ንሥሮችን ሲከተሉ የነበሩ አጥኚዎች የሞባይል እዳ ውስጥ ተዘፈቁ

ሚን ንሥር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአገር አገር የሚሰደዱ ንሥሮችን እየተከተሉ የሚያጠኑ ሩሲያዊያን ሳይንቲስቶች ወደ ኢራንና ፓኪስታን ተጉዘው ገንዘባቸውን ከመጨረሳቸው በተጨማሪ በሞባይል የኢንትርኔት አገልግሎት ከፍተኛ እዳ ውስጥ ገቡ።

አጥኚዎቹን ለእዳ የዳረጓቸውን ንሥሮች ከደቡባዊ ሩሲያና ከካዛኪስታን የተነሱ ናቸው ተብሏል።

በተለይ ሚን ተብሎ የሚጠራው ንሥር ከካዛኪስታን ተነስቶ ወደ ኢራን ስለሚጓዝ እሱን መከተሉ ነው ለአጥኚዎቹ እዳ መናር ምክንያት የሆነው።

አጥኚዎቹ ከሚከታተሏቸው አእዋፋት ላይ የሚሰበስቡት አጭር የጽሁፍ መልዕክት እንዳሉበት አገር የክፍያ ተመን ሁኔታ የተለያየ በመሆኑ ንሥሮቹ በሚሄዱባቸው አገራት ብዛት ክፍያው ከፍ እያለ ይሄዳል።

ሳይንቲስቶቹ የዱር እንስሳት ጥበቃን በተመለከተ ጥናት የሚያደርግ ሩሲያ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ማዕከል የበጎ ፈቃድ ተሳታፊዎች እንደሆኑም ተነግሯል።

አጥኚዎቹ የገቡበትን ችግር የተገነዘበው የሩሲያው የሞባይል ስልክ አገልግሎት አቅራቢ ሜጋፎን የተባለው ድርጅት እዳቸውን ሰርዞ ከዚህ በኋላ የሚጠቀሙትን የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት በቅናሽ እንዲከፍሉ ወስኗል።

ሳይንቲስቶቹ የገቡበትን የስልክ ዕዳ ለመክፈል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ ተከታዮቻቸው ገንዘብ እንዲለግሷቸው ጠይቀው ነበር።

አጥኚዎቹ በሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎት እዳ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ በማህበራዊ መገናኛ ብዙህን ላይ ድጋፍ ለማግኘት ባቀረቡት የድጋፍ ጥሪ መሰረት ከ1500 ዶላር በላይ ለመሰብሰብ ችለው ነበር።

ሳይንቲስቶቹ እዳ ውስጥ የከተታቸው ንሥሮቹ የት እንዳሉ በሚያመለከተው አጭር መልዕክት አማካይነት አእዋፋቱ ለደህንነታቸው አመቺ የሆነ ስፍራ መድረስ አለመድረሳቸውን በሳይንሳዊ መንገድ ለማወቅ ያስችላቸዋል።

ለየት ያለ የንሥር ዝርያ እንደ ሆኑ ከሚነገርላቸው ሚን ከተባሉት ንሥሮች መካከል አጥኚዎቹ 13ቱን በአሁኑ ጊዜ የት እንዳሉና ያሉበትን ሁኔታ እየተከታተሉ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት ከሚራቡበት የሳይቤሪያና የካዛኪስታን አካባቢዎች ወደ ደቡብ እስያ ይሄዳሉ።

የሞባይል ስልክ አገልግሎት አቅራቢው ሜጋፎን የሳይንቲስቶቹን እዳ መሰረዙ የጀመሩትን ንሥሮቹን የመከታተል ሥራ እንዲቀጥሉ ከማስቻሉ በተጨማሪ ለደህንነታቸው የሚያስፈልግ በጣም ጠቃሚ መረጃን ለመሰብሰብ ያግዛል ተብሏል።