ ዶናልድ ትራምፒ' የተባለው እንስሳ ይህንን ስያሜ ያገኘው ፕሬዚደንቱ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ ነው።

የቤት እንስሳትም ቢሆኑ የራሳችሁን ስም ካለወጣችሁላቸው በስተቀር በሳይንሳዊ መንገድ የተሰጣቸውን ስም ይዘው መቀጠላቸው እሙን ነው።

ታዲያ አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ስያሜ መስጠት አደገኛ ሊሆን ይችላል። ዐይነ ስውር የዋሻ ጥንዚዛ 'አኖፍታልመስ ሂትለሪ' ተብሎ በአውሮፓዊያኑ 1933 በጀርመናዊ አድናቂው አማካኝነት በናዚ ፓርቲ መሪና ፖለቲከኛ በነበረው አዶሊፍ ሂትለር ስም ከተሰየመ በኋላ ስሙን ይዞ ቀጥሏል።