በግጭት ውስጥ የሰነበቱት ከተሞች የዛሬ ውሎ

አዳማ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Merga Angasu

የምስሉ መግለጫ,

አዳማ

ባለፈው ረቡዕ በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ የተቀሰቀሱ ግጭቶች የብሔርና የሃይማኖት መልክ ይዘው ለቀናት ከቀጠሉ በኋላ ከ67 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፉ በኋላ በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጠሪዎች እየተያዙ መሆናቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ትናንት በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ሰልፎች እንደሚካሄዱ የሚገልጹ መልዕክቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ዛሬ ሰኞ ግጭቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተሰግቶ ነበር። ቢቢሲ እስካሁን ያለውን ሁኔታ ለማወቅ ከሰሞኑ ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎችን አናግሯል።

ሐረር

በሐረር ከተማ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ዛሬም በከተማዋ የነበረው እንቅስቃሴ መቀዝቀዙን ቢቢሲ ያናገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በዛሬው ዕለት ትምህርት ቤቶች ዝግ ሲሆኑ ወደ መንግሥት መስሪያ ቤቶች ተገልጋዮች ስለማይታዩ ጭር እንዳሉና አንዳንድ ሱቆችም ዝግ ናቸው።

በከተማዋ ያሉ መንገዶች እምብዛም ተሽከርካሪዎች ስለማይታዩባቸው ጭር ማለታቸውን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ የጸጥታ አካላትም በከተማዋ እየተዘዋወሩ ጥበቃ እያደረጉ እንደሆነም ተገልጿል።

በተጨማሪም ቀደም ካሉት ቀናት በተለየ የጸጥታ አካላት ስለትም ሆነ ዱላ ይዞ መንቀሳቀስን ከልክለዋል። እነዚህን ቁሶች ይዘው ከሚገኙ ሰዎች ላይ እንደሚቀሙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ሰልፍም ሆነ ግጭት ይህንን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ድረስ አለመከሰቱን ለማወቅ ችለናል።

ሞጆ

ዛሬ ጠዋት በሞጆ ከተማ በተከሰተ ሁከት ሁለት ሰዎች በጥይት ተመተዋል።

በከተማዋ ዛሬ ጠዋት 'የታሰሩ ሰዎች ከእስር ይለቀቁ' በማለት ሰልፍ የወጡ ሰዎች ከመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ተጋጭተው በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማው ከንቲባ ወ/ሮ መሰረት አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቅዳሜ ሌሊት ላይም በከተማዋ በምሽት ሰልፍ ተካሂዶ እንደነበር ከንቲባዋ ተናግረዋል።

"ቅዳሜ ሌሊት 'ቤተክርስቲያን ተቃጥለ' የሚል ወሬ ተናፍሶ ሌሊቱን ሁከት ተፈጥሮ ነበር። በንብረት ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር" ብለዋል።

ከንቲባዋ ጨምረው እንደተናገሩት ቅዳሜ ሌሊት ቤተ-ክርስቲያን ተቃጥሏል እየተባለ የተናፈሰው ወሬ ሃሰት መሆኑን እና ይህ የተደረገው "በከተማው ሆን ተብሎ ረብሻ ለመፍጠር" ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ዛሬም 'የታሰሩ ሰዎች ከእስር ይለቀቁ' በማለት አደባባይ እንደወጡ እና ከጸጥታ አካላት ጋር እንደተጋጩ እንዲሁም በተከፈተው ተኩስ ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውን አስረድተዋል።እስካሁን የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ የሞከሩ 9 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ፤ ዛሬ ተከስቶ የነበረው ሁከት በቁጥጥር ሥር ውሎ በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ጨምረው ተናግረዋል።አዳማ

አዳማ ከሰሞኑ ሁኔታ በተሻለ መልኩ አንጻራዊ ሰላም እንደሚታይባት በስፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን ዘግቧል።

የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ራውዳ ሁሴን በከተማዋ ዛሬ ጠዋት የታውሞ ሰልፍ ለማካሄድ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ ጥሪዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ይህን ለማስቆም ጥረት ማድረጋቸውን ተገልጸዋል።

በነዋሪዎች ዘንድ ከሚስተዋለው የደህንነት ስጋት ውጪ ከተማዋ ከሞላ ጎደል ወደ ቀድሞ የንግድ እንቅስቃሴ እየተመለሰች መሆኑን ሪፖርተራችን ዘግቧል።

ሰበታ

ሰበታ ከተማ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኑን የከተማው ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ታዬ ዋቅኬኔ ተናግረዋል።

የንግድ ተቋሞቻቸውን ዘግተው ከነበሩት እና ከአጠቃላይ ነዋሪው ጋር ውይይት ማድረጉ እንደቀጠለ ተናግረው፤ መልካም የሚባል ለውጦች እየተመለከቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ባሌ እና ጎባ ከተሞች

በማሕበራዊ ሚዲያዎች ዛሬ ጠዋት በባሌ ዞን በሚገኙ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ሲጠሩ ነበር። ይሁን እንጂ በከተሞቹ ዛሬ ምንም አይነት የተቃውሞ ሰልፎች አለመካሄዳቸውን ከነዋሪዎች ሰምተናል።

በተመሳሳይ መልኩ በነዋሪዎች ዘንድ ካለው የደህንነት ስጋት ውጪ በከተሞቹ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።