በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋና በሐረር ባለፈው ሳምንት ስላጋጠሙ ግጭቶችና ጥቃቶች አስካሁን የምናውቃቸው ነገሮች

የአዳማ ከተማ ከፊል ገጽታ

የፎቶው ባለመብት, Adama City BDK

ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ እኩለ ሌሊት ላይ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር ጃዋር መሀመድ በመንግሥት ተመድበውለት የነበሩት የደህንነት ጥበቃ አባላት 'በዚህ ለሊት እንዲነሱብኝ ታዘዋል' በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕከት አሰፈረ።

ጃዋር እንደሚለው ማክሰኞ ዕኩለ ሌሊት አቅራቢያ ሁለት መኪኖች ወደሚኖርበት ቤት አካባቢ በመምጣት ጥበቃዎቹን እርሱ ሳያውቅ "እቃቸውን ይዘው ቤቱን ለቀው እንዲወጡ" እንደተነገራቸው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።

አክሎም ጥበቃዎቹ ለምን እንዲወጡ እንደጠየቁና ለስልጠና እንደሆነ እንደተነገራቸው እነሱም እንዳልተቀበሉ፣ ከዚያም ስልክ ተደውሎላቸው በአስቸኳይ ቤቱን ለቀው ካልወጡ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ጠቅሷል።

ይህንንም ተከትሎ ደጋፊዎቹና የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ጃዋር ያሰፍራቸው የነበሩ አጫጭር መልዕክቶችን በመከታተል፣ ምን ሊከሰት እንደሚችል ግምታቸውንና በጉዳዩ ላይ አስተያየት በመስጠት መልዕክት ሲለዋወጡ እስከ ንጋት ቆዩ።

ሌሎች የጃዋር አድናቂዎችና ተከታዮች ደግሞ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል በሚል ስጋት ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ቦሌ አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በማቅናት መሰባሰብ ጀመሩ።

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ደግሞ ጃዋር ገጠመው የተባለውን ነገር በመቃወም ሰልፎች ሲካሄዱ በአንዳንድ ቦታዎችም መንገዶች ተዘጉ፤ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተገታ።

ረቡዕ

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽር እንደሻው ጣሰው በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ላይ ቀርበው ጃዋር መሀመድ ለተከታዮቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ጥቃት ሊደርስብኝ ነበር በማለት ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት መሆኑን ገለጹ።

አክለውም "በመንግሥትም በፖሊስም በኩል ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደም" በማለት ፖሊስ እንደወትሮው የየዕለት ተግባሩን እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ኮሚሽነሩ የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱና መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲቀጥሉ ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን ፖሊስ የሕግ ማስከበር ሥራውን እንደሚቀጥል አመለከቱ።

ጃዋር ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገረው "በውድቅት ለሊት በጣም አጠራጣሪ በሆነ መልኩ የተሞከረው ምን እንደሆነ አልገባኝም። የእስርም አይመስለኝም። በዱርዬዎች ቤቴ ላይ ጥቃት በማድረስ ለማሳበብ እንደታሰበ ነው ያሉኝ መረጃዎች የሚያሰዩት" በማለት በመኖሪያ ቤቱ የተፈጸመው ክስተት በእርሱ ላይ የተደረገ 'የግድያ ሙከራ' እንደሆነ መደምደሚያ ላይ መድረሱን ተናግሯል።

ከሰዓት በኋላ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተቀሰቀሱት ሰልፎች ግጭትና ጥቃቶችን በማስከተል በሰዎች ህይወትና አካል እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣት ጀመሩ።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው በሰጡት መግለጫ ክስተቱ "መሆን ያልነበረበት ትልቅ ስህተት ነው" በማለት የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌደራል መንግሥት የጃዋርን ደህንነት እንደሚያስጠብቁ ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስህተት ሲሉ የገለጹት ክስተት በማን እንደተፈጸመና፣ ለምን እኩለ ለሊት ላይ ማድረግ እንደታሰበ እንደሚጣራ አመለከቱ።

የፎቶው ባለመብት, Ashabbiir

ሐሙስ

ሐሙስ ዕለት ግጭትና ጥቃቱ በተለያዩ አካባቢዎች ቀጥሎ፣ ከእነዚህ ቦታዎች የሚወጡ መረጃዎች ዳግሞ ክስተቶቹ የብሔርና የሃይማኖት ገጽታን መያዛቸውና ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥርም ከአስር በላይ መሆኑን ቢቢሲ ያረጋገጠ ሲሆን ቁጥሩም ከፍ እያለ መጥቶ ከ20 በላይ ሆነ።

በሚፈጸሙ ጥቃቶች ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የአካል ጉዳትና ከፍ ያለ የንብረት ውድመትም አጋጥሟል። በዚህም በእሳት ከተቃጠሉ ተሽከርካሪዎች፣ የንግድ ተቋማትና መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ የእምነት ተቋማትም ላይ ጉዳት ደርሷል።

ሐሙስ ከሰዓት በኋላ የኦሮሞ የአገር ሽማግሌዎችና ፖለቲከኞች በአክቲቪስት ጃዋር መኖሪያ ቤት ተገኝተው በሰጡት የጋራ መግለጫ ወጣቶች ከሰሞኑ ከተከሰተው ግጭት ራሳቸውን እዲቆጥቡ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በዚህ ወቅት ጃዋር "ጉልበተኞች በጉልበታቸው ከቀጠሉ ግን ልክ እንደ ትላንቱ መፍትሄ ፈልግ እንልሃለን። .... አሁን ወደ ማረጋጋት ተመለሱ። ግን ሁል ጊዜም እንደምላችሁ ንቁ ሁኑ። አንድ ዓይናችሁን ብቻ ዘግታችሁ ተኙ" ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

