ኬንያዊው የፀረ ቅኝ ግዛት ነፃነት ታጋይ ዴዳን ኪማቲ መካነ መቃብር ከ62 ዓመታት በኋላ ተገኘ

የነፃነት ታጋይ ዴዳን ኪማቶ Image copyright Authenticated News

በኬንያ ቅኝ ግዛትን የመዋጋት ታሪክ ከፍተኛ ሥፍራ ያለው የነፃነት ታጋይ ዴዳን ኪማቲ ከሞተ 62 ዓመታት በኋላ የተቀበረበት ሥፍራ መገኘቱን በስሙ የተቋቋመው አንድ ፋውንዴሽን አስታውቋል።

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1950ዎቹ ኬንያ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ሥር ነፃ ለመውጣት ይታገል የነበረው የማው ማው እንቅስቃሴንም ይመራ ነበር። በጎርጎሳውያኑ 1957ም በእንግሊዞች ተገደለ።

ናይሮቢ በሚገኘው ካሚቲ እስር ቤት ውስጥ ቢቀበርም ትክክለኛ ሥፍራው አይታወቅም ነበር።

"ሌቱም አይነጋልኝ" የተባለላት የውቤ በረሃ ትዝታዎች

ማንዴላን ውትድርና ያሰለጠኑት ኢትዮጵያዊ

ዘ ዴዳን ኪማቲ ፋውንዴሽን እንዳሳወቀው የተቀበረበት ሥፍራ ታውቋል ብሏል። እንዴት ሥፍራው እንደተገኘ እንዲሁም ትክክለኛ ቦታ መሆኑን በምን መንገድ ተረጋገጠ የሚሉት ጉዳዮች ግልፅ አልተደረገም።

ፋውንዴሽኑ አርብ እለት በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው ለዴዳን ኬማቲ ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለነፃነት ታጋይ ጀግኖች ትልቅ ዜና ነው።

ለረዥም ጊዜያት ነፃነት ታጋዩን የቀብር ሥፍራ ለማወቅ ብዙ ሙከራ ተደርጓል። በተለይም በጎርጎሳውያኑ 2003 ሥልጣን ላይ የመጡት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ የቀብር ሥፍራውን ማግኘት ዋነኛ ቀዳሚ ስራቸው መሆኑን ቃል ገብተው ነበር።

በባርነት ከመሸጥ የተረፉት 64 ኢትዮጵያዊያን

በተቀበረበት ወቅት አይተናል የሚሉ እማኞችም በተለያዩ ጊዜያት የመቃብር ሥፍራውን እናውቃለን በማለት ባለሥልጣናትን ቢያሳዩም ሳይሳካ ቀርቷል።

መንግሥትም በበኩሉ በአጠቃላይ የማው ማው ነፃነት ታጋዮች ለነበሩ በሙሉ በናይሮቢ የክብር ሀውልት አቁሞላቸዋል።