የአይኤሱ መሪ አቡ ባክር አልባግዳዲ እንዴት ተገደለ?

አልባግዳዲ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአይኤስ መሪ የነበረው አቡባካር አልባግዳዲ በአሜሪካ ልዩ ኃይል የተደረገበትን ከበባ ተከትሎ ታጥቆት የነበረውን ቦንብ እራሱ ላይ አፈንድቶ ህይወቱን ማጥፋቱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታውቀዋል።

ለመሆኑ አልባድጋዲ ያለበት እንዴት ታወቀ?

ማረጋገጫ ያላቀረቡ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት የአልባግዳዲ መደበቂያ የሆነው ግቢ የሚገኘው ሶሪያ ውስጥ ከቱርክ ደቡባዊ ድንበር በ 5 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በኢድሊብ ግዛት በምትገኝ ባሪሻ በምትባል መንደር ነው።

የቤቱ መገኛ የታወቀው ባለፉት ጥቂት ወራት መረጃ አቀባዮች በሰጧቸው ተከታታይ መረጃዎች እንደሆነ ዘግበዋል።

ኒውስዊክ የተባለው መጽሄት አንድ የአሜሪካ ሃላፊን ጠቅሶ እንደዘገበው ከአልባግዳዲ ሚስቶች መካከል አንዷ እና የቤት ሰራተኛ ባለፈው ክረምት በቁጥጥር ስር ውለው ነበር። ዋሸንግተን ፖስት ደግሞ ከአይኤስ የተባረረና ለኩርዶች ቁልፍ የመረጃ ሰው የነበረ አንድ ግለሰብ መረጃውን እንደሰጠ ዘግቧል።

ከአሜሪካ ጋር ወዳጅነት ያለው በኩርዶች የሚመራው የሶሪያ ሞክራቲክ ሃይሎች አዛዥ ማዝሎም አብዲ ደግሞ ለብዙ ወራት መረጃውን ሲያሰባስቡ እንደነበረና ''በዚህ ታላቅ ተልእኮ'' ለተሳተፉ በሙሉ በትዊተር ምስጋና ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ኢድሊብ የአይኤስ ተቀናቃኝ የሆኑ አክራሪዎች የሚቆጣጠሩት አካባቢ እነደመሆኑ አልባግዳዲ እዛ ቦታ ላይ መደበቁ ብዙዎችን ያስገረመ ሲሆን ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የአይኤስ ወታደሮች በቦታው ይንቀሳቀሳሉ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በአልባግዳዲ ላይ ለሚፈጸመው ጥቃት ይሁንታቸውን ከሰጡ በኋላ በዋይት ሃውስ ከሚገኙ ሃላፊዎቻቸው ጋር 'ሲቹዌሽን ሩም' በሚባለው መሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተዋል።

አልባግዳዲ እንዴትስ ተገደለ?

ቱርክ፣ ኢራቅ፣ የኩርድ ሃይሎችና የኢድሊብን የአየር ክልል የምትቆጣጠረው ሩሲያን ጨምሮ በአካባቢው የሚኙ በርካታ የአሜሪካ ወዳጆች ስለጉዳዩ ቀድመው እንዲያውቁ ተደርጎ ነበር።

ምንም እንኳን ጥቃቱን የፈጸመው የትኛው ወታደራዊ ቡድን እንደሆነ ግልጽ ባይደረግም አንዳንድ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መረጃ 'ዴልታ ፎርስ' የተባለው የልዩ ሃይሎች ቡድን እንደሆነ ገልጸዋል ተብሏል። 'ዴልታ ፎርስ' ከዚህ በፊትም በእንደዚህ አይነት ተልዕኮዎች ላይ የሚሳተፍ ሲሆን ብዙ ልምድ ያለው ነው ተብሏል።

ለ100 ያልበለጡ ወታደሮችም በተልዕኮው ሳይሳተፉ እንደልቀሩም ተገልጿል።

በርካታ የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን ስምንት ሄሊኮፍተሮች ወታደሮችን ወደቦታው ለመውሰድ ግልጋሎት ሰጥተዋል። ከኢራቅ ተነስተው በቦታው እስኪደርሱም 1 ሰአት ከ 10 ደቂቃ ፈጅቶባቸው ነበር ተብሏል።

ወታደሮቹ ልክ በቦታው ሲደርሱ የአልባግዳዲ ወታደሮች ናቸው የተባሉ አካባቢውን በጥይት እሩምታ ያናወጡት ሲሆን የአሜሪካ ወታደሮችም አጸፋውን መልሰዋል። በባሪሻ መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ግለሰብ እንደገለጸው ሄሊኮፕተሮቹ በአካባቢው በነበሩ ሁለት ቤቶች ላይ ሚሳኤል ተኩሰው ከጥቅም ውጪ አድርገዋቸዋል።

ወታደሮቹ ወደ ምድር ከወረዱ በኋላም አልባግዳዲ እጁን እንዲሰጥ ትእዛዝ አስተላልፈውለት ነበር። ነገር ግን ሁለት ሰዎችና 11 ህጻናት ብቻ ነበሩ ከቤቱ የወጡት። አልባግዳዲ ውስጥ ሆኖ ቀድሞ በተቆፈረ ዋሻ በኩል ለማምለጥ ሞክሯል።

