የአይ ኤስ መሪ አቡ ባካር አል ባግዳዲ ማነው?

አል ባግዳዲ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የአስላማዊ መንግሥት ተብሎ የሚጠራው ቡድን መሪ አቡ ባካር አል ባግዳዲ በሚገኝበት አካባቢ ላይ ያካሄደውን ጥቃት ተከትሎ እራሱን ማጥፋቱን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ የአል ባግዳዲን ሞት ይፋ ከማድረጋቸው ከሰዓታት ቀደም ብለው ያለተጨማሪ ማብራሪያ በትዊተር ገጻቸው ላይ "አንድ ትልቅ ነገር ተከስቷል!" በማለት ግልጽ ያልሆነ መልዕክት አስፍረው ነበር።

ከዚያም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከቤተ መንግሥታቸው በቀጥታ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ቀርበው ይፋ እንደደረጉት የአይኤስ መሪ የሆነው አቡባካር አልባግዳዲ በአሜሪካ ልዩ ኃይል የተደረገበትን ከበባ ተከትሎ ታጥቆት የነበረውን ቦንብ እራሱ ላይ አፈንድቶ ህይወቱ ማለፉን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የአይኤስ መሪ የሆነው ባግዳዲ ስለመገደሉ በተደጋጋሚ የተሳሳቱ መረጃዎች መውጣታቸው ይታወሳል።

ኒውስዊክ የተባለው መጽሄት ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው "እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል" መረጃ በመገኘቱ የአሜሪካ የልዩ ዘመቻ ኃይሎች ጥቃት መፈጸማቸውን ዘግቧል።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሶሪያ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ተከታታይ ቡድን እንዳለው "ከእስላማዊ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች" ባሉበት የሶሪያዋ ኢድሊብ ግዛት ውስጥ ባለ አንድ መንደር አቅራቢያ በሄሊኮፕተር በተፈጸመ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል።

ከጥቂት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ሠራዊት ከሰሜናዊ ሶሪያ እንዲወጣ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከባድ ትችት ሲሰነዘርባቸው ለሰነበቱት ፕሬዝዳነት ትራምፕ የባግዳዲ ሞት ትልቅ ድል እንደሆነ እየተነገረ ነው።

አል ባግዳዲ ማነው?

አቡ ባካር አል ባግዳዲ ተብሎ የሚታወቀው ኢብራሂም አዋድ አል ባዳሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ከሚገኙ የሱኒ እስልምና ከሚከተሉ ቤተሰቦች እኤአ በ1971 ኢራቅ ውስጥ ሳማራ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ነበር የተወለደው።

ቤተሰቦቹ ከነብዩ ሙሐመድ የዘር ግንድ እንደመጡ የሚናገሩ ሲሆን እምነታቸውን አጥብቀው በመከተል የሚታወቁ ናቸው።

አል ባግዳዲ ወጣት እያለ የቁርአን ጥቅሶች በቃሉ ሸምድዶ ያለስህተት የሚደግም የነበረ ሲሆን ኃይማኖታዊ ህግጋትን አንድ በአንድ ተግባራዊ በማድረግም ይታወቃል።

ከዘመዶቹ መካከል ጥብቅ የሆኑትን ሃይማኖታዊ ህግጋትን በማያከብሩትን ላይ ባለው ጠንካራ አቋም የተነሳ ቤተሰቦቹ "አማኙ" የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውታል።

አል ባግዳዲ በሃይማኖት ላይ የነበረው ፍላጎት ወደ ከፍተኛ ተቋማት አድጎ የመጀመሪያ ዲግሪውን በእስላማዊ ጥናት ከባግዳድ ዩኒቨርስቲ ከዚያም ሁለተኛና የዶክትሬት ዲግሪውን ደግሞ በቁርአን ጥናት ከኢራቅ የሳዳም ዩኒቨርስቲ ወስዷል።

ባግዳዲ ከሁለት ሚስቶቹና ከስድስት ልጆቹ ጋር በሚኖርበት አቅራቢያ ባለ መስጊድ ውስጥ ያሉ ልጆችን ቁርአን ከማስተማሩ ባሻገር በእግር ኳስ ጨዋታ የአካባቢው ኮከብ ነበር።

ዩኒቨርስቲ ውስጥ በነበረበት ጊዜ አጎቱ የሙስሊም ወንድማማችነት ቡድን አባል አግባባውና ቡድኑን ተቀላቀለ።

ብዙም ሳይቆይ ቡድኑ ውስጥ ከሚታወቁት ጥቂት ወግ አጥባቂ አክራሪ አባላት መካከል አንዱ ሆኖ ታወቀ። ከዚያም የሳላፊስት ጂሃዳዊ እንቅስቃሴን ተቀብሎ መንቀሳቀስ ጀመረ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

አቡ በከር አልባግዳዲ በቅርቡ ለደጋፊዎቹ በኦን ላየን በተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ታይቶ ነበር

ከእስር ወደ አማጺነት

ከ15 ዓመት በፊት በአሜሪካ የተመራው የኢራቅ ወረራ በተጀመረ በጥቂት ወራት ውስጥ ጃይሽ አህል አል ሱናህ የተባለ የደፈጣ ተዋጊዎች ቡድን በመመስረት ተሳታፊ ነበር።

እኤአ የካቲት ወር 2004 ላይ የአሜሪካ ኃይሎች አል ባግዳዲን ፋሉጃ ውስጥ በቁጥጥር ስር አውለው ባቆዩበት ጊዜ ውስጥ ትኩረቱን በሃይማኖታዊ ተግባራት ላይ በማድረግ፣ የአርብ ጸሎትን በመምራትና አብረውት ላሉት ታሳሪዎች ሃይማኖታዊ ትምህርት በመስጠት ጊዜውን ያሳልፍ ነበር።

