የሳውዝዌስት አብራሪዎች በአውሮፕላን መጸዳጃ ክፍል ውስጥ ድበቅ ካሜራ ገጥመዋል የሚል ክስ ተመሰረተባቸው

የሳውዝዌስት አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሳውዝዌስት አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ በአውሮፕላን መጸዳጃ ክፍል ውስጥ ድብቅ ካሜራዎችን ገጥመዋል ያለቻቸው ሁለት የአየር መንገዱ አብራሪዎች ላይ ክስ መሰረተች።

ሪኒ ስቲንከር የተባለችው የበረራ አስተናጋጅ ሁለቱ አብራሪዎች በመጸዳጃ ክፍል ውስጥ ካሜራ መግጠማቸውን አይቻለሁ ያለችው ከሁለት ዓመት በፊት ከሩሲያ ፒተርስበርግ ወደ ፊኒክስ በነበራት በረራ ነው።

ዋና አብራሪ ቴሪ ግርሃም ወደ መጸዳጃ ክፍል ለመሄድ በማሰብ ከረዳት አብራሪው ራየን ራስል ጋር በመሆነ የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ አብራ እንድትቆየ ከጠየቃት በኋላ መጸዳጃ ክፍል ውስጥ እየሆነ ያለውን በቀጥታ የሚያስመለከት አይፓድ መመልከቷን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ጉግል የሰዎችን ፊት መለየት የሚችል ካሜራ ይፋ አድርጓል።

በአየር መንገዱ መመሪያ መሰረት በማንኛው ሰዓት ቢያንስ ሁለት የአየር መንገዱ ባልደረቦች የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ እንዲሆኑ ያዛል።

አብራሪዎቹ እና ሳውዝዌስት አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጆችን እና መንገደኞችን መጸዳጃ ቤት ውስጥ በድብቅ የሚቀርጽ ካሜራ አለመተከሉን ይናገራሉ።

የበረራ አስተናጋጇ ሪኒ ስቲንከር ስለ ካሜራው ዋና አብራሪው ለማንም ሰው እንዳትናገር እንዳስጠነቀቃት ተናግራለች።

ሪኒ ስቲንከር ስለ ጉዳዩ ለአየር መንገዱ ሪፖርት ብታደርግም የአየር መንገዱ አስተባባሪ ስለጉዳዩ ከማንም ጋር መነጋገር እንደማትችል እንደገለጸላት በክስ መዝገቡ ላይ ሰፍሯል።

ክስ የተመሰረተባቸው ሁለቱ አብራሪዎች ምንም አይነት እርምጃ ሳይወሰድባቸው በሥራቸው እንደቀጠሉበት ተነግሯል።

አየር መንገዱ በአውሮፕላን መጸዳጃ ክፍል ውስጥ ድብቅ ካሜራ ተገጥሟል መባሉን ተከትሎ ባደረኩት ፍተሻ ተገጥሞ የተገኘ ድበቅ ካሜራ የለም ብሏል።

"ካደረግነው ምረመራ ማረጋገጥ የቻልነው በመጸዳጃ ክፍሎች ውስጥ የተገጠመ ካሜራ አለመኖሩን ነው" ይላል የአየር መንገዱ ምላሽ።

በክሱ ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያስተላልፍበት ጊዜ እስካሁን አልተቆረጠም።