ዚምባብዌውያን በሃገሪቷ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በመቃወም ሰልፍ አካሄዱ

ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሺዎች የሚቆጠሩ ዚምባብዌውያን የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረትን ማዕቀብ በመቃወም ሰልፍ አድርገዋል።

መንግሥት ባዘጋጀው በዚህ ሰልፍ ማዕቀቡ ምን ያህል የዚምባብዌን ኢኮኖሚ እንዳሽመደመደው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት የተጣለው ማዕቀብ በግለሰቦችና በኩባንያዎች ላይ በመሆኑ የሃገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ያመጣው ተፅእኖ እንደሌለ እየተናገሩ ነው።

ሰልፉን ምክንያት በማድረግም ዚምባብዌ ቀኑን ሕዝባዊ በዓል ስትል ያወጀች ሲሆን ለሰልፈኞቹም የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡም አውቶብሶች ተዘጋጅተው ነበር።

በሰልፉ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋም ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር አድርገዋል።

"ማዕቀቡ በያንዳንዱ ዚምባብዌውያን ላይ ያደረሰው ተፅእኖ የከፋ ነው፤ ማዕቀቡ ስህተት ነው የምንልበትም ምክንያት የሁሉንም ቤት ያንኳኳ በመሆኑ ነው" ማለታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ንግግራቸውን ጠቅሶ ዘግቧል።

ተቃዋሚዎች "ማዕቀቡ መነሳት አለበት" የሚል ፅሁፍ ያለባቸውን ቲሸርቶች እንዲሁም "ማዕቀቡ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው" የሚል መፈክር ይዘው ነበር።

የተለያዩ ቢዝነስ ባለቤቶችም ለቢቢሲ እንደተናገሩት ማዕቀቡ "ጠባሳን የተወ" ነው ብለውታል፤ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ባንኮች ተመጣጣኝ በሆነ ወለድ ማበደር በማቆማቸው ሥራቸውን ቀጥ እንዳደረገው ይናገራሉ።

በሰልፉ ላይ የነበሩ ተናጋሪዎችም ዚምባብዌ እያጋጠማት ያለው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥና የውሃ እጥረትም በማዕቀቡ ነው ብለዋል።

ተችዎች በበኩላቸው ሃገሪቱ የገባችበትን የኢኮኖሚ አዘቅት እንዲሁም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ያለውን ግሽበት በነዋሪው ላይ የፈጠረውን ንዴት አቅጣጫ ማስቀየሪያ ነው ይላሉ።

የቢቢሲ ዘጋቢዎች እንደታዘቡትም የተጠበቀውን ያህል ሰልፈኞች አልመጡም ብለዋል፤ ስታዲየሙ 60ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ቢኖረውም የተገኘው ከ15ሺህ እስከ 20ሺህ የሚገመት ነው ተብሏል።

የተቃዋሚ መሪ ኔልሰን ቻሚሳ በበኩላቸው ሰልፉ በሃገሪቱ ላይ የመሪዎችን ውድቀት ለመሸፈን የተደረገ ፕሮፓጋንዳ ነው ብለውታል።

በዚምባብዌ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ መሽመድመድ "ደካማ ከሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች" ጋር የተያያዘ ነው በሚል በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

አሜሪካ ከገንዘብ ዝውውርና አለም አቀፍ ጉዞዎች ጋር በተገናኘ 85 ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም 56 ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

የሃገሪቱ ፕሬዚዳንትም ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካ ማዕቀብ ዚምባብዌ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ግዥ እንዳታደርግ የሚገድብም ነው።

የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብም በዚምባብዌ የመንግሥት ኃላፊዎችን እንቅስቃሴ መገደብ፣ የገንዘብ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ዝውውርና ማገድን ያካትታል።

ማዕቀቡ የተጣለው ከሃያ አመታት በፊት ሲሆን በዚህ አመትም የአሜሪካ መንግሥት ባለፈው አመት ከነበረው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ በሞቱ ሰዎች ላይ እጃቸው አለበት ያላቸውንም ሰዎች በማዕቀብ ዝርዝሩ አካቷቸዋል።