በመቀጠልም ወታደሮቹ ምናልባት ቀድመው የተጠመዱ ቦምቦች ካሉ በማለት ጉድጓዶቹንና ዋሻዎቹን በቦምብ አፈንድተዋቸዋል። ከወታደሮቹ በመሸሽ ላይ የነበረው አልባግዳዲ ሰውነቱ ላይ አስሮት የነበረው ቦምብ በማፈንዳት ከራሱ በተጨማሪ ይዟቸው የነበሩ ሶስት ህጻናትን አጥፍቷል።

ወታደሮቹ ባደረጉት አሰሳ ተጨማሪ ከአስር በላይ ህጻናትን ከቦታው ያስወጡ ሲሆን ትራምፕ ደግሞ ህጻናቱ በአካባቢው ወደ ሚንከባከቧቸው ሰዎች ተወስደዋል ብለዋል።

ጥቃቱ ከተሰነዘረበት አካባቢ የሚወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት ህንጻዎች ፈራርሰዋል፣ የተቃጠሉ መኪናዎች በየቦታው ይታያሉ በተጨማሪም የጥይት ቀዳዳዎች በግድግዳዎች ላይ በብዛት ይታያሉ።

ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች

የአልባግዳዲ ሚስቶች ናቸው የተባሉ ሁለት ሴቶች በቦታው ተገድለዋል። ሰውነታቸው ላይ ተቀጣጣይ ፈንጂ አስረው ሊሆን ይችላል ተብሎ ስለተገመተና ለማምከን መሞከር አደጋ ሊኖረው ይችላል በመባሉ ወታደሮቹ ሬሳቸውን ትተውት ሄደዋል።

ዋይት ሀውስ እንዳስታወቀው አምስት የአይኤስ ተዋጊዎች በግቢው ውስጥ የተገደሉ ሲሆን በርከት ያሉ ሌሎችም ከግቢው ውጪ ተገድለዋል።

ሁለት የአሜሪካ ወታደሮችም ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ጉዳቱ ቀላል በመሆኑ ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ግዳጃቸው ተመልሰዋል ተብሏል። አልባግዳዲ ለማምለጥ የሞከረበትን ዋሻ አነፍንፎ በማግኘት ሲከታተለው የነበረ ውሻ ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ወታደሮቹ ግዳጃቸውን ሲጨርሱ አብሯቸው መመለሱም ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

አሜሪካ አልባግዳዲ ስለመሞቱ እንዴት እርግጠኛ ሆነች?

ቅዳሜ ዕለት አልባግዳዲ ለመሸሽ ሲሞክር ወታደሮቹ በአይናቸው እንዳዩትና መሞቱን ማረጋገጣቸውን ከአሜሪካ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የተልእኮው ዋና መሪ የሆኑት ኮማንደርም መሳካቱን የሚገልጸውን 'ጃክፖት' የሚለውን ኮድ አሰምተዋል ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደገለጹት ከአልባግዳዲ ሬሳ የተወሰደው ቅንጣት በምርመራ እውነትም እሱ መሆኑን አረጋግጦልናል ብለዋል።

ምርመራው የተካሄደው ከወታደሮቹ ጋር አብረው በተጓዙ ባለሙያዎች ሲሆን በቦታው ተገኝተው ቀድመው ይዘውት ከነበረው የአልባግዳዲ የዘረመል (sample) ጋር አነጻጽረው እሱ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ከፍንዳታው የተረፈ የአልባግዳዲ ቀሪ የሬሳው አካል በሄሊኮፍተሩ እንዲወሰድ ተደርጓል።

የአሜሪካው የደህንነት አማካሪ ሮበርት ኦብራየን እንዳሉት የአልባግዳዲ ቀሪ የሬሳ አካላት ወደ ባህር ይጣላሉ። የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደንም በ 2011 ከተገደለ በኋላ ሬሳው ወደ ባህር መጣሉንም አክለዋል።

አልባግዳዲ የተገደለባት መንደር ባሪሻ ከሶሪያና ኢራቅ ድንበር በመቶ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን አካባቢውን ለምን እንደመረጠው መገመት ቀላል ነው ብለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ።

'' አልባግዳዲ ኢድሊብ የሄደው በአሜሪካ የሚደገፉት የኩርድ ሃይሎች በምስራቃዊ ሶሪያ ባጉዝ የተባለችውን መንደር ከአይኤስ ይዞታ በማስለቀቃቸው በአካባቢው የአይኤስ ወታደሮችን ለማደራጀት ነበር። ''

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በርካታ ለወደፊት ያቀዳቸውን ነገሮች የሚገልጹ መረጃዎች አግኝተናል ብለዋል።

'' ማንም ይሁን ማን ወደ ስልጣን ለመምጣት ካሰበ አንለቀውም። ማን ሊተካው እንደሚችልም እናውቃለን። በደንብ እየተከታተልናቸውም ነው።''