አብረውት ታስረው የነበሩ ሰዎች እንደሚሉት ባግዳዲ እስር ቤት ውስጥ በነበረው እንቅስቃሴ ቁጥብ የነበረና በእስር ላይ ከነበሩት የሳዳም ታማኞችና የጂሃድ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች መካከል በመሆን ተሰሚነትን ለማግኘት ችሎ ነበር።

ባግዳዲ በእስር ቤት ቆይታ ከአብዛኞቹ ታሳሪዎች ጋር ትብብርን ለመፍጠር ከመቻሉ በተጨማሪ ከእስር ከተለቀቀም በኋላ ግንኙነቱ ሳይቋረጥ ቀጥሏል።

ባግዳዲ ከእስር ከተፈታ በኋላ በኢራቅ ውስጥ ያለውን የአልቃኢዳ አንድ ክንፍን የሚመራው ዮርዳኖሳዊው የአቡ ሙሳብ አል ዛርቃዊ ቃል አቀባይን መገናኘቱ ይነገራል።

በ2006 ላይ ዛርቃዊ በአሜሪካ በተፈጸመበት የአየር ጥቃት ሲገደል ግብጻዊው አቡ አዩብ አል ማስሪ የመሪነቱን ቦታ ተረከበ።

ወዲያውኑም ግብጻዊው በኢራቅ ያለውን የአልቃኢዳ ክንፍ አፍርሶ የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት (አይኤስአይ) የተባለውን ቡድን መሰረተ። ነገር ግን ቡድኑ ለአልቃኢዳ ያለውን ታማኝነት እንደማያቋርጥ አሳወቀ።

ወደ አመራር ማደግ

ባግዳዲ በነበረው ሃይማኖታዊ ዕውቀትና አዲስ በተመሰረተው ቡድን የሌላ ሃገር ዜግነት ባላቸውና በኢራቃዊያን አባላቱ መካከል ያለውን ክፍፍል ለማጥበብ በነበረው ብቃት ምክንያት በፍጥነት ወደ አመራር ስፍራ ለማደግ ቻለ።

በ2010 ላይ የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት (አይኤስአይ) መሪ በሞት ሲለይ የቡድኑ ከፍተኛ ምክር ቤት አቡ ባከር አል ባግዳዲን በመሪነት ቦታው ላይ እንዲቀመጥ አደረገ።

ባግዳዲ መሪነቱን እንደያዘ በአሜሪካ ልዩ የዘመቻ ኃይል በተፈጸመበት ጥቃት ተዳክሞ የነበረውን የቡድኑን እንቅስቃሴ መልሶ የማጠናከር ሥራን ጀመረ።

በሶሪያ ውስጥ የተቀሰቀሰውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎም ለቡድኑ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በእርሱ ዕዝ የነበረ የሶሪያ ዜጋ የአል ኑስራ ግንባር የተባለ ምስጢራዊ ቅርንጫፍ ሶሪያ ውስጥ እንዲያቋቁም አደረገ።

የአይሲስ መፈጠር

ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ከአል ኑስራ ግንባር መሪ ጋር አብረው ለመስራት ስላልተግባቡ ተለያዩ። ባግዳዲም የተጽእኖ ክልሉን ሶሪያ ውስጥ ለማስፋት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ።

በ2013 ላይ አል ኑስራ የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት (አይኤስአይ) አንድ አካል እንደነበረና ቡድኑን በማጠቃለል "በኢራቅና አል ሻም/ሌቫንት እስላማዊ መንግሥት" (አይኤስአይኤስ/አይኤስአይኤል) በሚል ስያሜ ቡድኑን እንደገና አዋቀረው።

ነገር ግን አልቃኢዳ በዚህ እርምጃ ባለመደሰቱ የቡድኑ መሪ አይማን አል ዛዋሂሪ አል ባግዳዲ የአል ኑስራን ነጻነት እንዲያከብር ቢጠይቀውም ሳይቀበለው ቀረ። ይህንንም ተከትሎ ዛዋሂሪ አይኤስአይኤስን ከአል ቃኢዳ እንዲባረር አደረገ።

ባግዳዲም ለዚህ ውሳኔ ምላሽ ያደረገው አል ኑስራን በመዋጋት ቡድኑ በምሥራቃዊ ሶሪያ ጥብቅ ሃይማኖታዊ ህጎችን ተግባራዊ በማድረግ ያለውን ይዞታውን ማጠናከር ቀጠለ።

እስላማዊ መንግሥት

ከአምስት ዓመት በፊት ሰኔ ወር ላይ አይሲስ የኢራቋን ሁለተኛ ትልቅ ከተማን ሞሱልን መቆጣጠሩን ተከትሎ ቡድኑ ስሙን "እስላማዊ መንግሥት" በሚል አሳጥሮ በቃል አቀባዩ በኩል ጥንታዊው እስላማዊ መንግሥት መመስረቱን አሳወቀ።

ከቀናት በኋላም ባግዳዲ ሞሱል ውስጥ በሚገኝ መስጊድ ውስጥ አርብ ዕለት በነበረ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቶ ባደረገው ንግግር የእስላማዊው መንግሥት መሪ (ከሊፋ) መሆኑን ተናገረ።

ከዚህ በኋላም የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን አል ባግዳዲ እንደተገደለ የሚያመለክቱ በርካታ የተሳሳቱ ዘገባዎችን ሲያርቡ ቆይተዋል።

ባግዳዲ ባለው ለየት ያለ እውቀትና የአመራር ብቃት ቡድኑን ሲመራ ቆይቷል። ቡድኑ እርሱን ካጣ ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ይታመናል።