ሐሙስ ዕለት ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ለማካሄድ ተሰብስቦ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ግጭትና ጥቃትን መሰረት አድርጎ ባወጣው የሰላም ጥሪ "አገሪቷ እንኳንስ ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጎሳንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋታቸው እንዳሳሰበው" ገልጾ ለሦስት ቀናት የጸሎትና ምሕላ አውጇል።

አርብ

ግጭቱና ጥቃቱ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኙትን ቢሾፍቱ፣ አዳማና አምቦ ውስጥ ለሁለት ቀናት ቆይቶ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

ከእነዚህ አካባቢዎች በተጨማሪ ኮፈሌ፣ ዶዶላ፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋና ባሌ ሮቤ ውስጥ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አንዳንድ ቦታዎች ግጭትና ጥቃቶች መፈጸማቸው የተሰማ ሲሆን የሞቱና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍ እንዲል አድርጓል።

ቢቢሲ ከሆስፒታል ምንጮች፣ ከመንግሥት አካላትና ከሟች ቤተሰቦች ባሰባሰበው መረጃ መሰረት በሁለቱ ቀናት ግጭት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 44 መድረሱን ያረጋገጠ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህ የላቀ እንደሚሆን ስጋት እንዳለ አመልክቶ ነበር።

አርብ ረፋድ ላይ፣ ረቡዕና ሐሙስ ዕለት የተቃውሞ ሠልፍ በተካሄደባቸው የኦሮሚያ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ከተሞች በክልሎችና በአስተዳደሩ ጥያቄ መሰረት የመከላከያ ሠራዊት መሰማራቱን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ተናገሩ።

የመከላከያ ሠራዊት በፍጥነት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ጉዳት ማጋጠሙን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ በወቅቱ ጠቁመዋል።

በዚሁ ቀን 10፡00 ሰዓት ገደማ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ፣ ከሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እና ከፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሸነር ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የቤተክርስቲያኗ ተወካዮች በቤተክርስቲያን ላይ የሚቃጣው ጥቃት እንዲቆም እና መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን እንዲያከናውን ጠይቀዋል።

አርብ ምሽት ሮይተርስ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን ጠቅሶ እንደዘገበው በግጭቱና በጥቃቶቹ ህይወታቸውን ያጡት ሰዎች 67 መድረሱን አመልክቶ፤ ከሟቾቹ አስራ ሦስቱ በጥይት ቀሪዎቹ 54ቱ ደግሞ በድንጋይና በዱላ ተደብድበው እንደሞቱ ገልጿል። የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥርም ከሁለት መቶ በላይ መሆኑም ተነግሯል።

ቅዳሜ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ራይነር በአገሪቱ የተከሰተው ግጭትን በተመለከተ በኤምባሲው የፌስቡክ ገጽ ላይ በስማቸው በወጣ መልዕክት ላይ "ሰሞኑን በታዩት የጥላቻና ጠብ አጫሪ ንግግሮችና ጥቃቶች" በእጅጉ መረበሻቸውን አመልክተው፤ "የጥቃቶቹ ተሳታፊዎችንና ጥቃቶቹን የሚያነሳሱትን አጥብቀን እናወግዛለን። እንዲህ አይነቱ ድርጊትም ምንም አይነት ማሳመኛ ሊቀርብለት አይችልም" ብለዋል።

አገራቸው በኢትዮጵያን ሰላም፣ ብልጽግናና አካታች የሆነ የፖለቲካ ሁኔታ እንዲፈጠር እንደምትሰራና ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደምትሰጥ አመልክተው፤ ለዚህም አላማ ከሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል።

አምባሳደሩ ሲያጠቃልሉ "ሁሉም ለሚፈጽመው ድርጊትና ውሳኔ ኃላፊነት አለበት። ስለዚህም ጥቃቶችን ማነሳሳትም ሆነ ድርጊቱን አለማውገዝ ተቀባይነት የለውም። ሁላችንም ሰላምን፣ አንድነትንና መቻቻልን የመምረጥ ነጻነት እንዲሁም ኃላፊነት አለብን" ብለዋል አምባሳደር ራይነር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ

ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ በሩሲያና በአፍሪካ መሪዎች መካከል ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ በነበረበት ወቅት የተከሰተውን ይህን ግጭት በተመለከተ ከጉባኤው እንደተመለሱ ስለጉዳዩ አንዳች ነገር ይላሉ ተብለው የተጠበቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ቅዳሜ ምሽት ነበር መግለጫ የሰጡት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ተብሎ ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው የጽሁፍ መግለጫ በተከሠተው እጅግ አሳዛኝ ግጭት፣ በዜጎችና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት፣ ማዘናቸውን ገልጸው "የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎች በሕግ ፊት ቀርበው ተገቢው ሁሉ እንዲያገኙ ያለማወላወል እንሠራለን" ማለታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ አክሎም "ይህ ሁሉ ለምን እንደመጣብን እናውቃለን። ከዚህ የበለጠ ፈተና ቢያጋጥመንም እንኳን የጀመርነውን ጉዞ አናቋርጥም። አረሙን እየነቀልን፤ ስንዴውን እየተከባከብን እንሄዳለን እንጂ ለአረሙ ስንል ስንዴውን አንተወውም" ብለዋል።

ረቡዕና ሐሙስ በነበረው ግጭት ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በድሬዳዋ 110፣ በአዳማ ደግሞ ከ60 ሰዎች በላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።