የአንበጣ መንጋው እስካሁን በሰብል ላይ ጉዳት አላደረሰም

የአማራ ክልል የግብረና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አሰፋ (ዶ/ር)
የምስሉ መግለጫ,

የአማራ ክልል የግብረና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አሰፋ (ዶ/ር)

ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተወሰኑ ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አላደረሰም ሲል የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል የግብረና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አሰፋ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንዳስታወቁት መንጋው የተከሰተው ክልሉን ከአፋር ጋር በሚያዋስኑ ወረዳዎች ነው።

"በሰሜን ወሎ፤ በራያ ቆቦ እና ሃብሩ ወረዳዎች፤ በደቡብ ወሎ ደግሞ ወረባቦና አርጎባ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ደዌ ሃረዋ፣ ባቲ እና አርጡማ ፉርሲ" የአምበጣ መንጋው መከሰቱን አስረድተዋል።

የአንበጣ መንጋው ወደ አማራ ክልል ከመዛመቱ በፊት በአፋር እና ሶማሌ ክልል የመከላከል ሥራዎች ቢሠሩም ከጥቅምት ወር ጀምሮ ወደ አማራ ክልል ገብቷል።

አንበጣው ጉዳት እንዳያደርስ የተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎች ተግባራዊ መደረጉን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አስታውቀዋል።

"ያደገው አንበጣ ሰብል የማይበላ ቢሆንም ለእርባታ ምቹ ሁኔታን ካገኘ እንቁላሉ ሙሉ የዕድገት ሂደቱን እስኪያጠናቅቅ አውዳሚ ስለሆነ ለበልግና መስኖ ስራ አስቸጋሪ ይፈጥራል ስለዚህም የመከላከል ስራ እየተሠራ ነው" ይላሉ አቶ ሰለሞን። "በመኪና፣ በሰው በአውሮፕላንን እንዲሁም በባህላዊ መንገድ እየተከላከልን ነው።"

በአውሮፕላን የታገዘው የመድኃኒት ርጭት በትላንትናው ዕለት ደዌ ሃረዋ አካባቢ ሲሰራ ቆይቷል።

እስካሁን የአንበጣ መንጋው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አላደረሰም ያሉት ኃላፊው ክልሎች እና ግብርና ሚኒስቴርን በማቀናጀት የህይወት ሂደቱን ካለቋረጥን በበልግ እና በመስኖ ሥራችን ላይ ችግር ስለሚፈጥር መረባረብ አለብን ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ ክልል በትግራይ ደቡባዊ እና ምዕራባዊ ዞኖች ተመሳሳይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል።

የአከባቢው ነዋሪዎች በባህላዊ መንገድ የአምበጣ መንጋውን ለማበረር ቢጥረም እየተደረገ ያለው ጥረት ግን እጅግ አድካሚ እና የተፈለገውን አይነት ውጤት እያስገኘ አለመሆኑ ተነግሯል።

የአንበጣ መንጋው ባለፈው ዓመት ሰኔ መጀመሪያ ላይ ነበር ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የገባው።