ኢራን በስርቆት ወንጀል ተይዞ የተፈረደበትን ግለሰብ ጣቶች ቆረጠች

ከተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የተወሰደ-የኢራን ማረሚያ ቤት የጥበቃ አባል ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አምንስቲ ኢንተርናሽናል የኢራን ባለስልጣናት በስርቆት ወንጀል ተይዞ የተፈረደበትን ግለሰብ ጣቶች በመቁረጣቸው አወገዘ።

ይህ የመብት ተሟጋች ድርጅቱ እንዳለው ከሆነ የግለሰቡ ጣቶች የተቆረጡት በአገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት ማዛንዳራን ሲሆን "አስነዋሪ የማሰቃያ መንገድ" ሲል ገልጾታል።

የኢራን ባለስልጣናት ግለሰቡ በ28 የስርቆት ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።

የኢራን እስላማዊ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስርቆትን በተመለከተ "በመጀመሪያው ድርጊት" የቀኝ እጅ አራት ጣቶች እንዲቆረጡ ያዛል።

ምንም እንኳ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጊቱን በአንድ ድምጽ ቢያወግዙትም የኢራን ባለሰልጣናት ግን 'ሌብነትን ለመከላከል ፍቱን መድኃኒት ነው' ሲሉ ድርጊታቸው ትክክል መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲህ አይነት ቅጣት በኢራን ውስጥ ብዙ ጊዜ አይፈፀምም።

በአምንስቲ ኢንተርናሽናል ውስጥ የመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆነው ሳላህ ሂጋዝ "ሰውን መጉዳትና አካል ማጉደል ፍትህ አይደለም።"

"የሰው ልጅን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው። የኢራን ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ የሚወሰደው ማሻሻያ በመዘግየቱ እንዲህ አይነቱን ሰቅጣጭ ድርጊት ማስቆም አልተቻለም" ብሏል።

'ሚዛን' የተባለው የኢራን ፍትህ ዜና ኤጀንሲ እንዳለው ባለፈው ረቡዕ በማዛንዳራን ዋና ከተማ ሳሪ ውስጥ እርምጃው መወሰዱን ገልጿል።

እርምጃው የተወሰደበት ግለሰብ በስም አልተጠቀሰም።

ኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ስትሆን የሕግ ሥርዓቷ ከሸሪዓ ሕግ የተቀዳ ነው።

በ2018 ታህሳስ ወር በግ ሰርቋል የተባለ የ34 ዓመት ወጣት እጁ እንዲቆረጥ ተደርጓል።

ተመሳሳይ ቅጣት በሳዑዲ አረቢያ፣ ናይጄሪያና ሶማሊያ ይፈፀማል።